መዲናዋ ላይ በነበረው የሙዚቃ ድግስ ምክንያት ከቅዳሜ ወደ ነገ የተዘዋወረውን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአዳማ ከተማን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በሊጉ አንድ ጊዜ ብቻ የተሸነፉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች (ታህሳስ 18 በጅማ 2-1) በተከታታይ አራት የሜዳቸው ላይ ጨዋታዎች ያገኙትን ድል በዓመቱ አጋማሽ በሚደረግ ጨዋታ ለመድገም እና በተከታዮቻቸው መሸነፍ ምክንያት የሊጉን መሪነት ወደ አስተማማኝ ደረጃ ከፍ አድርገው አንደኛውን የውድድር ዘመን አጋማሽ ለማገባደድ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አቻ | አሸነፈ | አሸነፈ | አሸነፈ | አሸነፈ |
ከአስከፊ የሊጉ ጅማሮ በኋላ ወደ ጥሩ የመነቃቃት ስሜት የገቡት ጊዮርጊሶች የቀድሞ ኃያልነታቸውን ዳግም ያገኙ ይመስላል። በተለይ ቡድኑ በጀብደኝነት የማጥቃት እና በርከት ያሉ ግቦችን ተጋጣሚ ላይ የማስቆጠር ልማድ እያዳበረ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ የቡድኑ ፊት መስመር ተሰላፊ ተጨዋቾች የግል ብቃት እና የእርስ በእርስ መስተጋብር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መጠንከሩ ቡድኑን ግርማ ሞገስ አላብሶታል። ይህንን ተከትሎ ነገም ቡድኑ በከፍተኛ የራስ መተማመን እና ጀብደኝነት የአዳማዎችን የግብ ክልል ለመጎብኘት ይታትራል ተብሎ ይጠበቃል።
ድብልቅ የጨዋታ አቀራረብን (ኳስን መቆጠቀጠር እና ቀጥተኝነትን) የሚከተለው ቡድኑ የመስመር ላይ ጥቃቶችን በተደጋጋሚ ሲሰነዝር ይታያል። በተለይ ደግሞ ቡድኑ የተጋጣሚን የመከላከል ቅርፅ በመበታተን ግቦችን ለማስቆጠር ይጥራል። ከዚህም መነሻነት ነገ ቡድኑ በእነ አቤል እና ጌታነህ ታታሪነት ታግዞ የአዳማን ጊዜ ከባድ ለማድረግ እንደሚጥር የገመታል።
በፋሲሉ ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ጋዲሳ መብራቴ በነገው ጨዋታ አለመኖሩ ቡድኑን ሊያሳሳ ይችላል። በተለይ ተጨዋቹ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ነገ ቡድኑ የሚያጎድሉ ይሆናሉ። ከእሱ በተጨማሪ የመስመር ላይ ጥቃቶችን ከኋላ ሆኖ የሚያስጀምረው ደስታ ደሙ በቅጣት ምክንያት አለመኖሩ ቡድኑን ሊጎዳ ይችላል።
ፈረሰኞቹ ከጋዲሳ መብራቴ እና ደስታ ደሙ በተጨማሪ አስቻለው ታመነ፣ ለዓለም ብርሃኑ እንዲሁም አቤል እንዳለን በነገው ጨዋታ በጉዳት እና ቅጣት ምክንያት አያገኙም።
የአዳማ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ |
በሜዳቸው የሚደረግ ጨዋታን ማሸነፍ የጀመሩት አዳማ ከተማዎች የዓመቱን የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ድል በመዲናዋ ለማግኘት አዲስ አበባ ከትመዋል።
እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ 6 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው አዳማ ከሰሞኑ መጠነኛ መሻሻሎች እያስመለከተ ይገኛል። እርግጥ አሁንም ቡድኑ ከሜዳ ውጪ ያለውን አይናፋርነት ባያስተካክልም ግብ አካባቢ ያሉበት ችግሮቹ እየተቀረፉ ይመስላል። በተለይ ደግሞ ቡድኑ ፍጥነት የተሞላበትን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመከተል የተጋጣሚን ጊዜ ከባድ ለማድረግ ይጥራል።
አዳማዎች በነገው ጨዋታ ቀጥተኝነትን ከፈጣን የሽግግር አጨዋወቶች ጋር በመቀላቀል ለጨዋታው እንደሚቀርቡ ይገመታል። በተለይ ደግሞ ቡድኑ ቦታቸውን በየቅፅበቱ በመቀያየር በሚጫወቱን የቡድኑ የወገብ በላይ ተጨዋቾች ታግዞ ጥቃቶችን ይሰነዝራል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ ወደ ራሱ የግብ ክልል በአብዛኛው በመጠጋት ጨዋታውን ያከናውናል ተብሎ ይታሰባል።
ከሜዳ ውጪ የሚደረጉ ጨዋታዎች ውጤት ወደ ራሱ የመውሰድ ከፍተኛ ችግር ያለበት አዳማ ነገም ይህ ችግሩ ዋጋ እንዳያስከፍለው አስግቷል። በተጨማሪም ቡድኑ ፈጣን አጥቂዎችን በሚያገኝነት ጊዜ ሲቸገር ይስተዋላል። ከዚህ መነሻነት ቡድኑ ነገ ችግሮች ውስጥ እንዳይገባ ያሳስባል።
ምንም አስጊ የጉዳት እና የቅጣት ዜና የሌለባቸው አዳማዎች ምናልባት ግብ ጠባቂያቸውን ጃኮ ፔንዜን በነገው ጨዋታ ላያሰልፉ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– አሁን በሊጉ እየተወዳደሩ ከሚገኙና በርከት ላለ ጊዜ ከተገናኙ ቡድኖች መካከል የሆኑት ጊዮርጊስ እና አዳማ እስካሁን በሊጉ 36 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 በማሸነፍ የበላይ ሲሆን አዳማ 7 ጨዋታ አሸንፏል። 11 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
– በግንኙነቶቹ ጊዮርጊስ 45፤ አዳማ ከተማ 24 አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)
ፓትሪክ ማታሲ
አብዱልከሪም መሐመድ – ሳላዲን በርጌቾ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ – ሄኖክ አዱኛ
ሙሉዓለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ
አቡበከር ሳኒ – ጌታነህ ከበደ – አቤል ያለው
ሳላዲን ሰዒድ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ደረጄ ዓለሙ
ሱሌይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – መናፍ ዐወል – ቴዎድሮስ በቀለ
አማኑኤል ጎበና – አዲስ ህንፃ – ከነዓን ማርክነህ
በረከት ደስታ – ዳዋ ሆቴሳ – ቡልቻ ሹራ
© ሶከር ኢትዮጵያ