በሁለት ምድብ ተከፍሎ 5ኛ ሳምንት የደረሰው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሲቀጥል ተጠባቂውን ሸገር ደርቢ ጨምሮ የሌሎች ጨዋታዎች ተደርገዋል። እኛም እንዲህ አጠናቅረነዋል።
ምድብ ሀ
ድሬዳዋ በሚገኘው ሳቢያን ሜዳ ረፋድ 4:00 በተካሄደው የድሬደዋ ከተማ ከ ኢ/ወ/ስ/ አካዳሚ ጨዋታ በእንግዶቹ አካዳሚዎች 3-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በድል ተመልሰዋል።
ባለሜዳዎቹ ድሬዎች ሰላዲን አፈንዲ እና በወንደሰን ደረጄ ሁለት ተከታታይ ጎሎች እየመሩ ወደ እረፍት ቢያመሩም በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የመጡት አካዳሚዎች በፊሊሞን ዓለም የመጀመርያውን ጎል ሲያስቆጥሩ ብዙም ሳይቆይ በአካዳሚ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ዓምና መልካም የውድድር ዓመት ያሳለፈው ተስፈኛው አጥቂ ከድር ዓሊ የአቻነት እና የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአካዳሚዎች 3-2 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።
08:00 በአዲስ አበባ ስታድየም በተካሄደው ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስ አገናኝቶ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በኢትዮጵያ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በርከት ያሉ የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች በታደሙበት እና በሚያምር ህብረ ዝማሬ ጨዋታውን ባደመቁበት በዚህ ጨዋታ ላይ ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ነበሩ። የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች እና ግብጠባቂው የፈጠሩት ሰህተት ተከትሎ ፈጣኑ የመስመር አጥቂ በየነ ባንጃ በግሩም የአጨራረስ ብቃት በ13ኛው ደቂቃ ጎል ቡናማዎቹን ቀዳሚ አድርጓል።
አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ያልዘገዩት ፈረሰኞቹ ዳግማዊ ከመስመር ያሻገረለትን በጎሉ ፊት ለፊት አስራ ስድስት ከሀምሳ ጠርዝ ላይ ቆሞ የነበረው በዋናው ቡድን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው አብርሀም ጌታቸው ግሩም የአቻነት ጎል አስቆጥሮ ጨዋታውን ወደ ጥሩ ፉክክር ቀይሮታል። ራሱ አብርሀም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችልበት ዕድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ወደ እረፍት አምርተዋል።
ተመጣጣኝ ፉክክር ተደርጎበት የቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ በ55ኛው ደቂቃ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በየጨዋታዎቹ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ተገኝ ዘውዴ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ግሩም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ በስታድየም የነበሩ ደጋፊዎች አስደስቷል።
ጊዮርጊሶች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን በዳግማዊ አርዓያ እና ፀጋዬ አበራ አማካኝነት የጎል ዕድል መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙ ሲቀሩ በአንፃሩ ቡናማዎቹ በበየነ ባንጃ አማካኝነት ተጨማሪ የጎል አጋጣሚ ቢያገኙም ያመከኑት የሚያስቆጭ ነበር። በመጨረሻም በሁሉም መልኩ አዝናኙ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና 2-1 በሆነ አሸናፊት ተጠናቋል።
በሌሎች ጨዋታዎች መከላከያ በሜዳው ሀዋሳ ከተማን አስተናግዶ ከእረፍት መልስ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ፍሬ የሆነው ይበልጣል ወንድማገኘው ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ሲያሸንፍ አሰላ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከሲዳማ ቡና ያገናኘው ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ጎሎቹን ለጥሩነሽ ዳንኤል ደምሱ እና ወንድወሰን ደረጄ ሲያስቆጥሩ ሲዳማ ቡና ከሜዳው ውጭ አንድ ነጥብ ያገኝበትን ሁለቱንም ጎሎች አቤኔዘር አሰፋ አስቆጥሯል።
ምድብ ለ
ወደ ወልቂጤ የተጓዘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ይዞ ተመልሷል። ባለሜዳዎቹ ወልቂጤዎች አቤል ጌቱ ባስቆጠራት ጎል ቀዳሚ የነበሩ ቢሆኑም የወጣቶች አካዳሚ ፍሬ የሆነው እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ ዋና ቡድን እና በተስፋ ቡድኑ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ፀጋ ደርቤ ቡድኑ አቻ አድርጎ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ጎሉን አሸናፊ ተስፋዬ አስቆጥሮ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከወልቂጤ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል።
አዳማ ከተማ በሜዳው አሰላ ኅብረትን 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል። በየጫዋታዎቹ ጎል የሚያስቆጥረው ልማደኛው አጥቂ ፍራኦል ጫላ ሁለት ጎሎችን በስሙ ሲያስመዘግብ የቀሩትን ጎሎች ሙዓዝ ሙኅዲን፣ ቢንያም አይተን እና ዮናስ ጌታቸው አስቆጥረዋል።
ሌላው የሳምንቱ አስገራሚ ውጤት መድን ሜዳ ላይ ያልተጠበቀ ውጤት ተመዝግቧል። ሱሉሉታ ከተማ ኢትዮጵያ መድንን 3-2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። መድን ከሽንፈት ያልታደገች ጎል አሸብር ደረጄ እና መሐመድ ኑረዲን ሲያስቆጥሩ ሱሉልታ ከሜዳ ውጭ ወሳኝ ነጥብ እንዲያገኝ እና የውድድር ዓመቱ የመጀመርያውን ድል እንድያስመዘግብ ሦስቱን ጎሎች ኢሳይያስ ኃይሉ፣ ኢሳይያስ በላይ እና ወንዱ ደረጄ አስቆጥረዋል። በዚህ ምድብ ሀላባ ከተማ ላይ ሊካሄድ የነበረው የሀላባ ከተማ እና የአአ ከተማ ጨዋታ አአ ከተማዎች ባስገቡት ደብዳቤ መሠረት ጨዋታው ወደ ሌላ ቀን ተዟዙሯል።
የምድቡ ሌላኛው ጠንካራ ቡድን ፋሲል ከነማ የዚህ ሳምንት አራፊ ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ