የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልዋሎ 3 – 3 ወልቂጤ

ዓዲግራት ላይ የተደረገውና 3-3 የተጠናቀቀውን ጨዋታ ተከትሎ የወልቂጤው ደግአረገ ይግዛውን አስተያየት ስናካትት በወልዋሎ በኩል አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልንም።

“አሸንፈን የምንወጣበት ዕድሎችም ፈጥረናል፤ ግን አልተጠቀምንባቸውም” ደግአረግ ይግዛው (ወልቂጤ ከተማ)

ስለ ጨዋታው

የዛሬው ጨዋታ የአንደኛው ዙር ማጠናቀቅያ ጨዋታ ነው። ቀድመው የተጫወቱ ቡድኖች ስለነበሩ ጫና ነበረው። ወልዋሎ ጠንካራ ቡድን ነው፤ ለሜዳው ሁለታችንም አዲሶች ብንሆንም። ወደ ሜዳ ከመግባታችን በፊት ሶስት ነጥብ ለማግኘት እና በአጠቃላይ ለሁለተኛው ዙር የሚያስተማምን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ነበር። ሆኖም ጨዋታው ባሰብነው መንገድ አልሄደም። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ግቦች አስተናገደን ከቅኝት ወጥተው ነበር። ተጫዋቾቹን ወደ ቅኝት ለማስገባት ምን ያህን ከባድ እንደነበር ታይቷል። የማትጠብቀው ነገር ሲከሰት ከአጨዋወትህ ትወጣለህ። በልምድ እነሱ የተሻሉ ናቸው፤ በመጀመርያው አጋማሽም ምን ያህል እንደጠቀማቸው አይተናል። የመስመር አጨዋወታቸው ለመቆጣጠር ትንሽ ተቸግረን ነበር። እየተመራን በተደጋጋሚ ጊዜ ግቦች ማስቆጠራችን የተጫዋቾቻችን ጥንካሬ ያሳያል። ለኛ ትልቅ ነጥብ ነው በውጤቱ ተደስተናል።

ጨዋታውን ጨርሰውት ነበር፤ ሆኖም እስከመጨረሻው ያደረግነው ተጋድሎ በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል። በተገኘው ውጤት በጣም ደስተኛ ነው።

ግቦች ከተቆጠረባቸው በኃላ ስላደረጓቸው ለውጦች

ከእረፍት መልስ ሶስተኛ ግብ ከተቆጠረብን በኋላ ‘ሪስክ’ ስለመውሰድ ነበር ስንነጋገር የነበረው። ሁለተኛው አጋማሽም በሶስት ተከላካይ ነው ለመጫወት የወስንነው። እንዲህ አይነት ውሳኔዎች ለመውሰን የምትገሰድበት ወቅት አለ። የማጥቃት ባሕሪ ያላቸው ተጫዋቾች ቀይረን በማስገባት ቶሎ ቶሎ ወደ ግን ለመድረስ አስበን ነበር የገባነው ተሳክቶልንም ግቦች አስቆጥረናል። አሸንፈን የምንወጣበት ዕድሎችም ፈጥረናል ግን አልተጠቀምንባቸውም።

ስለ ጫላ አስተዋፅዖ

ጫላ ለብሄራዊ ቡድንም የሚያስፈልግ ተጫዋች ነው። ምክንያቱም በማጥቃትም ተመልሶ በመከላከልም ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ጎል ላይ የመድረስ ችግር የለበትም ትንሽ ግብ የማስቆጠር ክፍተት ነበረበት እሱም ፈቷል። ዛሬም ቡድኑን ታድጓል። ትልቁ የማጥቅያ መሳርያችን ጫላ ነው። ለጫላ ጎልቶ መውጣትም የቡድኑ ጓደኞች ሚና ከፍተኛ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ