አለልኝ አዘነ ለአንድ ዓመት ሲታገድ ይግባኝ ጠይቋል

አለልኝ አዘነ ለአንድ ዓመት ከማንኛውም እግርኳስ እንዲታገድ ውሳኔ ሲወሰንበት ዛሬ ጠዋት ይግባኝ ጠይቋል።

ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በነበረው ጨዋታ በሀያ ስድስተኛው ደቂቃ ላይ ጥፋት ሰርቶ ቢጫ ካርድ ከተመለከተ በኋላ ከዋና ዳኛው ብሩክ የማነብርሀን በፈጠረው አታካራ በቀይ ካርድ የወጣው የሀዋሳ ከተማው አማካይ አለልኝ አዘነ በውድድሩ ፍትህ አካል ለአንድ ዓመት ከእግር ኳስ እንዲታገድ እና ሰላሳ ሺሕ ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

በጨዋታው በአንድ ተጫዋች ላይ ጥፋት ሰርቶ ቢጫ ካርድ ከተመለከተ በኋላ ዋና ዳኛው ብሩክ የማነብርሀንን በግንባር ለመምታት ሙከራ ያደረገው ይህ አማካይ በዛሬው ዕለት ወደ አዲስ አበባ አምርቶ ይግባኝ እንደጠየቀም ለማወቅ ተችሏል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት አርባምንጭ ከተማን ለቆ ወደ ሀይቆቹ ካመራ በኋላ በጥሩ ብቃት የቡድኑን የአማካይ ክፍል መምራት ጀምሮ የነበረው ግዙፉ አማካይ ቅጣቱ የሚፀና ከሆነ ለቀጣይ 12 ወራት ድረስ ከእግር ኳስ ይገለላል።

© ሶከር ኢትዮጵያ