የፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ትናንት ሲጠናቀቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ሊያሰፋበት የሚችለውን አምክኗል። ፋሲል እና መቐለ ዙሩን በሽንፈት ደምድመዋል። በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ከተማ ወደ ድል ሲመለሱ ኢትዮጵያ ቡናም ዙሩን በድል አጠናቋል። በየሳምንቱ እንደተለመደው በዚህኛው የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ክለብ ነክ ጉዳዮችን በተከታይ መልክ አሰናድተናል።


👉ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን የሚያሰፋበት ዕድል አምክኗል

ከትላንቱ ጨዋታ በፊት በተከታዮቹ ነጥብ መጣል የተነሳ ዙሩን በበላይነት ማጠናቀቃቸውን አስቀድመው ያረጋገጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አዳማን አሸንፈው ከተከታያቸው ያለውን ልዩነት ያሰፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ከአዳማ ከተማ ጋር 0-0 በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ከፋሲል ከተማ ጋር 2 አቻ ከተለያየው የቡድን ስብስብ ውስጥ የአራት ጨዋታዎች ለውጥ ያደረጉት ፈረሰኞቹ የአዳማ ከተማን ወደ ኋላ የተሰበሰበውን የመከላከል አደረጃጀት አልፎ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በርካታ ረጃጅም ኳሶች በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተስተዋለበት በዚሁ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይ በሁለቱ አጋማሾች የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች የተሻሉ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ካለፉት ሁለት ዓመታት የተሻሻለውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ባስመለከተን የመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የተሻለን ነገር እያለሙ የሁለቱኛውን ዙር ጅማሮ እንዲጠባበቁ አድርጓል።

👉ድሬዳዋ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ መቐለን አስደንግጧል

በሊጉ ግርጌ እየዳከረ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ በዚህኛው ሳምንት መቐለን አስተናግዶ ዳኛቸው በቀለ በ90ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ በማሸነፍ የመጀመሪያው ዙር ባልተጠበቀ ድል ደምድመዋል። የማሸነፊያ መንገዱ ጠፍቷቸው የሰነበቱት ድሬዎች እንደ ቡድን ከፍተኛ መነሳሳትን ባሳዩበት ጨዋታ በስተመጨረሻም ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክተው መውጣት ችለዋል። በሁለተኛው ዙር ከወራጅ ቀጠና ለመላቀቅ ከፍተኛ የቤት ሥራ የሚጠብቃቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ይህ ድል ለቀጣይ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ጥሩ መነሳሻ ይሆናቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

መቐለዎች ከተከታታይ ሽንፈት መልስ ባለፈው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በመርታት ወደ አሸናፊነት ስነልቦናቸው የተመለሱ ቢመስልም አሁንም በወጥነት መንፈሱን ለማስቀጠል ሳይችሉ ቀርተዋል። ቡድኑ በሁለተኛው ዙር አሁንም በርካታ የጥገና ሥራ እንደሚጠብቀው አሁንም አሳይቶ ያለፈ ጨዋታ ሆኖ አልፏል።

👉ፋሲል ከነማ አሁንም ከሜዳ ውጭ እየተቸገረ ነው

በመጀመሪያው አጋማሽ ድራማዊ ክስተቶችን ባስተናገደው የሀዋሳው ጨዋታ ፋሲል ከነማ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃ 2-0 ከመምራት ተነስተቶ በተከታታይ በሀዋሳ ከተማ በተቆጠሩበት ሦስት ግቦች አሁንም ከሜዳ ውጭ ያለው ደካማ ክብረወሰን እንዲቀጥል ሆኗል።

በአዎንታዊ የጨዋታ አቀራረብን በሁሉም ጨዋታዎች ይዞ የሚገባው ቡድኑ አጥቂው ሙጂብ ቃሲም በሚቸገርባቸው ጨዋታዎች አሁንም ጨዋታዎችን አሸንፎ ለመውጣት እንደሚቸገር በዚህ ሳምንትም ተስተውሏል። በተለይ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሙጂብ ብቃት ላይ የተመረኮዘው ጨዋታዎችን የመወሰን አቅሙ እሱ ሲቸገር ተክቶት በግሉ ጨዋታዎችን የሚወስኑ ተጫዋቾችን ያጣ ይመስላል።

ከዐምናው ስብስብ ብዙም ያልተለወጠው ቡድኑ እንደ ቡድን ከሜዳ ውጭ ሲጫወት ያለውን ሞገስ የመመለሱ ጉዳይ አሁንም መልስ የሚሻ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል።

👉 መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኘው ሆሳዕና ድል ቀንቶታል

ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቅጥር አንስቶ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳዮ የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በዚህኛው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርን ድል አድርገዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ግቦችን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት ሀዲያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ማጠናቀቂያ ላይ የተገኘችን ብቸኛ ግብ በሁለተኛው አጋማሽ በግሩም የመከላከል እንቅስቃሴ አስጠብቀው በመውጣት የናፈቁትን ሶስት ነጥብ አሳክተው መውጣት ችለዋል።

ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስለመሻሻላቸው በግለፅ ፍንጮች እያሳዩ የነበሩት ሆሳዕናዎች አሁንም ፊት መስመራቸው ላይ የሚታየው የስልነት ችግር በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽሎ ከቀረበ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉ኢትዮጵያ ቡና ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ አሸንፏል

አስቸጋሪ የጨዋታ ሳምንታትን ያሳለፉት ኢትዮጵያ ቡና በስተመጨረሻም ከአምስት ጨዋታዎች በኃላ ወላይታ ድቻን በማሸነፍ በአሸናፊነት የመጀመሪያ ዙሩን ማጠናቀቅ ችለዋል። በሰበታ ጨዋታ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ማስቆጠር ባለመቻላቸው ብቻ በአቻ ውጤት ቢፈፅሙም በዚህኛው ሳምንት ግን በሦስት አጋጣሚዎች ግብን አስቆጥረው አሸንፈው ለመውጣት በቅተዋል። በከፍተኛ ጫና ውስጥ የነበሩት አሰልጣኝ ካሳዬ እና ተጫዋቾቻቸው ከዚህ ጫና በተወሰነ መልኩ ለመላቀቅ አስፈላጊ የነበረውን ሶስት ነጥብን በዚህኛው ሳምንት አስመዝግበዋል።

ቡድኑ በሚቸግርባቸው ወቅቶች እንደአማራጭነት እየተገበሩት የሚገኘው የረጃጅም ኳሶች አጨዋወት በዚህኛው ሳምንትም በተመለከትንበት በዚሁ ጨዋታ ድል በማድረጋቸው ከክለቡ የልብ ደጋፊዎች ዳጎስ ያለ የማትጊያ ክፍያም ያገኙበት የጨዋታ ሳምንት ነበር።

👉ጀብደኛው ወልቂጤ ከተማ

ከሜዳ ውጭ በተለየ ከመመራት ተነስቶ ነጥቦችን መያዝ እጅግ አዳጋች በሆነበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዚህኛው ሳምንት ወልቂጤ ከተማዎች 3-1 ከመመራት ተነስተው 3 አቻ ተለያይተው ከአዲግራት ተመልሰዋል።

በቅርቡ እድሳቱን ያጠናቀቀው የአዲግራት ስታዲየም ባስተናገደው የመጀመሪያ ይፋዊ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ 3 ግቦችን አስቆጥረው በታደሰው ስታዲየም ለመጀመሪያ ጊዜ ክለባቸው ለመደገፍ የታደሙት ደጋፊዎች ፈንጠዝያ ውስጥ መክተት ቢችሉም የተከላካይ ቁጥራቸውን ቀንሰው የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት በሁለተኛው አጋማሽ በጀብደኝነት ሲያጠቁ የነበሩት ወልቂጤዎች አቻ ከመሆንም አልፈው ጨዋታውን ማሸነፍ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎችን ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀሩ እንጂ አሸንፈው በወጡ ነበር።

ጥንቃቄ በበዛበት ሊጋችን ላይ መሰል ቡድኖችን ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት ወቅት መሰል ሒደቶች መበረታት የሚገባቸው ናቸው።

👉ሲዳማ ቡና በመከላከሉ ረገድ እየተሻሻለ ይመስላል

ምርጥ የአጥቂ መስመር ጥምረት ባለቤት የሆነው ቡድኑ ግቦችን ቢያስቆጥርም በቀላሉ ግቦችን በማስተናገዱ የተነሳ ነጥቦችን በተደጋጋሚ ሲጥል ይስተዋል ነበር ፤ በሂደት ግን ለዚህም ክፍተት መፍትሄ የተገኘለት ይመስላል።

በተከታታይ ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማ እና ሰበታን ሲረታ ቡድን ምንም ግብ ሳይቆጠርበት በጠባብ የግብ ልዩነት እያሸነፈ ይገኛል።

ከግለሰባዊ ጉዳዮች ይልቅ አጠቃላይ የአደረጃጀት ችግር ሲስተዋልበት የከረመው ቡድኑ በርከት ያሉ ተጫዋቾች በመከላከል ሒደት ተሳታፊ በማድረግ ይህን ክፍተት ለመድፈን እየሞከሩ ይመስላል። ይህም በተወሰነ መልኩ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ቢያሳድርም ቡድኑ ከነበረበት የመከላከል ድክመት አንፃር ከሰሞኑ
የታየው መሻሻል ይበል የሚያሰኝ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ