የፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎችን በሚከተለው መልኩ አሰናድተናል።

👉 ጎሎች በቁጥራዊ መረጃ

– በአስራ አምስተኛው ሳምንት 19 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም ባለፈው ሳምንት ከተቆጠረው የጎል ብዛት በ2 ከፍ ያለ ነው።

– በዚህ ሳምንት አንድ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል። ከባለፈው ሳምንት በአንድ ዝቅ ማለትም ችሏል።

– በዚህ ሳምንት ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡ ቡድኖች ካላፈው ሳምንት በአንድ ዝቅ ብሎ 6 ሆኗል። ጅማ፣ ሰበታ፣ ሽረ፣ መቐለ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡ ቡድኖች ናቸው።

– በዚህ ሳምንት 18 ተጫዋቾች (በራስ ላይ ጨምሮ) ጎል በማስቆጠር ተሳትፈዋል። ጫላ ተሺታ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ቀዳሚውን ቦታ ሲይዝ ቀሪዎቹ 17 ተጫዋቾች አንድ አንድ ጎሎች አስቆጥረዋል።

– ከተቆጠሩት 19 ጎሎች መካከል 14 ጎሎች በአጥቂ (የመሐል እና የመስመር) ተጫዋቾች ሲቆጠሩ 3 ጎሎች በአማካይ ሥፍራ ተጫዋቾች፤ በተመሳሳይ 2 ጎሎች (በራስ ላይ ጨምሮ) በተከላካዮች ተቆጥረዋል።

– ከ19 ጎሎች መካከል 17 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ ሲቆጠሩ ሁለት በቀጥታ ቅጣት ምት ተቆጥረዋል።

– ከ19 ጎሎች መካከል 15 ጎሎች ሳጥን ውስጥ ተመትተው ሲቆጠሩ 4 ጎሎች ከሳጥን ውጪ ተመትተው ጎል ሆነዋል።

👉 ካርዶች በዚህ ሳምንት

– በዚህ ሳምንት 31 የማስጠንቀቂያ እና 1 የቀይ ካርዶች ተመዘዋልል። ይህም በቢጫ ካለፈው ሳምንት በ7፤ በቀይ ደግሞ በ3 ዝቅ ያለ ሆኖ ተመዝግቧል።

– ሀዋሳ ከተማ (0) ከፋሲል ከነማ (1) ያደረጉት ጨዋታ በአንድ የማስጠንቀቂያ ካርድ ዝቅተኛው ሆኖ ሲመዘገብ ሲዳማ ቡና (3) ከ ሰበታ ከተማ (3/1) ደግሞ በ5 የማስጠንቀቂያ እና አንድ ቀይ ካርድ ከፍተኛው ነው።

– ሀዋሳ ከተማ በዚህ ሳምንት ምንም የማስጠንቀቂያ ካርድ ያልተመለከተ ቡድን ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር በ4 ከፍተኛው ነው።

👉 በዚህ ሳምንት…

– በዚህ ሳምንት አራት ተጫዋቾች ዘንድሮ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ጎል አስቆጥረዋል። ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል)፣ ዳኛቸው አሰፋ (ድሬዳዋ ከተማ)፣ አዩብ በቀታ ( ሀዲያ ሆሳዕና) እና ራምኬል ሎክ (ወልዋሎ) ለመጀመርያ ጊዜ ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

👉 ተከታታይ ጎል አስቆጣሪነት 

ብሩክ በየነ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር ሲችል ይገዙ ቦጋለ እና ኢዙ አዙካ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር ችለዋል። 

👉 የሲዳማ ቡና Clean sheet እና ያለ አቻ ጉዞ

በተከላካይ ክፍሉ ላይ ድክምት ሲስተዋልበት የሰነበተው ሲዳማ ቡና በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ጎል ሳያስተናግድ ወጥቷል። ይህም ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን በአጠቃላይ ደግሞ ከጥር 25 ቀን 2011 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው። በወቅቱ መከላከያ (2-0) እና ደደቢትን (3-0) ካሸነፈ በኋላ ይህን ለማሳካት 31 ጨዋታዎችን ጠብቋል።

ሌላው የሲዳማ ቡና አስገራሚ እውነታ በአንደኛው ዙር ምንም ጨዋታ አቻ ያልወጣ ብቸኛው ቡድን መሆኑ ነው። በአጠቃላይ አቻ ከተለያየም 28 ጨዋታዎች ሆነውታል። 



© ሶከር ኢትዮጵያ

በሶከር ኢትዮጵያ የሚወጡትን ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎች በቀጥታም ሆነ በግብዓትነት ሲጠቀሙ ምንጭ ይጥቀሱ።