ለሦስት ተከታታይ ቀናት ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከጀርመኑ ባየር ሙኒክ ጋር በመተባበር ለፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።
የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ ባዘጋጀውና 20 የሚሆኑ የሴት እና የወንድ የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች በተካፈሉበት በዚህ ሥልጠና ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ስታዲየም በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር ሲሰጥ ቆይቶ ዛሬ ተጠናቋል። ይህ ስልጠና በቀጣይ ጊዜያትም እንደሚቀጥል ሰምተናል።
ስልጠናውን ከተካፈሉት መካከል የስልጠናውን ጠቀሜታ አስመልክቶ የሁለት አሰልጣኞችን ሀሳብ አካተናል።
“እግርኳሰ በአንድ ቀን የስልጠና ፕሮግራም የሚስተካከል ሳይሆን በእቅድ መሰራት እንዳለብን ጥሩ ጠቀሜታ ያገኘንበት ሥልጠና ነው” ፀጋዬ ኪ/ማርያም(ሀዲያ ሆሳዕና)
“እንደሚታወቀው ባየር ሙኒክ የ120 ዓመት ታሪክ ያለው አንጋፋ፣ ትልቅ እና ከፍተኛ ልምድ ያለው ክለብ ነው። እግርኳሱንም ወደ ሳይንስ በመቀየር ስኬታማ እየሆኑ መጥተዋል። ዓላማቸው ኢትዮጵያ ውስጥ አካዳሚ መክፈት እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአሰለጣጠን እቅድ አወጣጥ ለምሳሌ በውድድር ጊዜ የዕለት፣ የሳምንት፣ የወር አወጣጥ እና በእረፍት ወቅት አንድ ፕሮፌሽናል ክለብ ሊከተው የሚገባው የእቅድ አወጣጥ ጥሩ ትምህርት ሰጥተውናል። በሦስት ቀን ሁሉ ነገር ይጠናቀቃል ማለት ባይቻልም አንድ ቡድን የያዘውን የአጨዋወት ፍልስፍና ከተጋጣሚ ቡድን ጋር ሲጫወት ፍልስፍናውን ሳይለቅ እንዴት መቅረብ እንዳለበት። ከታች ጀምሮ በምን መልኩ መስራት እንደሚገባን በተጨማሪም ከተግባር በላይ በፕላን ላይ ብዙ ማተኮር እንደሚገባን ጥሩ ልምድ ያገኘንበት። እግርኳሰ በአንድ ቀን የስልጠና ፕሮግራም የሚስተካከል ሳይሆን በፕላን መሰራት እንዳለብን ጥሩ ጠቀሜታ ያገኘንበት ሥልጠና ነው”።
“በጨዋታ ወቅት በከፍተኛ ውጥረት እና በዝቅተኛ ውጥረት ወቅት እንዴት መጫወት እንዳለብን ተምረናል” ፍሬው ኃ/ገብርኤል (የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ)
” በሥልጠናው ሦስት ነገር አግኝቼበታለው፤ በመጀመርያ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ጠቀሜታው ትናንት የተማርከውን ነገር አሁንም ደግመህ የምታስታውስበት፣ አዳዲስ ነገሮች የምትማርበት ትምህርት ነው። በሁለተኛ ደረጃ የባየር ሙኒክ ክለብ ይዞልን የመጣው አዲስ ነገር ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት (ጎል ለማስቆጠር ክፍት ሜዳ ፍለጋ) ብዙ አይነት ቢሆንም ለታክቲክ ዲሲፕሊን እንዴት ተገዢ መሆን እንዳለብህ። የእኛ ሀገር ተጫዋቾች ጎል ለማስቆጠር ቦታ አጠቃቀም (ተቀባይ እና አቀባይ) ላይ የአቅም ውስንነት ያለ በመሆኑ ሦስተኛ ወገኖች እንዴት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባቸው፣ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በጨዋታ ወቅት በከፍተኛው ጥረት እና በዝቅተኛ ውጥረት ወቅት እንዴት መጫወት እንዳለብን ተምረናል። ከዚህ በተጨማሪ ስልጠናውን የተከታተልን አሰልጣኞች የሀሳብ ልውውጥ ያደረግንበት ጥሩ ስልጠና ነበር። ”
በተያያዘ ዜና ባየር ሙኒክ በዓመቱ የሚያዘጋጀውና የተለያዩ ሀገራት የሚሳተፉበት የታዳጊዎች ውድድር ላይ ኢትዮጵያ እንደምትሳተፍ ተገልጿል። ከ16 ዓመት በታች ዕድሜ ላይ በሚገኙ ታዳጊዎች መካከል በሚደረገው በዚህ ውድድር ላይ ለሚካፈለው ቡድን የሚሆኑ ተጫዋቾችን ለመምረጥ የሚከናወኑ ጨዋታዎች የካቲት 19 እና 20 በአዲስ አበበ ስታዲየም የሚደረጉ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ