የፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

በዚህ ሳምንት የተከናወኑ ጨዋታዎች ላይ የታዩ ሌሎች ጉዳዮችን እነሆ!
👉 በቸልተኝነት የተከሰተው የደጋፊዎች ግጭት

በበርካታ ስጋቶች ተሞልቶ ቢጀምርም ግምቶችን በማፋለስ ተስፋ ሰጪ የደጋፊዎች መቀራረቦችን ውጥረቶችን የማለዘብ ስራዎች ተሰርተው በእግርኳሱ የሰላም አየር መንፈስ የጀመረ ቢሆንም እዚህም እዚያም አንዳንድ መልካም ያልሆኑ ተግባራትን ስንመለከት ቆይተናል።

አንደኛ ዙር የመጨረሻ መርሐ ግብሩን በዚህኛው ሳምንት ያካሄደው ፕሪሚየር ሊጉ በ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር በሁለተኛው ዙር ሊጉ ሊገጥመው የሚችለውን ፈታና አስቀድመው መስራት ስለሚገባቸው የቅድመ ጥንቃቄ ስራ የጠቆመ ድርጊት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከስቷል።

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ለእንግዶቹ ወላይታ ድቻ ክለብ ደጋፊዎች የተመደበው በተለሞዶ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የሚገኙት ከማን አንሼ ባለ ወንበርና ያለ ወንበር በተሰኙት የመቀመጫ ክፍሎች ለወትሮው ቁጥራቸው መቀነስ አሳይቶ የነበሩትና በክለባቸው ወቅታዊ የውጤት መነቃቃት ከፍ ባለ ቁጥር ወደ ስታዲየም የመጡት የክለቡ ደጋፊዎች እንደ ወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች ሁሉ ትኬት ቆርጠው በቦታ እጦት መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል።

የሆነው ሆኖ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ለወትሮው በዳፍ ትራክ አካባቢ ወደ ከማን አንሼ በተጠጋው የመቀመጫ ክፍል ሰብሰብ ብለው እንደሚቀመጡ እየታወቀ በሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች መካከል የተወሰነ ክፍተት መተው እየተገባ የመሻሻል ተስፋዎችን ባሳየው የደጋፊዎች መስተጋብር መነሾነት በሚመስል መልኩ እጅግ ተቀራርበው በተቀመጡበት ሁኔታ ጨዋታው ሊካሄድ ችሏል።

በወላይታ ድቻዎች 1-0 የበላይነት የተጠናቀቀው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ መልስ በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሶስት ግቦችን አስቆጥረው ከመመራት ተነስተው ከተከታታይ 5 ጨዋታዎች በኃላ ወደ ድል የተመለሱበትን ውጤት ለማስመዝገብ በቅተዋል። ነገር ግን አቡበከር ናስር በ82ኛው ደቂቃ ካስቆጠራት ሦስተኛ ግብ መልስ ግን የተፈጠረው ነገር ግን እጅግ አሳዛኝ ነበር ፤ በተራ የቃላት ልውውጥ የጀመረው የደጋፊዎች አለመግባባት ወደ ድንጋይ ውርወራ አምርቶ የደጋፊዎች ግጭት ዳግም በሊጋችን በርዕሰ ዜናነት እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።

በድንጋይ ልውውጡ እንዲሁም የፀጥታ አስከባሪዎች ግጭቱን ለማርገብ ደጋፊዎች ከአካባቢው ለማራቅ የሄዱበት አግባብ በርካታ በተለይ የኢትዮጵያ ቡና ሴት ደጋፊዎች በተፈጠረው ግርግር ጉዳት አስተናግደው የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ተስተውሏል።

በደጋፊዎች መካከል የተሰሩት በጎ ጅምሮች መበረታታት ያለባቸው ቢሆንም መሰል ተስፉዎች ግን በአግባቡ መከወን ይገባቸው የነበሩ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን ግን ከመስራት ቸል እንዲባሉ ግን ሊያደርግ አይገባም ፤ በቀጣይ ውድድሩ ከፍ ወዳለ የጡዘት ደረጃ ላይ እየገሰገሰ እንደመሆኑ ከቡድናቸው ፍላጎት በተፃራሪ የሚመዘገቡ ውጤቶችን በፀጋ ለመቀበል የመቸገር አዝማሚያዎች ስለሚኖሩ ሁሉ አካላት በአትኩሮቶ ማጤን የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል።

👉ለመገናኛ ብዙሃን አባላት ያልተመቸው የስራ ከባቢ

በቂ የሆነ የሚድያ ትኩረት አይሰጠውም እየተባለ ይነሳ የነበረው የሀገራችን እግርኳስ በሂደት የተሻለ የሚድያ ሽፋን እያገኘ እየመጣ ይገኛል። በተለያዩ ፅንፍ በሚገኙ የአክራሪነት አስተሳሰቦች በታጠረውና ለስራ ምቹ ባልሆኑ ሁኔታዎች የታጀበው እግርኳሳችን ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ስራቸውን በነፃነት እንዳይከውኑ ተግዳሮት መሆኑን ቀጥሏል።

በ15ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ፋሲልን 3-2 በረታበት ጨዋታ ላይ በ4ኛ ዳኛነት የተመደቡት ፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የተለየ ክፍልና የመስሪያ ቦታ በሌለው የሀዋሳ ስታዲየም እንደወትሮው በሜዳው ቅጥር በሚገኘው የሽቦ አጥር ስር ሆነው ስራቸውን ለመስራት የመጡትን ከተለያዩ ተቋማት የተላኩ ባለሙያዎች በተለይም ካሜራ የያዙ ሙያተኞች ወደ ሜዳ እንዳይገቡ ለመከልከል የሞከሩበትና ለበርካታ ንትርኮች መነሻ የነበረው ክስተት ብዙ የሚያስብል አጋጣሚ ነበር።

በየትኛው ዓለም በሚገኙ የእግርኳስ ሜዳዎች የካሜራ ባለሙያዎች በሜዳው ጠርዝ የጨዋታውን እንቅስቃሴ በማያውክ መልኩ ተጠባባቂ ተጫዋቾች ከሚቀመጡት የሜዳ ክፍል ውጭ በሚገኙት በሚገኙት ሦስቱ የሜዳ ወገኖች ላይ በመሆን ስራቸውን ሲከዉኑ ይስተዋላል ። በተመሳሳይም በሀገራችን ደግሞ ለካሜራ ባለሙያዎች ምስል ለመቅረፅ የሚረዳ የተለየ የተዘጋጀ ቦታ ባለመኖሩ በመሮጫ ትራኮች ላይ ሆነው ምስል ሲቀርፁ ማስተዋል በሀዋሳና መሰል ሜዳዎችም እንግዳ የሆነ ነገር አይደለም።

የእሁድ ድርጊት ምንም እንኳን ያልተለመደ ቢሆንም በሌሎች የጨዋታ ቀናትም በተለያዩ ሜዳዎች በእለቱ ዳኞች ግላዊ ፍላጎት መነሻነት ፎቶ የሚያነሱ ባለሙያዎች ከሜዳ ሲወገዱ እንዲሁም ሲከለከሉ ይስተዋላል። የሜዳ ላይ የካሜራ ቦታዎችና ለባለሙያዎቹ ስለተከለከሉ ቦታዎችና መሰል የሜዳ ጉዳዮች ላይ በግልፅ የተቀመጠ የህግ ማዕቀፍ በሌበት ሁኔታ አንድ ወቅት ትኩረት ተነፍጎ ለነበረው እግርኳሳችን እድገት እየተጉ የሚገኙ ባለሙያዎችን ባልተገባ መልኩ ማዋከብና ባለተገባ መልኩ ማስተናገዱ ተገቢ አይደለም።

እርግጥ ነው በየጊዜው እየጨመረ ከሚመጣው የስፖርት መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አንፃር ይህንን በበቂ ሁኔታ ለማስተናገድ የሚችሉ ቦታዎችን ማዘጋጀት ላይና በአግባቡ ለየቶ ማስተናገድ ዙሪያ መሻሻል የሚገባቸው ስራዎች በበርካቶቹ የሀገራችን ስታዲየሞች ላይ መሰራት ይኖርባቸዋል።

👉ተምሳሌት የሆነው የዓዲግራት ስታዲየም

ላለፉት አንድ ዓመት ከግማሽ ያክል ጊዜያት በእድሳት ላይ የከረመው የአዲግራት ስታዲየም በአስገራሚ የግንባታ ጥራት በዚህኛው ሳምንት ይፋዊ ጨዋታዎችን ማስተናገድ ችሏል። ምንም እንኳን መጀመሪያ ከተቀመጠለት የግንባታ ጊዜ የተጓተተ የግንባታ አፈፃፀም ቢኖረውም አጠቃላይ የግንባታ ጥራቱ በአመርቂነቱ የሚጠቀስ የግንባታ ሂደትን አሳልፏል።

በክለቡ ደጋፊዎች ያላሰለሰ ጥረት ከዳር የደረሰው ስታዲየሙ ከድሮ ይዞታው የክቡር ትሪቡን መቀመጫ ፣ የመልበሻ ክፍል እና የመጫወቻ ሜዳ እድሳት ተደርጎበታል። በተለይ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ባደገበት 2010 የውድድር ዘመን እጅግ አቧራማ የነበረው የመጫወቻ ሜዳ አሁን ላይ ፍፁም የተለየ ገፅታን ተላብሷል። እጅግ በጥንቃቄ የተሰራ ስለመሆኑ የሚያስታውቀው የመጫወቻ ሳሩ ዘላቂ እንክብካቤ የሚደረግለት ከሆነ በሊጉ የሚገኙ የመጫወቻ ሜዳዎችን የጥራት ደረጃ ለማሳደግ በአብነት መጠቀስ የሚችል መሆኑ አያጠያይቅም።

ከመጫወቻ ሳር በላይ በስታዲየም ዙርያ የሚገኙት ግንባታዎች (Civil Works) እንደ ወሳኝ የግንባታ አፈፃፀም በሚቆጠርበት ሀገራችን የከተማ አስተዳደሩ ለሳሩ ጥራት የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ነው።

ዓብይ ኮሚቴው ከሊጉ ጅማሮ በፊት ባደረገው የሜዳ ግምገማ ወቅት በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት በርከት ያሉ ስታዲየሞች ወደ እድሳት እንዲገቡ ተደርጓል ፤ ከእነዚህም መካከል ከስሑል ሽረና ሰበታ ስታዲየሞች በስተቀር ሌሎች የማሻሻያ ስራዎቻቸውን አጠናቀው ዳግም ወደ አገልግሎት መመለሳቸው ይታወሳል።

ነገር ግን በቅርቡ ወደ ስራ ከተመለሱት ስታዲየሞች ላይ ጭምር አሁንም ስለመጫወቻ ሜዳቸው የጥራት ደረጃ ጥያቄዎች እየተነሳባቸው ይገኛል። የሜዳ ላይ ተጠቃሚነታቸው በፍጥነት ለማግኘት በማሰብ በጥድፊያ ግንባታቸው ተጠናቆ ገፅታቸው ሳር ስለለበሰ ብቻ ወደ ስራ ለገቡት ሜዳዎች የወልዋሎው ስታዲየም ምላሽ ያለው ይመስላል።

👉ያልተፈታው የኳስ አቀባዮች ጉዳይ እና ሀዲያ ሆሳዕና

በዚህኛው የውድድር ዘመን በርከት ባሉ ጨዋታዎች ላይ በተለይ በባለሜዳው ቡድን ባደለ ውጤት ጨዋታው ከቀጠለ የኳስ አቀባዮች ለተጋጣሚ ኳስን ለማቀበል ሲያንገራግሩና ሲያዘገዩ ስለመስተዋሉ በስፋት አንስተናል። መሰል ሁነቶች በተደጋጋሚ ሲከወኑ የሚስተዋል ቢሆንም በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ይህን መንገድ እንደ አማራጭ የሰአት ማካከኛ መንገድ ለመጠቀም እንደሚሞክሩ ቅሬታ ሲቀርብባቸው ይስተዋላል።

ቡድኑ ከዚህ ቀደም በሜዳው አቢዮ አርሳሞ ሲዳማ ቡናን በመርታት የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥብ ባሳካበት ጨዋታ በኳስ አቀባዮቹ ድርጊት የተማረሩት የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ከፍተኛ ምሬታቸውን ማሰማታቸው የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከወላይታ ድቻ እንዲሁም በዚህኛው ሳምንት ከጅማ አባ ጅፋር በተለዋጩ የሀዋሳ ስታዲየም ጨዋታዎች መሰል የሚያንገራገሩና የሚዝናኑ የኳስ አቀባዮች ጉዳይን በተደጋጋሚ እየተመለከትን እንገኛለን።

በዚህኛው የጅማ ጨዋታ በለተይ በሁለተኛው አጋማሽ በነበረው ኳስን የማዘግየት ሂደት የጅማ አባጅፋር የቡድን አባላት በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ተደምጧል።

👉 የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች መለያ

ከደሞዝ ክፍያና ተያያዥ የተጫዋቾች ይፋዊ የልቀቁኝ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ውጥረት ውስጥ የሚገኘው አዳማ ከተማ የቡድን አባላት የትጥቅ ጉዳይ ሌላው አንገብጋቢ ችግር ስለመሆኑ በዚህኛው ሳምንትም ተስተውሏል።

ለወትሮው በመጀመሪያ ተመራጭነት ከሚጠቀሙበት ቀይ መለያ በአማራጭነት የሚጠቀሙትን ነጭ መለያ በዚህ ሳምንት የተጠቀሙት አዳማዎች የተጫዋቾቹ የቁምጣና የመለያ ቁጥር ያልተጣጣሙ ፤ የቡድኑ ተጫዋቾች በልምምድ ወቅት ተጠባባቂ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች የሚጠቀሙ የተዘበራረቁ ትጥቆችና መሰል ጉዳይ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ከሚገኝ ክለብ የሚጠበቁ አይደሉም።

በተደጋጋሚ በአሰልጣኙና በተጫዋቾች ቅሬታ እየቀረበት የሚገኘው የክለብ ትጥቅ አቅርቦት ላለፉት 5 አመታት ግዢም አልተፈፀም ሲባል የተደመጠባቸው አጋጣሚዎችም አሉ። በመሆኑም ክለቡ በቀጣይ ሁለተኛ ዙር የትጥቅ ጉዳይን ፈቶ ለመቅረብ ሥራዎችን ከወዲሁ መጀመር ይኖርበታል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ