ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ነጥብ ተጋርቶ መሪነቱን የሚያሰፋበትን ዕድል አመከነ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ዙሩን በበላይነት ማጠናቀቁን ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተጫውቶ ያለግብ አቻ ተለያይቷል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ጎንደር አምርቶ ከፋሲል ከነማ ጋር 1ለ1 ከተለያየው ስብስብ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም አብዱልከሪም መሐመድ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ ሳልሀዲን ሰዒድ እና አቡበከር ሳኒን በዛሬው ጨዋታ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት በማስገባት ጀምረዋል። እንግዶቹ አዳማ ከተማዎች ደግሞ በፉአድ ፈረጃ ምትክ የቡድኑ አምበል ሱሌይማን መሐመድን ወደ በተሰላፊነት በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳዩበት ሲሆን በመጀመሪያዎቹ 5 ደቂቃዎች ሁለት ግሩም አጋጣሚዎችን ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በ2ኛው ደቂቃ ሙሉዓለም መስፍን ከተከላካዮች ጀርባ የጣለለትን ኳስ በጃኮ ፔንዜ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታግዞ አቡበከር ሳኒ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ቢያገኝም ኳሷን ሳይጠቀምባት ቀርቷል። በተመሳሳይ በ4ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም አሻግሮት በጊዮርጊስ ተጫዋቾች ተሸርፎ የደረሰውን ኳስ ምንተስኖት አግኝቶ በግንባሩ የገጨው ኳስ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ሊወጣበት ችሏል።

መከላከል ላይ መሰረት በማድረግ ከቡድኑ ተከላካዮች እና ሁለት የመሐል አማካዮች ፊት በሚገኙት አራት ተጫዋቾች አስደናቂ ፍጥነትና የግል ጥረት ላይ በተንጠለጠለ ሁኔታ መልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ለመፍጠር ይዘውት የገቡት የጨዋታ ዕቅድ ብዙም ውጤታማ ሆኖ መመልከት አልቻልንም። በአጋማሹ በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ የተሻለ የማግባት አጋጣሚ መፍጠር የቻሉት አዳማዎች በ16ኛው ደቂቃ ከማዘን የተሻማውን ኳስ ሱሌይማን ሰሚድ የሞከረውና ተከላካዮች የተደርረቡበት እንዲሁም አስከትሎም ከነአን ማርክነህ ከሳጥን ጠርዝ የሞከረውና ፓትሪክ ማታሲ በአስደናቂ ሁኔታ ያዳነባቸው እንዲሁም በ34ኛው ደቂቃ ቡልቻ እና በረከት በግሩም አንድ ሁለት ቅብብል የሄዱት ኳስ በረከት ከማታሲ ጋር ተገናኝቶ አስቆጠረ ሲባል ፍሪምፖንግ ሜንሱ ደርሶ ያከሸፈበት አጋጣሚዎች ብቻ ናቸው።

በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል በ19ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከቅጣት ያሻማውን ኳስ ድንገት ከራቀው ቋሚ አጠገብ የነበረው ሜንሱ ሾልኮ ወደ ጎል የሸረፋት ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ ልትወጣ ችላለች።

በሒደት በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ጨዋታውን ጀምረው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሂደት እየተዳከሙ የመጡ ሲሆን አዳማ ከመከላከል በዘለለ ውጤታማ ያልነበረ መልሶ ማጥቃት ተጨማሪም ተሻጋሪ ኳሶች ከመስመር ለማሻማት ያደረጓቸው ጥረት ውጤታማ ካለመሆናቸው በሂደት እየደበዘዘ አሰልቺ መልክ የተላበሰው የመጀመሪያ አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል።

በሁለቱ ክለቦች ተጫውቶ እንደማሳለፉ በልዩ ሁኔታ መዘከር ሲገባው በመጀመርያው የጨዋታ ጅማሬ የተዘነጋው ሞገስ ታደሰን የሚያስታውሰው ህሊና ፀሎት ከእረፍት መልስ ሊታሰብ መቻሉ ግርምትን አጭሯል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጊዮርጊሶች ረጃጅም ኳሶች እና በተደጋጋሚ ወደ ጎል በሚጣሉ ፈጣን ኳሶች ወደ ጎል ቢደርሱም ኳሶቹ በተከላካዮች እየተቋረጡ የጨዋታውን መልክ አሰልቺ ያደረገው ሲሆን በተለይ ከ60 ደቂቃ በኋላ ያልተረጋጋ እንቅስቃሴ ተመልክተናል። ሄኖክ አዱኛ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ያሾለከውን ኳስ አቤልና ሳላዲን ሳጥን ውስጥ ሲገባበዙ በተፈጠረ መዘናጋት አቤል ሳይጠቀምበት ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ለፈረሰኞቹ መልካም የጎል አጋጣሚ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ከነዓን ማርክነህ ከሱሌይማን መሐመድ በጥሩ መናበብ መስርተውት የሄዱትን ኳስ ሱሌይማን ወደ ሳጥን አጥብብቦ አምስት ከሀምሳ ውስጥ ለማቀበል አስቦ ግብጠባቂው ማታሲ የተቆጣጠረበት የአዳማዎች ምላሽ ሳይሳካ ቀርቷል።

ጨዋታው ወደ እረፍት አልባ የደርሶ መልስ የማጥቃት እንቅስቃሴ አምርቶ 64ኛው ከነዓን ነፃ ኳስ አግኘቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጭ የወጣበት፣ በጊዮርጊስ በኩል ደግሞ 69ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ ከተከላካዮች መሐል የጣለለትን በማይታመን ሁኔታ አቤል ያለው ከግብጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ወደ ሰማይ የሰደዳት ኳስ መሪ ልታደርጋቸው የምትችል ጥሩ አጋጣሚ ነበረቸ።

ጨዋታው ወደ መገባደዱ ሲቃረብ በአዳማ በኩል በጥንቃቄ አጨዋወት አጥብቀው መከላከልን ምርጫቸው ሲያደርጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ጫና ለማሳደር ሙከራ ማድረጋቸውን ቀጥለው ሀይደር ሸረፋ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ጃኮ ፔንዜ በሚገርም ሁኔታ ያዳነበት እንዲሁም የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ጌታነህ ከበደ ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ የሚያስቆጩ ሆነው አልፈዋል። ተጠባቂው ጨዋታም ምንም አይነት ጎል ሳይስተናገድበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ወደ አራት ነጥብ ልዩነተ የሚያሰፋበትን ዕድል ሲያመክን አዳማ ከተማ ወደ ዘጠነኛ ከፍ ማለት ችሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ