ሀዲያ ሆሳዕና ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

ትናንት ሳሊፉ ፎፋናን በማስፈረም ወደ ዝውውር የገባው ሀዲያ ሆሳዕና አሁን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋችች አስፈርሟል። ቢኒያም ሲራጅ እና ተስፋዬ አለባቸውም አዲስ ፈራሚ ሆነዋል።

ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ወላይታ ድቻን ተቀላቅሎ መልካም ጊዜ በክለቡ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው ተስፋዬ አለባቸው በድቻ ለመቆየት በቃል ደረጃ በመስማማቱ ውሉን እንደሚያራዝም ቢጠበቅም ማረፊያው ሀዲያ ሆሳዕና ሆኗል። የቀድሞው የሰበታ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልዲያ የተከላካይ አማካይ በአንፃራዊነት የተሻለ የአማካይ ክፍል ባለው ሀዲያ ሆሳዕና ሰብሮ ለመግባት ፉክክር ይገጥመዋል።

ሌላው ለቡድኑ የፈረመው የተከላካይ መስመር ተጫዋች የሆነው አንጋፋው ቢንያም ሲራጅ ባለፈው ዓመት ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጋር በወልዋሎ ቆይታ ያደረገ ሲሆን በሐረር ቢራ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በአሰልጣኙ ሥር ተጫውቷል። ጅማ አባ ጅፋር ሌላው የተጫወተበት ክለብ ነው።

በሁለት ቀናት ውስጥ የሦስት ተጫዋቾች ዝውውር ያጠናቀቁት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በቀጣይም ተጨማሪ ዝውውሮች ይፈፅማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ