ጫላ ቲሽታ ስለ ወቅታዊ አቋሙ ይናገራል

“ወልቂጤ ከተማን ምርጫዬ ማድረጌ ትክክለኛ ውሳኔ ነበር”

በሻሸመኔ ከተማ ካቶሊክ ሚሽን በሚባል ሜዳ የእግርኳስ ሕይወቱን የጀመረው ጫላ በሻሸመኔ ከተማ በቢጫ እንዲሁም በአረንጓዴ ቲሴራ ተጫውቷል። ከሻሸመኔ በመቀጠል በሰበታ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ የተጫወተው ፈጣኑ ተጫዋች በ2008 በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሩ የማጣርያ ጉዞ ባደረገው ቡድን ውስጥ ከአቡበከር ናስር፣ ሚኪያስ መኮንን እና የመሳሰሉት ጋር የበርካቶች ዓይን ውስጥ መግባት ችሎ ነበር።

ዘንድሮ አዲስ አዳጊውን ወልቂጤ ከተማን የተቀላቀለው ጫላ በሌሎች ክለቦች ካገኘው የተሻለ የመሰለፍ ዕድል በማግኘት በአንደኛው ዙር ወጥ ብቃቱን ማሳየት ችሏል። ዛሬ ከሜዳቸው ውጪ በወልዋሎ 3-1 ከመመራት ተነስተው አቻ በተለያዩበት ጨዋታም ሁለት አስቆጥሮ አንዱን በማመቻቸት ደምቆ ውሏል። ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ጫላ ተሺታ አሁን ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታ እና ስለቀጣይ እቅዱ ከዛሬው ጨዋታ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ከፕሪምየር ሊጉ ጋር የተዋወቅኸው በሲዳማ ቡና ነበር። ስለነበረህ ጊዜ አጫውተኝ?

ሲዳማ ቡና በነበረኝ ቆይታ በጣም ደስተኛ ነበርኩ ማለት ያስቸግረኛል። ከታችኛው ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ወደሚጫወት ቡድን ስትመጣ የራሱ ጫና እንዳለ ሆኖ በወቅቱ ሲዳማ ቤት እኔ ስመጣ በቦታዬ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ነበሩ። አሰልጣኙም እድል የሚሰጣቸው ቀድሞ ለነበሩት ተጫዋቾች ነው። በቦታው ለመጫወት እድል አላገኘሁም ነበር።

በመቀጠል ወደ አዳማ በውሰት አቅንተህ ነበር…

አዎ በእርግጥ ሲዳማ ቡና እያለሁ ነው የመጫወት እድል ለማግኘት ወደ አዳማ ከተማ በውሰት የሄድኩት። ከአዳማ ጋር ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። ሆኖም የአዳማ ጊዜን ካጠናቀቅኹኝ በኋላ ከሲዳማ ጋር ውል ስለነበረኝ ወደ ክለቡ ተመልሻለሁ።

ወልቂጤ ስትመጣህ የነበረውን ሒደት ብትገልፅልኝ ?

ወልቂጤ ለሊጉ አዲስ ነው። ከጎኔ የነበሩ ብዙ ሰዎች ወደዚህ ቡድን ፊርማዬን እንዳላኖር በስልክም በአካልም ተፅዕኖ ሲደርጉብኝ ነበር። እኔ ግን በራሴ እና በአሰልጣኝ ደግአረግ ሙሉ እምነት ነበረኝ። አሰልጣኙ በወጣቶች እና በሥራ ያምናል። ይህን ካጣራው በኋላ የቡድኑ የበላይ ኃላፊዎች ጋር አውርቼ አቅሜን በማውጣት መጫወት የተሻልኩኝ ሆኜ ከተገኘው መሰለፍ እድል እንደሚሰጥኝ ተማምኜ ነው ወደ ወልቂጤ የመጣሁት። በእርግጥም ያገኘሁት ይህን ነው። አሰልጣኙ በሥራ ያምናል። ሁሌም የሚመዝነው በሥራ እና በሥራ ነው። ወደ ወልቂጤ በመምጣቴ እጅጉን ደስተኛ ነኝ። ወልቂጤ ከተማ ምርጫዬ ማድረጌም ትክክለኛ ውሳኔ ነበር።

በቀጣይ ወልቂጤ በሊጉ እንዲቆይ በግልህ እና ከቡድን አጋሮችህ ጋር ምን ታስባለህ?
ቡድኑ ውስጥ ያለው ነገር በጣም የሚገርም ጥንካሬ መተሳሰብ ነው ያለው ስብስቡ እንደ አዲስ አይመስልም። አብረን የከረምን ነው የምንመስለው። አስተዳደሩ መልካም ነው፤ ከቀን ወደቀን እየተሻሻለ ነው። የሚያስፈልጉትን ነገር እያሟላላን ነው። ቀጣይ በአመራሩ በኩል ያለው ክፍተት ሲስተካከል ይበልጥ ከዚህ በላይ እነሆናለን። ቡድኑ ቀስ በቀስ በጣም እየተሻሻለ ነው። አሁን ላይ ሁላችንም ደስተኞች ነን።

በምርጥ አቋም ላይ ተገኛለህ። ስለ ግል ብቃትህ የምትለው ካለህ?

አሁን ላለሁበት ብቃቴ ላይ ብዙ ሠዎች ከኋላ አሉ። በተለይም ልጅ እያለው ፕሮጀክት ያሰራኝ አሰልጣኜ፣ ያሬድ አበጀ ሌሎችም ሰዎች አሉ። አሁንም እያሰለጠነኝ ያለው ደግያአረጋል ይግዛውን አመስግናለው። በተጫዋች ዘመንህ ምን እንደምትችል እና ምን እንደሚስፈልግህ የሚያውቅህ አሰልጣኝ ማግኘት በጣም ትልቅ እድል ነው። ወልቂጤ ቤት ስመጣ ብቃቴን አሳማኝ በሆነ መልኩ ለቡድኑ ለማድረስ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ይበልጥ ራሴን ለማሻሻል ነበር፤ ይህን ማሳካት ችያለው። በግሌም ብዙ ጊዜ ባይሆንም ልምምድ አደርጋለው። በቀጣይ ፈጣሪ ጤና ይስጠኝ እንጂ ካሁኑ የተሻሻለ ጫላ ይዤ ለምምጣት ነው የምጥረው።

ቡድኑንስ የት እንጠብቀው?

እኛ ስለ መውረድ አናስብም። ሰዎች ቡድኑ እንደሚወርድ ነው የሚያወሩት፤ ቡድናችን በማንኛውም ጨዋታ ተበልጦ እንኳን አያቅም። ቡድኑ እንደሚታሰበው ሳይሆን ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነን ነው ብቅ ያልነው። በሁለተኛው ዙር እጅግ ተሻሽለን ብቅ የምንል ይሆናል። ሀሳባችን ቡድኑ በዚህ ዓመት የደረጃ ሠንጠረዡ አጋማሽ ላይ ሆኖ ለማጠናቀቅ ያሰብነው። በግሌም እንደ ቡድንም የምንችለውን በማድረግ ቡድናችን ከፍ ለማድረግ ነው ሀሳባችን። ቡድኑን መደገፍ ከማይደክማቸው ደጋፊዎቻችን ጋር በመሆን የምናመጣውን ውጤት በፀጋ ተቀብለው ለነገ ተስፋ ሰጥተው እንዲደግፉን ነው በዚህ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው። በቀጣይ ጨዋታዎች ደረጃችንን የበለጠ እናሻሽላለን ብዬ አስባለው።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ