በፕሪምየር ሊጉ አንደኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች የተስተዋሉ ተጫዋች ነክ ጉዳዮችን እነሆ!
👉የበረከት አማረ ደስታ አገላለፅ
ኢትዮጵያ ቡናን ወላይታ ድቻን በረታበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረበት ግብ ሲመራ ቢቆይም በሁለተኛው አጋማሽ በ66ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ታደሰ የአቻነቷን ግብ ሲያስቆጥር ከአስቆጣሪው በላይ የበረከት አማረ ደስታ እጅግ የተለየ ነበር። ጨዋታውን በተጠባባቂ ወንበር የጀመረው ግብጠባቂው በረከት ግቧ ስትቆጠር ከተጠባባቂዎች መቀመጫ ተነስቶ እየሮጠ ወደ ሜዳ የገባው በከፍተኛ ስሜት ሜዳ ውስጥ ሲሮጥ የታየው በረከት አማረ አጠቃላይ ቡድኑ ተጫዋቾች ላይ የነበረውን የጫና ስሜትና ጭንቀት መላቀቅን የገለደች የጨዋታ ቅፅበት ነበረች።
👉የወልቂጤ የነፍስ አዳኝ ጫላ ተሺታ እና ተስፈኛ አጣማሪው አሕመድ ሁሴን
በዚ ሳምንት በበርካታ ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ቀዳሚው ነው። በግሉ ሁለት ግቦች አስቆጥሮ አሕመድ ሀሴን ላስቆጠረው ግብ አመቻችቶ ያቀበለው ይህ ፈጣን አጥቂ ሠራተኞቹ ከሜዳቸው ውጭ ከኃላ ተነስተው ነጥብ ተጋርተው ሲወጡ በጨዋታው ኮከብ ሆኖ ውሏል። በጨዋታው ሁለት ለአንድ ግንኙነቶች ሳይቀር በማሸነፍ የተጋጣሚን የተከላካይ ክፍል ሲረብሽ የዋለው ጫላ ከዚ በፊት በአጨራረስ ላይ ይታዩበትን የነበሩትን ጥቃቅን ስህተቶችን አርሞ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች እስከ መሆን ደርሷል።
ተጫዋቹ በግሉ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጭም ከአሕመድ ሁሴን ጋር የፈጠረው ጥምረት ምን ያህል አስፈሪ እየሆነ እንደመጣ በባለፈው ጨዋታ ተስተውሏል። ተጫዋቾቹ በተጠቀሰው ጨዋታ በድምር ካስቆጠሯቸው ሦስት ግቦች እርሰ በርሳቸው አንድ አንድ ለግብ የሚሆኑ ኳሶች ማመቻቸታቸው ጥምረቱ ምን ያህል ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ማሳያ ነው።
👉አብዱልከሪም መሐመድ እና አቡበከር ሳኒ ላይ ያነጣጠሩት ተቃውሞዎች
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ ያለ ግብ አቻ በተለያየበት ጨዋታ በመጀመርያ ተሰላፊነት ጨዋታውን የጀመሩት የመስመር ተከላካዩ አብዱልከሪም መሐመድ እና አቡበከር ሳኒ ከተወሰኑ የክለቡ ደጋፊዎች ተቃውሞ ሲያስተናግዱ ተስተውሏል።
ምንም እንኳን ሁለቱም ተጫዋቾች በእስካሁኑ የ15 ሳምንት ቆይታ በቂ የመሰለፍ እድል ካለማግኘት ጋር በተገናኘ ወቅታዊ ብቃታቸውን ለማሻሻል የተወሰነ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ቢታመንም በቅዱስ ጊዮርጊስ ደረጃ ለዋንጫ በሚፎካከር ቡድን ውስጥ የሚገኝ ተጫዋቾች በየትኛውም አጋጣሚ የመሰለፍ እድሉን ሲያገኙ በሚጠበቅባቸው ደረጃ በማገልገል ቡድኑን በተፎካካሪነት የማስቀጠል ድርሻቸውን የመወጣት ግዴታም እንዳለባቸው እንዲሁ።
ምንም እንኳን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አሰልጣኙ የደጋፊውን ድርጊት ቢኮንኑም ደጋፊዎችም የቡድናቸው ተጫዋቾች ጥሩ ቀንን ማሳለፍ ባልቻሉባቸው ጨዋታዎችም ቢሆን ተጫዋቾቻቸውን በማበረታት ለተሻለ ውጤት ማትጋት ይገባቸዋል።
👉በዓይናለም ኃይለ ጥገኛ የሆነው የወልዋሎ ደካማው የኋላ ክፍል
በዚህ ሳምንት አዝናኝ የነበረው እና ስድስት ግቦች የታዩበት የወልዋሎ እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ላይ በርካታ ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች ቢኖሩም የባለሜዳው ደካማ የመከላከል አደረጃጀት እና የጊንያዊው ግብ ጠባቂ ደካማ ውሳኔዎች ትኩረት ሳቢ ነበሩ።
በመጀመርያው አጋማሽ በአንፃራዊነት ጥሩ የነበረው የቡድኑ የተከላካይ ክፍል በሁለተኛው አጋማሽ አምበሉ ዓይናለም ኃይለን በጉዳት ካጣ በኃላ ግርማ ሞገሱ ተገፎ በተጋጣሚ አጥቂዎች ሲቸገር ተስተውሏል። በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ግቦች ያስቆጠረው ይህ የተከላካይ ክፍል በአማካይ ክፍሉ በቂ ሽፋን አለማግኘቱ የቡድኑን የመከላከል አደረጃጀት ክፍተቶች ጉልህ እንዲሆኑ አስችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ በጨዋታው ደካማ እንቅስቃሴ ያሳየው ዓብዱልዓዚዝ ኬይታ የተከላካይ ክፍሉ ከኋላ ሆኖ መምራት ባለመቻሉ ቡድኑ ለተጋጣሚ ፈጣን አጥቂዎች ሲሳይ ሆኖ አምሽቷል።
👉 አዩብ በቀታና ስሜታዊው የደስታ አገላለጽ
ሀዲያ ሆሳዕና ከስድስት ሳምንት የዘለቀ ድል አልባ ጉዞ መልስ ወደ ድል በተመለሱበት የ15ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ለሀዲያ ሆሳዕና ብቸኛዋን ግብ አዩብ በቀታ በግሩም ሁኔታ ከቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ የግቧ ባለቤትና ዐምና በከፍተኛ ሊግ ለቡድን ጥቂት የማይባሉ ግቦችን ያስቆጠረው ተጫዋቹ በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ግቡን ያስቆጠረው አዩብ በቀታ ስሜቱን በዕንባ ገልጿል።
ባለፈው ሳምንትም በተመሳሳይ ከቅጣት ምት በረከት ሳሙኤል ማስቆጠሩን ተከትሎ በፕሪምየር ሊጉ የግብ ማስቆጠር ደመነፍስ ያላቸው የመሐል ተከለካዮች እጥረት ባለበት በዚህ ወቅት ጎሎች ሲያስቆጥሩ መመልከት መጀመራችን ግቦች ከአጥቂዎች ብቻ በሚጠበቅበት ሊግ ለክለቦች ሌላም መንገድ ስለመኖሩ የሚጠቅም ይሆናል ተብሎ ይገመታል።
© ሶከር ኢትዮጵያ