በ15ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት በዚህ መልኩ አቅርበነዋል።
“ለአንዳንድ በተጨዋቾች ላይ ለሚጮሁ ደጋፊዎች መናገር የምፈልገው ነገር አለ” ሰርዳን ዝቪጅኖቭ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ስለ ጨዋታው
ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን ጠብቄ ነበር። ምክንያቱም የአዳማ ተጨዋቾች ለረጅም ጊዜ አብረው የተጫወቱ መሆናቸው እና ጥንቃቄ በተሞላበት አቀራረብ ለአንድ ነጥብ በመምጣታቸው ነው። የእኔ ተጨዋቾች በርካታ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ማስቆጠር ግን አልቻሉም። በየጨዋታው እንድናሸንፍ እና መሪ ሆነን እንድንቀመጥ መጠበቁም ጫና ነበረው።
በእርግጥ አሁንም መሪ ነን፤ ነገር ግን ለአንዳንድ በተጨዋቾች ላይ ለሚጮሁ ደጋፊዎች መናገር የምፈልገው ነገር አለ። መጮህ ካለባቸውም እኔ ላይ እንዲጮሁ ነው፤ ተጫዋቾቹን ይተዋቸው። ምክንያቱም ያለፉትን ስድስት ወራት ጠንክረው ሲሰሩ ቆይተዋል። ደግሞም ላለፉት ሁለት የውድድር ዓመታትም በውድድሩ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉ መሪ አልነበረም። ስለዚህ ደጋፊዎች ትዕግስተኛ እንዲሆኑ እጠይቃለው። ከፋሲል ከነማ በሁለት ከመቐለ ደግሞ በሦስት ነጥቦች በልጠን አሁንም እየመራን ነው። አሁንም ቻምፒዮን የመሆን ሰፊ ዕድሉ አለን። አንዳንድ ደጋፊዎች ለምን በተጫዋቾች ላይ እንደሚጮሁ አይገባኝም። መጮህ ካለባቸውም እኔ ላይ ይጩሁ።
” ያሰብነውን አሳክተናል” የአዳማ ምክትል አሰልጣኝ ደጉ ዱባም
ስለ ጨዋታው
በሁለታችንም በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻልንበት ቆንጆ ጨዋታ ነበር።
ጥንቃቄ ስለመምረጣቸው
እነርሱ ረጃጅም ኳሶችን ለፈጣን አጥቂዎቻቸው በማድረስ ለመጠቀም አስበው ነበር። ያም ቢሆን በእኛ በኩል የጎል እድሎችን መፍጠር ችለናል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ነው። የሊጉ መሪ ጠንካራ ቡድን ነው። እንደዛም ሆኖ ያሰብነውን አሳክተናል።
የተጫዋቾች መልቀቂያ ማስገባት ቡድኑን በቀጣይ አይረብሸውም?
በእርግጥ በተወሰነ መልኩ ተፅዕኖ አለው። ከበላይ አካሎች ጋር ተነጋግረው ያለውን ችግር ይፈታሉ ብዬ አስባለው። እንደ አጋጣሚም ሆኖ የቡድኑ የበላይ አመራሮች በሙሉ ዛሬ ከቡድኑ ጋር አብረው ይገኛሉ። በእርግጠኝነት ሁለተኛው ዙር ከመግባታችን በፊት ያለውን ችግር ለመቅረፍ ቃል ገብተውልናል።
አንደኛው ዙር እንዴት አለፈ ?
ዘንድሮ ብዙ ችግሮችን አልፈን ነው እዚህ የደረስነው። ከደሞዝ ክፍያ ጋር ልምምድ ሳንሰራ የተጫወትንበት ጊዜ ሁሉ ነበር። እንደዛም ሆኖ ለእኛ የያዝነው ውጤት ጥሩ ነው። እነዚህ ነገሮች ተቀርፈው ቡድኑ ሙሉ ሲሆን ወደ ፊት መሄድ የሚችል ቡድን መሆኑን አሳይተናል። በሁለተኛው ዙር ጠንክረን እንቀርባለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ