“እግርኳስን በማየት ብቻ የምትደሰትበት ስፖርት አይደለም” ማየት የተሳነው ወጣት ፍቃዱ ተስፋዬ
በዓለም እግርኳስ በተለይ ባደጉ ሀገራት አካል ጉዳተኞች በሚፈጠርላቸው አመቺ ከባቢ ምክንያት እግርኳስን ሲከታተሉ መመልከት አዲስ አይደለም። በቅርቡ እንኳ በእናቱ ሲልቪያ ጌሬኮ ድጋፍ ጨዋታዎችን ሲመለከት የነበረው የብራዚሉ ፓልሜይራስ ደጋፊ ኒኮላስ ታሪክ ዓለምን አነጋግሮ እስከ ፊፋ ሽልማት መድረሱ የሚታወቅ ነው። በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት የስታዲሞች ደኅንነት እና ኋላ ቀር መሠረተ ልማት አካል ጉዳተኞችን ወደ ሜዳ የሚጋብዝ አይደለም። ሆኖም እነዚህን ችግሮች ተቋቁመው አሁን አሁን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚወዷቸውን ክለቦች በስታዲየም ሲከታተሉ እየተመለከትን እንገኛለን።
በ15ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐግብሩን ትናንት ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን 3-1 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይም በኢትዮጵያ እግርኳስ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ሦስት ማየት የተሳናቸው የኢትዮጵያ ቡና የልብ ደጋፊዎችን በስታዲየም መመልከት ችለናል። ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ እነዚህ ወጣቶች ፍቃዱ ተስፋዬ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመርያ ዓመት ተማሪ)፣ ፋንታሁን አበራ (ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር ዓቀፍ ፈተና ተፈታኝ) እና መርሻ ሉልዬ (የሁለተኛ ደረጃ) ተማሪዎች ናቸው። ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ ማየት እንደተሳናቸው የሚገልፁት እነዚህ ወጣቶች በቅርብ ጊዜ ጨዋታዎችን መከታተል እንደጀመሩ ይናገራሉ። መርሻ እና ፍቃዱ ለመንገድ የሚሆን እጅግ ጥቂት የሆነ ዕይታ እንዳላቸው ያም ቢሆን ኳስን አጥርቶ ለመመልከት የሚያችል የዓይን ብርሀን እንደሌላቸው ለድረ-ገፃችን ተናግዋል። ትናንት በተፈጠረው ክስተት ዙርያ እና ማየት ተስኗቸው እግርኳስን ከመደገፍ ካላገዳቸው ምክንያታቸው ጋር በተያያዘ ከፍቃዱ ተስፋዬ ጋር ሶከር ኢትዮጵያ አጭር ቆይታ አድርጋለች።
ወደ ስታዲየም መጥታችሁ ለመደገፍ ያነሳሳችሁ ምክንያት ምድነው? ብዙ ጊዜ በእኛ ሀገር ደረጃ ይህ አልተለመደም ብዬ ነው?
ብዙ ሰዎች እግርኳስን የዕይታ ስፖርት ብቻ አድርገው ይወስዱታል። እግርኳስን በማየት ብቻ የምትደሰትበት ስፖርት አይደለም። በተለይ ድጋፍ ሲሆን ይለያል፤ ኳሱን ባያታየውም ከደጋፊው ጋር ሆነ የምታደርገው ጭፈራ፣ ክለብህን የምትደግፍበት ሁኔታ እና ስሜት ከምንም ነገር በላይ ይበልጣል። ሰዎችም ይሄንን ቢረዱ ደስ ይለኛል። ድጋፍ ከዕይታ በላይ ነው። እግርኳስ ሲሆን ደግሞ ይለያል።
የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል አያሰጋችሁም?
ወደ ስታዲየም ስንመጣ ይህ ሊያጋጥመን እንደሚችል እኛም እናቀዋለን፤ ይህን ዋጋ እንደምንከፍል አምነን ነው የምንመጣው። ሰዎችም ይመክሩናል፤ ስታዲየም ለምን ትሄዳላቹ የድብድብ ቀጠና ነው አትሂዱ ይሉናል። እኛም ይሄን እያወቅን ነው እየሄድን ያለነው። ትናንትም እንዳጋጣሚ ችግሩ በተፈጠረበት ቦታ እንገኝ ነበር። ሆኖም የችግሩን ገፈት ሳንቀምስ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማኅበር በፍጥነት ችግር ሳይደርስብን ወደ ሌላ ቦታ እንድናመራ አድርጎናል። ከዚህ በፊትም በአንድ አጋጣሚ ከትናንትናው በባሰ ሁኔታ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞ ነበር። እንግዲህ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ያለፉት ዓመታት ትልቅ ስጋት ሆኖብን ነበር። ዘንድሮ እንድያውም ትንሽ መለስ ብሎ ነበር። በእርግጥ የትናንቱ ችግር ዘር፣ ብሔር፣ ፖለቲካን እና ሐይማኖት የመሳሰሉትን ነገሮች መሰረት ያላደረገ ስፖርታዊ ብሽሽቅ ቢሆንም ችግሩ አላስፈላጊ ነው ብዬ አስባለው።
ሰዎች ቡድኖቻቸውን ሲደግፉ ያራሳቸው ደጋፊዎች የሚሰማቸውን ስሜት የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ያስሜት ሊሰማው እንደሚችል መረዳት አለባቸው። ምክንያቱም አንተ ስትመራ የሚሰማህ የደስታ ስሜት ተቃራኒ ቡድን ደጋፊም ያ ሊሰማው እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል። አንተ የምትናደደው ንዴት የተጋጣሚ ቡድን ደጋፊ ይናደዳል። ስታዲየም ለዓይነ ስውራን ብዙ አመቺ ባይሆንም ሁሌም የምንመጣው ድጋፉን፣ ጭፈራውን እና ኢትዮጵያ ቡናን ፈልገን ነው።
የፀጥታው ቦታ አስተማማኝ በሆነ የስታዲየም ክፍል ገብታቹ ለማየት ድጋፍ እንዲደረግላችሁ ያደረጋችሁት ጥረት አለ ?
ይሄንን ብዙዎቻችን አናስበውም፣ ፍላጎቱም የለንም። ብዙ አካል ጉዳተኛ እና ዓይነ ስውራን ወደ ስታዲየም አይመጣም። ልምዱ፣ ባህሉ የለም። ለብቻህ አንድ፣ ሁለት.. አስር ሆነህ በምትቀመጥበት ቦታ ላይ መከታተል ትንሽ ይከብደናል። ያው እንግዲህ እኛ እግርኳሱን በቀጥታ አናየውም። ከደጋፊው ጋር ነው አንድ ላይ ስሜቱን የምንጋራው። ደጋፊ መሐል መሆናችንን እንወደዋለን። ግን እንደነዚህ ያሉ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ሲኖር ተጓዳኝ የሆኑ ችግሮች ይመጣሉ። ምንም የተለየ ነገር እንዲደረግን ጥረት አላደረግንም። ወደ ፊትም የሚለወጥ ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም። ሆኖም ግን በተረጋጉ ፀጥታቸው አስተማማኝ በሆኑ ቦታዎች ማየት ለሚፈልጉ ሰዎች ቢዘጋጅ ጥሩ ነው። ይህ እንዲደረግ ጥረታችንን እንቀጥላለን። ተደባልቀን መደገፍ ለምንፈልግ ለእኛ ደጋፊዎች ግን በተለየ ቦታ መቀመጥ አይታሰበንም።
© ሶከር ኢትዮጵያ