ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዓርብ ጀምሮ ትናንት በተደረገ ጨዋታ መገባደዱ ይታወሳል። በአንደኛው ዙር የመጨረሻ ሳምንት ላይ በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ጥሩ ብቃታቸውን ማሳየት የቻሉትን 11 ተጫዋቾችንም በሚከተለው መልኩ አቅርበንላችኋል። 

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች እንዲሁም ጨዋታዎችን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ለተጫዋቾች በሚሰጡት ነጥብ መነሻነት ነው። 

* ምርጫው ተጫዋቾች በዕለቱ በተሰለፉበት ጨዋታ ላይ ባሳዩት ብቃት ላይ የተመረኮዘ ነው።

* ፎርሜሽኖች እና የተጫዋቾች ቦታዎች በምርጫው የተካተቱት ተጫዋቾችን ባማከለ መልኩ በየጊዜው ሊቀያየሩ ይችላሉ። 

አሰላለፍ ፡ 4-2-3-1


ኦቬር ኦቮኖ (ሀዲያ ሆሳዕና)

በዚህ ሳምንት ሀድያ ሆሳዕና ከረጅም ጊዜ በኋላ ሦስት ነጥቦች ይዞ የመጀመሪያውን ዙር ሲፈፅም የኢኳቶሪያል ጊኒያዊው ግብ ጠባቂ ድርሻ ቀላል የሚባል አልነበረም። በተለይ ጅማ አባ ጅፋሮች በሁለተኛው አጋማሽ በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ሀዲያ ግብ ክልል ሲያሻገሩ የነበሩትን ኳሶችን ከመቆጣጠሩ ባለፈ ሁለት ግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማምከን ጥሩ ቀን አሳልፏል። ለሁለተኛ ጊዜም በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።


አሕመድ ረሺድ (ኢትዮጵያ ቡና)

የአማኑኤል ዮሐንስን አለመኖር ተከትሎ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የገባው አሕመድ ከመከላከል ተሳትፎው ባለፈ በቁጥር በርከት ብሎ የተጋጣሚን ሳጥን ለማጥቃት በሚፈልገው የካሳዬ አራጌው ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ በሜዳው የላይኛው ክፍል ያልተጠበቀ አፈትላኪ ሩጫዎችን በማድረግ ሁነኛ የቡድኑ የማጥቂያ አማራጭ እየሆነ መጥቷል። ኢትዮጵያ ቡናዎች አደገኛ በነበሩበትና ወላይታ ድቻን እጅግ በፈተነው ወደ ቀኝ መስመር ባደላው የማጥቃት ሂደታቸው ውስጥ የአህመድ ረሺድ ተሳትፎ የጎላ ነበር። ውብሸት ዓለማየሁ በራሱ ግብ ላይ ላስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ኳሷን በማሻገርም ተሳትፎ አድርጓል።


ፍሬዘር ካሳ (ድሬዳዋ ከተማ)

ወጣቱ ተከላካይ የመሰለፍ ዕድል ፍለጋ ባመራበት ድሬዳዋ ከተማ ያገኘውን እድል እየተጠቀመበት ይገኛል። ተጫዋቹ በዚህ ሳምንት ጠንካራው መቐለ 70 እንደርታን ሲረቱ ለኋላ መስመሩ ጥንካሬ ከፍተኛ ድርሻ የተወጣ ሲሆን በተለይም የፊት አጥቂው ኦኪኪን በመቆጣጠሩ ረገድ የተዋጣለት እንቅስቃሴ አድርጎ ቡድነለ ጎል ሳይቆጠርበት እንዲወጣ አድርጓል። በዚህም በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ተካቷል።


አዩብ በቀታ (ሀዲያ ሆሳዕና)

በሀዲያ ሆሳዕና በግሉ ጥኩ አቋም እያሳየ የዘለቀው አዩብ ቡድኑ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ሙሉ ነጥቦችን ሲያሳካ ብቸኛዋን እና ማራኪዋን የማሸነፊያ ግብ ከቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል። ከዚህ ባሻገር በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማስጀመር ጥሩ የተንቀሳቀሰ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ በተደራጀ የመከላከል አጨዋወት በጊዜ ያገኟትን መሪነት አስጠብቀው እንዲወጡ ትልቁን ሚና መወጣት ችሏል። በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥም ለሁለተኛ ጊዜ መካተት ችሏል።


ሳሙኤል ተስፋዬ (ባህር ዳር ከተማ)

ይህ ተስፈኛ የግራ መስመር ተጫዋች በእሁዱ የባህር ዳር ከተማ እና ስሑል ሽረ ጨዋታ ጥሩ ጊዜን አሳልፏል። በተለይ የመስመር ላይ ጥቃቶችን ከኋላ በማስጀመር እና የተሳኩ ኳሶችን ከመስመር ወደ ሳጥን በማሻገር ቡድኑን አገልግሏል። ከዚህ በተጨማሪ የቆሙ ኳሶችንም ወደ ግብነት ለመቀየር የሚሞክርበት መንገድ ድንቅ ነበር። ይህንን ተከትሎ ይህ ወጣት የግራ መስመር ተጨዋች ለመጀመሪያ ጊዜ የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።


ዳንኤል ኃይሉ (ባህር ዳር ከተማ)

አይደክሜው የአማካይ መስመር ተጫዋች በዚህ ሳምንት ምርጥ ጊዜን አሳልፏል። ዳንኤል የቡድኑን ሚዛን ከመጠበቁ እና የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ከማፋጠኑ በተጨማሪ ቡድኑን በአምበልነት በመምራት እና በማነሳሳት ጠቅሟል። ከምንም በላይ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው ግብ ሳያስተናግድ ለወጣው ቡድኑ ጠንካራ የመከላከል ሽፋን ሰጥቷል። ይህንን ተከትሎ ዳንኤል ለሁለተኛ ጊዜ የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።


ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)

ፋሲል ከነማ ከመምራት ተነስቶ በሀዋሳ የ3ለ2 ሽንፈት ቢገጥመውም ሱራፌል ዳኛቸው ያደረገው እንቅስቃሴ እጅግ ድንቅ ነበር፡፡ እስከ አስራ አምስተኛ ደቂቃ ድረስ ሁለት ግብ አስቆጥረው ሲመሩ ለቡድኑ ፈጣን እንቅስቃሴ ከነበረው ድርሻ በዘለለ እጅግ ማራኪ የቅጣት ምትም አግብቷል፡፡ ሆኖም ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በመዳከማቸው በሀዋሳ ሶስት ግብ ፋሲሎች ቢቆጠርባቸውም ተጫዋቹ በግሉ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ያደረጋቸው ሙከራዎች እንዲሁም የፈጠራቸው የማጥቃት አጋጣሚዎች በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ለሁለተኛ ጊዜ እንዲካተት አስችሎታል።


ኢታሙና ኬሙይኒ (ወልዋሎ)

ከረጅም ጊዜያት በኋላ ባለፈው ጨዋታ ጥሩ ብቃት በማሳየት ጥሩ ቀን ያሳለፈው ናሚቢያዊው ሁለገብ ኢታሙና ምንም እንኳ አበርክቶው ቡድኑን ሙሉ ሦስት ነጥብ ባያስገኝም በግሉ ምርጥ ሳምንት አሳልፏል። ከወልቂጤ ጋር በነበረው ጨዋታ አንድ ግብ አስቆጥሮ አንድ ለግብ የሆነ ኳስ ያቀበለው ይህ ተጫዋች ከተጠቀሱት አበርክቶዎች ውጪም ጁንያስ ናንጂቡ ላመከናቸው ንፁህ የግብ ዕድሎች መፈጠር ድርሻው የጎላ ነበር። ቀስ በቀስ ከአዲሱ ቦታው ጋር እየተላመደ የመጣው ኢታሙና በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሲገባ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።


ሚኪያስ መኮንን (ኢትዮጵያ ቡና)

በዚህ ሳምንት ሌላው ህዩነት ፈጣሪ ነበር። ሁለት ግቦችን አመቻችቶ ያቀበለው ሚኪያስ ከሰሞኑ ጥሩ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል። ግሩም የቴክኒክ ብቃት ባለቤት የሆነው ሚኪያስ ውሳኔ አሰጣጡ ላይ በሒደት መሻሻሎች እያመጣ መሆኑንም እያስመሰከረ ይገኛል። በድቻው ጨዋታ ከኋላው የተሰለፈው የመስመር ተከላካዩ አሕመድ ረሺድ ቀኝ መስመሩን ይዞ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ስለሚሳተፍ ለእሱ በቂ ክፍተት ለመስጠት ወደ መሐል እያጠበበና ወደ ውስጥ እየሰበረ በመግባት ተደጋጋሚ ጫናዎችን ሲፈጥር ተስተውሏል። በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ቡድን ውስጥም ለመጀመርያ ጊዜ ተካቷል።


ጫላ ተሺታ (ወልቀጤ ከተማ)

በዚህ ሳምንት ምርጥ ብቃት አሳይተው ቡድናቸው ተሸክመው ከወጡት ተጫዋቾች ቀዳሚው ጫላ ተሺታ ነው። ሠራተኞቹ ከኋላ ተነስተው ከወልዋሎ ጋር አቻ ሲለያዩ ሁለት ግቦች አስቆጥሮ አንድ ለግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው ይህ ፈጣን የመስመር ተጫዋች በጨዋታው ላይ የነበረው ውጤታማነት እና የጨዋታ ፍላጎት እጅግ የሚደነቅ ነበር። ዘንድሮ በወጥነት ድንቅ ግልጋሎት ያበረከተው ጫላ ለአራተኛ ጊዜ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ተካቷል።


አሕመድ ሁሴን (ወልቂጤ ከተማ)

ቶጓዊውን አጥቂ ጃኮ ክለቡን ከለቀቀ በኋላ መልሶ ያገኘውን የመሰለፍ ዕድል በአግባቡ እየተጠቀመ የሚገኘው አሕመድ ሁሴን ቡድኑ ወደ ዓዲግራት አምርቶ ወሳኝ ነጥብ ሲያሳካ ትልቅ ድርሻ ነበረው። በጨዋታው አንድ ግብ አስቆጥሮ አንድ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው አሕመድ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የነበው እንቅስቃሴ እና ከጫላ ተሺታ ጋር የነበረው ጥሩ ተግባቦት ቡድኑ ከኋላ ተነስቶ ጣፋጭ አንድ ነጥብ እንዲያሳካ ትልቅ ድርሻ ነበረው። በዚህም ለሁለተኛ ጊዜ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።


ተጠባባቂዎች

መክብብ ደገፉ (ወላይታ ድቻ)
ላውረንስ ላርቴ (ሀዋሳ ከተማ)
ያሲን ጀማል (ድሬዳዋ ከተማ)
ፍፁም ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)
ሄኖክ ድልቢ (ሀዋሳ ከተማ)
መስፍን ታፈሰ (ሀዋሳ ከተማ)
ብዙዓየው እንዳሻው (ጅማ አባ ጅፋር)


© ሶከር ኢትዮጵያ