ሪፖርት | ወልዋሎ ወደ ሜዳው በተመለሰበት ጨዋታ ከወልቂጤ ጋር ነጥብ ተጋርቷል

ስድስት ግቦች በታዩበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታ ወልዋሎ እና ወልቂጤ ነጥብ ተጋርተዋል።

ከጨዋታው መጀመር በፊት ወልዋሎዎች ከዓመት በላይ በፈጀው የስታዲየም ዕድሳት ላይ ድርሻ ለነበራቸው አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በጨዋታው ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተሸነፈው ስብስብ ምስጋናው ወልደዮሐንስ እና ዘሪሁን ብርሀኑን በዓይናለም ኃይለ እና ፍቃዱ ደነቀ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ ከሜዳቸው ውጭ የተሻለ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ወልቂጤዎች ከባለፈው ሳምንት ስብስብ ዐወል መሐመድን በይበልጣል ሽባባው ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ተመጣጣኝ ፉክክር እና ስድስት ግቦች በታየበት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ቀጥተኛ አጨዋወትን ለመተግበር የሞከሩበት ሲሆን ባለሜዳዎቹ ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች የተሻሉ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ጁንያስ ናንጂቡ በሁለት አጋጣሚዎች ከራምኬል ሎክ እና ገናናው ረጋሳ ከመስመር የተሻገሩት ኳሶች ተጠቅሞ በግንባር ያደረጋቸው ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

በመጀመርያዎቹ ደቁቃዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ወልዋሎዎች በስምንተኛው ደቂቃ ጥረታቸው ሰምሮ ግብ አስቆጥረዋል። ጁንያስ ናንጂቡ ኢታሙና ኬይሙኔ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ አብርዶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ያልተቸገሩት ቢጫ ለባሾቹ በሄኖክ መርሹ ከርቀት ሙከራ አድርገዋል። በአርባኛው ደቂቃም ራምኬል ሎክ ከርቀት ግሩም ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

በአጋማሹ እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ቀጥተኛ እና የመስመር አጨዋወቶች ለመጠቀም ጥረት ያደረጉት ወልቂጤዎች በተለይም አዳነ በላይነህ ተጎድቶ እስከወጣበት ደቂቃ ድረስ ጥሩ የመስመር አጨዋወት ቢኖራቸውም ተጫዋቹ ጉዳት አስተናግዶ ከወጣ በኃላ የተጠቀሰው አጨዋወት በጥሩ መንገድ ለመተግበር ሲቸገሩ ተስተውለዋል። ሆኖም የጫላ ተሺታ እና መሐመድ ሁሴን ጥምረት በጨዋታው ተስፋ ሰጪ ነበር።

ወልቂጤዎች ከሞከሯቸው ሙከራዎች ውስጥ አሳሪ አልማህዲ ከርቀት አክርሮ መቶት ዓብዱልዓዚዝ ኬይታ ያዳነው ኳስ እና ሳዲቅ ሴቾ ከመስመር የተሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ጨርፎ ያደረጋት ሙከራ ይጠቀሳሉ። ወልቂጤዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ በጫላ ተሺታ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ልዩነቱን ማጥበብ ችለዋል። ፈጣኑ አማካይ መሐመድ ሁሴን ያመቻቸለት ኳስ ገፍቶ በግሩም ሁኔታ ነበር ግቧን ያስቆጠረው።

ሦስት ግቦች በታዩበት እና የወልዋሎ የመከላከል ክፍተት ጎልቶ በተስተዋለበት ሁለተኛው አጋማሽ ወልቂጤዎች ተሻሽለው የተመለሱበት እና ያገኟቸውን ዕድሎች የተጠቀሙበት ነበር።

የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት ዓይናለም ኃይለን በጉዳት ምክንያት ቀይረው ያስወጡት ቢጫ ለባሾቹ በአጋማሹ የተከላካይ ክፍላቸው ተፍረክርኮ በተጋጣሚ አጥቂዎች ሲፈተን ውሏል።

ወልዋሎዎች በመጀመርያው ደቂቃ ባገኙት የመዓዝን ምት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሆኖም ገናናው ረጋሳ ከመዓዝን ምት የተሻገውን ኳስ መትቶ በይድነቃቸው ኪዳኔ ድንቅ ብቃት ተመልሷል። በስልሳ ሶስተኛው ደቂቃ ደግሞ ወደ ድል ተቃርበው የነበረበትን ጎል አስቆጥረዋል። በወልዋሎ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኢታሙና ኬይሙኔ በአስቸጋሪ ሁኔታ ያገኛትን ኳስ ከግብ ጠባቂው በላይ ከፍ አድርጎ በማስቆጠር የግቡን ልዩነት አስፍቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ዓብዱልከሪም ወርቁን ቀይረው ካስገቡ በኃላ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ሰራተኞቹ በደቂቃዎች ልዩነት አከታትለው በማስቆጠር ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። በሰባ ሁለተኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ጫላ ተሺታ የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ የቡድኑን ተስፋ ሲያለመልም ከሁለት ደቂቃ በኃላም ጫላ ተሺታ ከተጫዋች ጋር ታግሎ ለአሐመድ ሁሴን ያቀበለውን ኳስ አጥቂው ግቧን አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

በመከላከል ችግሮች ሁለት ግቦች ካስተናገዱ በኋላ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ተቀይሮ በገባው ካርሎስ ዳምጠው እና ጁንያስ ናንጂቡ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ጁንያስ ናንጂቡ በሳጥኑ ጠርዝ አከባቢ ያገኘው ወርቃማ ዕድል መቶ የግቡን አግዳሚ የመለሰበት ኳስ እና ካርሎስ ዳምጠው አግዳሚው ገጭቶ የተመለሰው ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው አስቆጪ ሙከራ ባለሜዳዎቹ በድጋሚ መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ።

ወልዋሎዎች ከተጠቀሱት ሁለት ሙከራዎች ውጭም መሪ የሚሆኑበት አጋጣሚዎች አግኝተው ነበር። በተለይም ካርሎስ ዳምጠው ምስጋናው ወልደዮሐንስ ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ተንሸራቶ ያደረገው እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ባለሜዳዎቹን ሦስት ነጥብ ለማስጨበጥ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።

ስድስት ግቦች የታዩበት ጨዋታ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ወልዋሎዎች ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ አንድ ነጥብ ቢያሳኩም ወደ 15ኛ ሲንሸራተቱ ወልቂጤዎች ወደ 9ኛ ከፍ ብለዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ