ሴቶች 2ኛ ዲቪዚዮን | በዛሬ ጨዋታዎች ለገጣፎ፣ አካዳሚ እና ጥሩነሽ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ስምንተኛ ሳምንት ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው ለገጣፎ፣ አካዳሚ እና ጥሩነሽ አሸናፊ ሆነዋል።

ለገጣፎ ከተማ ላይ ለገጣፎ ለገዳዲን ከልደታ ክ/ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በባለሜዳዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብዙም ያልተጠና፣ ሳቢ ያልሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ብንመለከትበትም በተሻለ ሁኔታ ልደታ ክፍለ ከተማዎች ኳሱን መስርተው እስከ ለገጣፎ የሜዳ ክፍል ድረስ ቢደርሱም ግልፅ የማግባት አጋጣሚ መፍጠር አለመቸላቸው የወሰዱትን ብልጫ በጎል እንዳይታጀብ አድርጎባቸውል። 

ባለሜዳዎቹ ለገጣፎዎች የተጠና የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባያስመለክቱንም በሚገኙ አጋጣሚዎች በተለይ በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ሞክረዋል። 45ኛው ደቂቃ የልደታዋ ግብጠባቂ አክሱማዊት ከግብ ክልሏ ውጭ ኳስ በእጇ በማራቋ ምክንያት የተሰጠውን ቅጣት ምት ለማዳን የተደረበችው ጤናዬ ዘርጋው በግንባሯ ገጭታ በራሷ ላይ ባስቆጠረችው ጎል ለገጣፎዎችን መሪ ማድረግ ችላለች።
ከእረፍት መልስ በሁለቱም በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ሲሆን ከተከላካዮች ጀርባ ቤተልሔም ስለሺ የተቀበለችውን ኳስ ወደ ፊት ገፍታ በመሄድ በጥሩ አጨራረስ የለገጣፎን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጋቸዋለች። ከደቂቃዎች በኃላም በተመሳሳይ የማጥቃት መንገድ ወደ ፊት በመሄድ ነፃ የጎል ዕድል የለገጣፎዋ አጥቂ ሰላም አየለ ብትፈጥርም ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

ጨዋታውን ተቆጣጥረው ቢጫወቱም ጎል ለማስቆጠር የተቸገሩት በአሰልጣኝ ዮናስ የሚመሩት ልደታዎች የተጫዋች እና የጨዋታ አቀራረብ ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረቶችን በማድረግ በ67ኛው ደቂቃ አጥቂዋ መሰታወት አመሎ አማካኝነት ከሽንፈት ያልታደገቻቸውን ጎል አስቆጥራለች።
ለገጣፎዎች በመከላከል ረገድ ልደታዎች መጀመርያ ከሚከተሉት ኳሱን ተቆጣጥሮ የጎል ዕድልን ለመፍጠር ያደርጉት ከነበረው አጨዋወት ወጥተው ረጃጅም ኳሶች በፍጥነት ወደ ጎል ለማድረስ ቢፈልጉም ምንም የተለየ ነገር መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታውቀ በለገጣፎ 2-1 በሆነ አሸነፊነት ተጠናቋል።

ዛሬ በተካሄዱ ሌሎች ጨዋታዎች ንፋስ ስልክ ላፍቶ ጥሩነሽ ዲባባ 2-1 ተሸንፏል። አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በተደረገው ጨዋታ ጤናዬ ለታሞ የእንግዶቹን ሁለቱንም ጎሎች ስታስቆጥር ብዙዓየሁ ፀጋዬ የንፋስ ስልክን አስቆጥራለች።

አካዳሚ ሜዳ ላይ ኢ/ወ/ስ አካዳሚ ፋሲል ከነማን 3-0 ማሸነፍ ችሏል። አርያት ኦዶንግ ሁለት፣ ንግስት በቀለ አንድ አስቆጥረዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ