የፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – የአሰልጣኞች ትኩረት

የሊጉ 15ኛ ሳምንት ላይ የተከሰቱ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዋና ዋና አስተያየቶች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።

👉 የካሳዬ እና የተጫዋቾቹ ጉዳይ

ከአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እስከ 10ኛው ሳምንት ድረስ በነበሩት ወቅቶች ከፍተኛ ተስፋ ሰንቆ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ልብ በአሰልጣኙ ሀሳብ ዙርያ በሒደት በሁለት የተለያዩ ፅንፎች በመከፈል ከሀሳብ ፍጭት እስከ ተቃውሞ የዘለቁ ጫናዎች በተጫዋቾች እና በአሰልጣኝ ቡድን አባላት ላይ ማንዣበብ መጀመራቸው ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የተመለከትነው ገሀድ ሀቅ ነበር።

ከሰሞኑም በተጫዋቾች ላይ በተፈጠሩ ጫናዎች አጠቃላይ የአንደኛ ዙር ጉዞውን በማስመልከት በቡድኑ አባላት ፣ በተወከሉ ደጋፊዎች እና በክለቡ አመራሮች መካከል የሦስትዮሽ የውይይት መድረክ እና የእራት ግበዣ በደጋፊ ማኅበሩ አዘጋጅነት መካሄዱ የሚታወስ ነው። በመድረኩም በርካታ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በተጫዋቾች በኩል ከ15ኛው ሳምንት ጀምሮ ወደ ውጤት ለመመለስ እና ደጋፊውን ለመካስ ቃል ገብተው ነበር።

በ15ኛው ሳምንት መርሐ ግብር ወላይታ ድቻን ከመመራት ተነስተው 3-1 ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ በተለይ ከአቻነቷ ግብ በኃላ ከተቆጠሩት ሁለት ግቦች በኃላ የቡድኑ አባላት ወደ አሰልጣኛቸው በማምራት አሰልጣኙ በተጫዋችነት ዘመን ይለብሰው የነበረው 15 ቁጥር መለያን ይዘው ደስታቸውን የገለፁበት መንገድ የተለየ ነበር።

ከፍተኛ ጫና ውስጥ ለነበሩት አሰልጣኛቸው የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ያላቸውን አጋርነት ያሳዩበት ይህ የደስታ አገላለፅ ለአሰልጣኙ ትልቅ የልብ ልብ የሚሰጥ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

👉ተጫዋቾቻቸውን የሚከላከሉት ሰርዳን ዝቪጅኖቨ

በክረምቱ ፈረሰኞቹን የተረከቡት ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቮጅኖቨ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት ወቅት አንስቶ በሚሰጡት የድህረ ጨዋታ አስተያየቶች ላይ ተጫዋቾቻቸውን ከየትኛውም ውጪያዊ የሆነ ግፊት ለመጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት አስገራሚ ነው።

በዚህኛውም የ15ኛ ሳምንት ጨዋታ ከአዳማ ከተማ ጋር በሜዳቸው 0-0 በተለያዩበት ጨዋታ ላይ አንዳንድ የቡድኑ ተጫዋቾች ባሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ ከተወሰኑ የቡድኑ ደጋፊዎች ተቃውሞን ቢያስተናግዱም አሰልጣኙ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ይህን ድርጊት ኮንነዋል።

“በእርግጥ አሁንም መሪ ነን፤ ነገር ግን ለአንዳንድ በተጨዋቾች ላይ ለሚጮሁ ደጋፊዎች መናገር የምፈልገው ነገር አለ። መጮህ ካለባቸውም እኔ ላይ እንዲጮሁ ነው፤ ተጫዋቾቹን ይተዋቸው። ምክንያቱም ያለፉትን ስድስት ወራት ጠንክረው ሲሰሩ ቆይተዋል። ደግሞም ላለፉት ሁለት የውድድር ዓመታትም በውድድሩ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉ መሪ አልነበረም። ስለዚህ ደጋፊዎች ትዕግስተኛ እንዲሆኑ እጠይቃለው። ከፋሲል ከነማ በሁለት ከመቐለ ደግሞ በሦስት ነጥቦች በልጠን አሁንም እየመራን ነው። አሁንም ቻምፒዮን የመሆን ሰፊ ዕድሉ አለን። አንዳንድ ደጋፊዎች ለምን በተጫዋቾች ላይ እንደሚጮሁ አይገባኝም። መጮህ ካለባቸውም እኔ ላይ ይጩሁ።” ሲሉ ተደምጠዋል።

መሰል አስተያየቶች በምዕራባዊያን አሰልጣኞች ሲሰጡ ማድመጥ የተለመደ ነገር ቢሆንም ሀገር በቀል አሰልጣኞች ቡድናቸው ውጤት በማያስመዘግብበት ወቅት በተጫዋቾች ላይ ጣት መቀስር እና ማሳበብ የተለመደ እንደመሆኑ አሁን አሁን መሰል ተጫዋቾቻቸውን የሚከላከሉ ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞችም ብቅ እያሉ መጥተዋል።

👉 ተቃውሞ ያስተናገዱት አሰልጣኞች

በዚህኛው ሳምንት የሊጉ የመጀመሪያ ዙር የመዝጊያ መርሐ ግብሮች ውስጥ ሀዋሳ ስታዲየም ላይ የተደረጉት ሁለት ጨዋታዎች አሰልጣኞች ላይ ከፍ ያሉ ተቃውሞዎች የተስተናገዱባቸው ነበሩ። ከሰሞኑ ጫና የበረታባቸው አሰልጣኝ አዲሴ ካሳና የሰበታው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በዚህኛው ሳምንት ከፍተኛ ተቃውሞን አስተናግደዋል።

ዘንድሮ ዳግሞ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተለመለሱት ሰበታ ከተማዎች ከደካማ አጀማመራቸው በሒደት በመንቃት ወጣ ገባ የሆነ የውድድር አጋማሽ አሳልፈው በ18 ነጥብ 12ኛ ደረጃን በመያዝ የመጀመሪያውን ዙር አጠናቀዋል።

ቡድኑ በሲዳማ ቡና 1-0 በተሸነፉበት ጨዋታ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ወደ ሀዋሳ ያቀኑ የተወሰኑ የክለቡ ደጋፊዎች የቀድሞ አሰልጣቸውን ክፍሌ ቦልተና ስም እየጠሩ ተቃውሞ ከማሰማት በዘለለ አሰልጣኙ ውበቱ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ወዳረፉበት ሆቲል በሚያመሩበት ወቅት በተመሳሳይ እሳቸው ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩም አልታጡም።

ከሊጉ ባህርይ እና በሰንጠረዡ ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ሁሉም ቡድኖች በሚባል ደረጃ ከታችኛው ሊግ ያደጉም ሆኖ እንደነገሩ በሊጉ የከረሙ ክለቦች ቢሆኑም ቡድናቸው ከሰንጠረዡ ወገብ በላይ እንዲገኝ የመፈለጋቸው ነገር እየተለመደ መምጣቱ ከተወሰኑ ጥቂት ቡድኖች ውጭ ሁሉም የሚታዩበት መነፅር እየተመሳሰለ መጥቷል።

ምንም እንኳን ከፍተኛ ሊግ ላይ ከነበረው ሰበታ ከተማ አንፃር በሊጉ የካበተ ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች በጅምላ ቢተኩም አሰልጣኙ የሚፈልጉትን አጨዋወት በበቂ ሁኔታ ለማስረፅና ተፈላጊውን የቡድን ውህደት ለማምጣት ጊዜው ገና መሆኑን ቡድኑ በአማራጭነት ባስያዘው ሜዳ ጨዋታዎችን እያደረገ ከመሆኑ አንፃር ለእግርኳሳዊ ተቃውሞዎች ጊዜው ገና ቢመስልም አሰልጣኙ ላይ ጫናዎች እየታዩ ይገኛል።

ሌላኛው በአጨዋወት መንገድ እና በተጫዋቾች አጠቃቀም ወትሮውን ተቃውሞ የማያጣቸው አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝነት መንበራቸው እየተናጠ ይመስላል። በኃላፊነት የመቆየታቸው ነገር አጠራጥሮ የሰነበቱት አሰልጣኙ በሜዳቸው በፋሲል ከነማ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ግቦችን ከማስተናገዳቸው ጋር ተዳሞሮ በክለቡ ደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲሰነዘርባቸው የተደመጠ ሲሆን በተጨማሪም የፕላስቲክ ውሃ መያዣዎችም ሲወረወሩባቸው ተስተውሏል፤ በሀዋሳ ከተማ ሁለተኛ አመታቸውን የያዙት አሰልጣኙ ቡድናቸው ከኋላ ተነስቶ ግቦችን በማስቆጠር ባሸነፈበት ጨዋታ ከሶስተኛዋ ግብ መቆጠር በኃላ ደስታቸውን በዕንባ የገለፁበት መንገድ እጅግ ልብ የሚነካ ክስተት ነበር።

👉 ወደ ሁለት የሚከፈለው ወላይታ ድቻ ጉዳይ

በ15ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን በኢትዮጵያ ቡና 3-1 በተሸነፈበት ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ለመመስረት የሚያደርጉትን ጥረት ለማክሸፍ በቁጥር በርከት ብለው ወደ ተጋጣሚ ክልል በሚገቡበት ወቅት ቡድኑ በግልፅ ለሁለት ሲከፈል ይስተዋላል።

በተቃራኒ ሜዳ ጫና ለመፍጠር የሚሄዱት ስድስት ተጫዋቾች ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል ተጠግተው ቅብብሎችን ለማቋረጥ ሲሞክሩ በተቃራኒው ወደ ዝርግነት የቀረበው የተከላካይ መስመር ደግሞ ወደ ኃላ ተነጥሎ ሲቀር እና በመሀል ለሁለት በተሰነጠቀው የቡድኑ ክፍል መሀል እጅግ ሰፊ ክፍተት ሲፈጥር ይስተዋል ነበር።

ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናዎች ይህን ሰፊ ክፍተት ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት አለመኖሩ ነበር። ይህ ክስተት በሀገራችን እየተለመደ ከመምጣቱ የተነሳ ቸል የተባለ ቢመስልም ከፊት ያሉት ጫና ሲፈጥሩ የተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾች በየመጫወቻ ቦታቸው ወደ ፊት ተጠግተው በሜዳው ቁመት ጠበብ ያለ ቅርፅ በመያዝ መልሰው የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ሲገባቸው በተደራጀ መልኩ ክፍተቶችን አንብበው ለመጠቀም የሚሞክሩ ቡድኖች በብዛት አለመኖራቸው የቡድኖቹ ችግር ተደፋፍኖ መታለፉን ቀጥሏል።

👉 ዐበይት አስተያቶች

የአዳማ ከተማው ምክትል አሰልጣኝ ደጉ ዶባሞ ተጫዋቾች መልቀቂያ ማስገባት ቡድኑን ላይ በቀጣይ ሊፈጠር ስለሚችለው ጫና

“በእርግጥ በተወሰነ መልኩ ተፅዕኖ አለው። ከበላይ አካሎች ጋር ተነጋግረው ያለውን ችግር ይፈታሉ ብዬ አስባለው። እንደ አጋጣሚም ሆኖ የቡድኑ የበላይ አመራሮች በሙሉ ዛሬ ከቡድኑ ጋር አብረው ይገኛሉ። በእርግጠኝነት ሁለተኛው ዙር ከመግባታቸው በፊት ያለውን ችግር ለመቅረፍ ቃል ገብተውልናል።”

– የወልቂጤው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በወልዋሎው ጨዋታ ግቦች ከተቆጠረባቸው በኃላ ስላደረጉት ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ እና የጫላ ተፅዕኖ

ከእረፍት መልስ ሦስተኛ ግብ ከተቆጣጠረብን በኃላ ስለ ‘ሪስክ’ ነበር ስንነጋገር የነበረው። ሁለተኛው አጋማሽም በሦስት ተከላካይ ነው ለመጫወት የወስንነው። እንዲህ አይነት ውሳኔዎች ለመውሰን የምትገደድበት ወቅት አለ። የማጥቃት ባሕሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀይረን በማስገባት ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ አስበን ነበር የገባነው፤ ተሳክቶልንም ግቦች አስቆጥረናል። አሸንፈን የምንወጣባቸውን ዕድሎችም ፈጥረናል፤ ግን አልተጠቀምንባቸውም።

“ጫላ ለብሔራዊ ቡድንም የሚያስፈልግ ተጫዋች ነው። ምክንያቱም በማጥቃትም ተመልሶ በመከላከልም ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ጎል ላይ የመድረስ ችግር የለበትም ትንሽ ግብ የማስቆጠር ክፍተት ነበረበት እሱም ተፈቷል ፤ ዛሬም ቡድኑን ታድጓል። ትልቁ የማጥቅያ መሳርያችን ጫላ ነው ፤ ለጫላ ጎልቶ መውጣትም የቡድን ጓደኞች ሚና ከፍተኛ ነው።”

– የወላይታ ድቻው ጊዜያዊ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ግብ ካስቆጠረ በኃላ ኢትዮጵያ ቡና ስለተከተለው ያልጠቁት አጨዋወትና የመከላከል ስህተቶች

“በመጀመሪያው አጋማሽ ቡና በራሱ አጨዋወት ነበር የገባው ፤ ረጃጅም ኳሶችን ይጠቀማሉ ብለን አልገመትንም ነበር። እኛ ካገባን በኃላ ክፍት ቦታዎች ላይ ረጃጅም ኳሶችን መጠቀም ጀምረው ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ተነጋግረን የገባነውን ነገር በተለይ ከኃላ ያሉ ልጆች ሊፈፅሙልኝ አልቻሉም፤ በዚህም የእኛ ስህተቶች እነሱን አነሳስተዋል ብዬ አስባለሁ።”

– ሥዩም ከበደ በሀዋሳ ስለተሸነፉበት ጨዋታ

“አጀማመራችን የመጀመሪያው አስራ አምስት ሃያ ደቂቃ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ግብ በመሄድ የተሻልን ነበርን። በዚህም ወቅት ሁለት ጎሎችነን ማስቆጠር ችለናል፡፡ ከዚህም በላይ የምንራመድ ይመስል ነበር። ነገር ግን ሁለት ለዜሮ መምራታችን አሸናፊ እንደሆንን ያስመሰለን ነበር። የኛ የመከላከል መላላት ለተጋጣሚ ቡድን ጥንካሬ ሰቷቸዋል፡፡ በእያንዳንዱ ኳስ ትኩረት መስጠት እያለብን በኮንሰንትሬሽን ማጣት በራሳችን የፈጠርናቸው ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል፡፡ ሀዋሳዎች ሁለት ለዜሮ እየተመሩ ከኃላ ተነስተው ያደረጉት ጥረት ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ በራሳችንን ስህተቶች ዋጋ ከፍለናል። ከእረፍት በኃላ ጥሩ ለመጫወት ሞክረናል። በአጠቃላይ ለኛ ግን ጨዋታው ደስታን የፈጠረ አይደለም፡፡ ይህም ብዙ ነገር አበላሽቶብናል፡፡”

-ዘርዓይ ሙሉ ስለተጫዋቾችን እያፈራረቁ መጠቀምና ቡድኑን ስለማጠናከር

“እስካሁን ከነበረው ጥሩ ነው። ግን ያም ሆነ ይህ ቡድናችንን መጠናከር አለብን። ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናችን በመቀላቀል የተሻለ ተጠናክረን በሁለተኛው ዙር መቅረብ ይኖርብናል።”

-ፋሲል ተካልኝ ባህርዳር ከተማ ከረጅም ጊዜ በኃላ ግብ ሳያስተናግዱ ስለመውጣታቸው

“ግብ ሳይገባብን ጨዋታውን መጨረሳችን ለተከላካዮቼ የስነ ልቡና እገዛ ያደርጋል። እኔ ግን በተፈጥሮዬ አንድ ለዜሮ ከሚያሸንፍ ቡድን ሶስት ለሁለት የሚያሸንፍ ቡድን ቢኖረኝ ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ተመልካች ወደ ስታዲየም የሚመጣው ሊደሰት ነው እና ግቦች መግባት አለባቸው። ይህንን ስል ግን የመከላከሉ ላይ ያለንን ክፍተት ለመሸፈን እየሞከርኩ አይደለም።”

– ካሳዬ አራጌ ድቻ ላይ ስላስቆጠሯቸው ሦስቱ ግቦቹ ስለተቆጠሩበት መንገድና የተጫዋቾች ጫና

” ጎሎቹ የተቆጠሩት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ቀርበን በመጫወታችን ነው ፤ ተጋጣሚ ጎል አካባቢ ተጠግቶ መጫወት በጣም አስቸጋሪ ነው። አንደኛ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ክምችት አለ። ሁለተኛ በተጋጣሚ ጎል አካባቢ ቁጥርህን ለማብዛት አካሄድህም ወሳኝነት አለው። ሰዎችን ይዘን መሄድ ስላችልን የተገኙ ግቦች ናቸው ፤ ለምሳሌ ሁለተኛ ግብ ሲቆጠር ኳሱ የተነሳው ከአህመድ ነው። አህመድ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ነው ነገር ግን እንቅስቃሴ እሱን እዛ ድረስ ይዞት እንዲሄድ በመቻሉ ግቡ ተቆጥሯል።

” እንድናሸንፍ ይፈለጋል ፤ እንደአሰልጣኝ ደግሞ ለማሸነፍ እና ወደ ጎል እንድንሄድበት የምንፈልገው መንገድ አለ በጣም ጫና ውስጥ ሲገቡ ያንን ይረሱና ቶሎ ወደ ጎል መድረሳቸውን ብቻ ነው የሚያዩት ፤ ነፃ ሰው መኖሩ ፣ እንቅስቃሴ ከአዕምሯቸው ይወጣል ፤ በተወሰነ መልኩ ይህ ነገር አሁንም አለ። እንደአሰልጣኝ ተጫዋቾችን ከጫና መጠበቅ የእኛ ስራ ቢሆንም በተወሰነ መልኩ ውጤት እየመጣ ሲሄድ እየቀነሰ የሚመጣ ነገር ነው።”

– ውበቱ አባተ በሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ በሙቀት መጫወት ላለመዱት ቡድኖች ፈታኝ ስለመሆኑ

“ከባድ ጨዋታ ነው ፤ ከሜዳው አንፃር በብዙ ነገሮች ጠንካራ ጨዋታ ነው። አሪቲፊሻል ሜዳ ላይ ነበር። በተለይ ከዕረፍት በፊት ከባድ ፀሃይ ነበር እና ጎማ ላይ መጫወት በጣም ከባድ ነው። በተለይ ለኛ ሜዳውን ለማናውቀው በዛላይ ሲዳማን ነው የገጠምነው ለኛ ከባድ ነበር። ያም ሆኖ ግን ጥሩ ነበርን። ግን 1-0 ተሸንፈናል የምንችለውን ለማድረግ እስከ መጨረሻው ተፎካክረናል ያው ወጤቱን መቀበል ነው።”

– አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስለመጀመሪያ ድላቸው ቡድኑ እንዳይወርድ ለማድረግ ስለሚሰራ ሥራ

“የዙሩ የመጨረሻ ጨዋታ ስለሆነ አጥቅተን መጫወት አለብን። እንደ ጥሎ ማለፍ ባህሪ መጫወት አለብን ብለን ወደ ሜዳ መግባት ነበረብን እና ተጫዋቾቻችን እንዳያችሁት ብዙ ጉጉት አለ ጫና አለ አንደኛውን ዙር ላለመሸነፍ በሚል ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ አድርገን አሸነፈን ወጥተናል፡፡ ከምንም የበለጠ ሦስት ነጥብ ማግኘታችን ነው። በሁሉም ነገር ቡድኑ ሙሉ ነው። ባንልም ከውጤት አንፃር አስፈላጊ እና ወሳኝ ነጥብ ስላገኘን በተለይ በተለይ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ያደረጉት ተጋድሎ የደጋፊዎቻችን ድጋፍ ከአጠገባችን ካሉ ክለቦች እንዳንርቅ ነጥቡ አስፈላጊ ስለነበረ ተባብረን በጋራ አሳክተነዋል፡፡ እኔ ብቻዬን የትም ልደርስ አልችልም ደጋፊዎችም ከጎኔ ናቸው አመራሩም ተጫዋቹም ከጎኔ ናቸው በጥራት ደግሞ አስተካክለን ተጫዋች ካገኘን አምጥተን በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት ነው እቅዳችን፡፡ አሁን ግን ወራጅ አይለይም ለምን አንድ ስታሸንፍ ከላይ ትመጣለህ፡፡”

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ