አሁን በወልዲያ እየተጫወተ በሚገኘው አንጋፋው አጥቂ አንዱዓለም ንጉሴ እና በቀድሞ ክለቡ ወላይታ ድቻ መካከል የነበረው ውዝግብ ዙርያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔ አሳልፏል።
ተጫዋቹ ውሉ እስከ መስከረም 30 ቀን 2012 ድረስ የሚቆይ በመሆኑ የ3 ወራት ውል እየቀረው መሰናበቱን በመግለፅ ቅሬታውን ያቀረበ ሲሆን ክለቡ በአንፃሩ ብቃቱ እየወረደ በመሆኑና በስነምግባር ጥሰት ተደጋጋሚ ደብዳቤ ተፅፎለት እንዲቀጣ መደረጉን፤ ብቃቱን እንዲያሻሽል ሁለት ጊዜ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ይህ ካልሆነ እንደሚሰናበት መግለፃቸውን በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል። በመጨረሻም የ9 ወር ክፍያ መፈፀማቸውና የሦስቱ ወር ክፍያ እንደማይመለከታቸው ለፌዴሬሽኑ ማሳወቃቸውና ተጫዋቹም ክሱን ዘግይቶ አሁን ላይ መመስረቱ አግባብ ባለመሆነኑ ስንብቱ ህጋዊ መሆኑን ክለቡ ገልጿል።
ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ተጫዋቹ ክሱን ዘግይቶ ቢመሰርትም በይርጋ የሚታገድበት ጊዜ ላይ ባለመድረሱ የተጫዋቹን ስንብት ህጋዊነት ለማረጋገጥ ምርመራ ማድረጉን ገልጾ በምርመራው መሰረት ስንብቱ ተገቢ እንዳልሆነ ማብራርያ አቅርቧል።
በውሳኔው መሰረትም ክለቡ ውሳኔው በተላለፈ በ7 ቀናት ውስጥ በአንድ ጊዜ እንዲከፍል ሲወስን በተጠቀሰው ጊዜ ካልፈፀመ ከፌዴሬሽኑ አገልግሎት እንዲታገድ፤ በተጨማሪም ክፍያው ሳይፈፀም ከቀነ ገደቡ ካለፈ በየቀኑ የደሞዙ ሁለት በመቶ እየተሰላ እንዲከፈል ውሳኔ አስተላልፏል።
ሙሉ የውሳኔ ደብዳቤ ፡-
© ሶከር ኢትዮጵያ