ድሬዳዋ ከተማ ከሦስት ተጫዋቾች ጋር በስምምነት ተለያየ

ተከላካዩ ዘሪሁን አንሼቦ፣ አማካዩቹ አማኑኤል ተሾመ እና ዋለልኝ ገብሬ ከድሬዳዋ ጋር የስድስት ወራት የውል ኮንትራት እየቀራቸው በጋራ ስምምነት ተለያይተዋል፡፡

መስከረም ወር ላይ ደቡብ ፖሊስን ለቆ ወደ ቀድሞው ክለቡ የተመለሰው የመሐል ተከላካዩ ዘሪሁን አንሼቦ ለክለቡ ባስገባው የመልቀቂያ ጥያቄ መሠረት ክለቡም ደብዳቤውን ተቀብሎ ከተጫዋቹ ጋር በስምምነት ተለያይቷል፡፡

ሌላው ክለቡን የለቀቀው አማካዩ አማኑኤል ተሾመ ነው፡፡ የቀድሞው የአአ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ እና መከላከያ ተጫዋች በክለቡ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ለመግባት በተደጋጋሚ ሲቸገር የተመለከትነው ሲሆን ከአቋም ጋር በተገናኘም ክለቡ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤን ለተጫዋቹ ከዚህ ቀደም ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል። በዚህም በስምምነት ከክለቡ ተለያይቷል፡፡

ሦስተኛው ከክለቡ ጋር የተለያየው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዋለልኝ ገብሬ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ በመጫወት ያሳለፈው ይህ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ጅማ አባ ጅፋርን ለቆ ብርቱካናማዎቹን ቢቀላቀልም ግማሽ ዓመት ብቻ ቆይታ አድርጎ ከክለቡ ጋር ተለያይቷል፡፡

በሁለተኛው ዙር ራሱን ለማጠናከር በቃል ደረጃ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ስምምነት እየፈፀመ ያለው ድሬዳዋ ከተማ በጥቂት ቀናትም ውስጥ አዲስ አሰልጣኝ እንደሚሾም ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ