የሴቶች ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ ተከናውነው ንግድ ባንክ እና ሀዋሳ ከተማ በሜዳቸው ሲያሸንፉ ጌዴኦ ዲላ፣ አዳማ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ከሜዳቸው ውጪ ድል አስመዝግበዋል።

ኤሌክትሪክ 0-1 አዳማ ከተማ

(ዳንኤል መስፍን)

10:00 በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው አሰልቺው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ በመጨረሻው ደቂቃ ትግስት ሀይሉ በራሷ ላይ ባስቆጠረችው ጎል በአዳማዎች 1-0 ጠባብ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል። ቡድኖቹ እንዳላቸው ወቅታዊ አቋም ጥሩ ፉክክር ይታይበታል ቢባልም በእንቅስቃሴም ደረጃ ሆነ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ በመፍጠርም ረገድ የረባ ነገር ሳንመለከትበት አሰልቺ ጨዋታ ሆኖ አልፏል።

ከአዳማ ከተማዎች የወረደ እንቅስቃሴ ይልቅ የተሻለ ነገር ለማሳየት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጥረት ቢያደርጉም እንቅስቃሴያቸው በጎል ያልታጀበ በመሆኑ በመጨረሻም ዋጋ ለመክፈል ተገደዋል። ተቀይራ በገባችው መሳይ ተመስገን ከቅጣት ምት የሞከረችው እና የግቡ አግዳሚ የመለሰባት መልካም አጋጣሚ ነበር። በአዳማ በኩል ምርቃት ፈለቀ ከምታደርገው የግል ጥረት ውጭ እንደ ቡድን የተደራጀ እንቅስቃሴ ባንመለከትም በመጨረሻው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ሰርካዲስ ጉታ ከግራ መስመር ያሻገረችውን በኤሌክትሪክ በኩል ሴናፍ እና ምርቃትን በጠንካራ መከላከል ስትከላከል የቆየችው ትግስት ኃይሉ ኳሱን በግንባሯ ለማራቅ ስትሞክር ወደ ራሷ ጎል አስቆጥራ አዳማዎች 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።

አርባምንጭ ከተማ 0-2 አዲስ አበባ ከተማ

(ፋሪስ ንጉሴ)

አርባምንጭ ላይ በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦችን ያገናኘው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ጎሎች ባይስተናገድበትም ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች ታይተዋል። 3ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባዋ አጥቂ ዓይናለም መኮንን ከርቀት የመታችው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ የተመለሰው የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። አርባምንጮች በበኩላቸው በተከታታይ 10ኛ፣ 12ኛ እና 20ኛው ደቂቃዎች ላይ በመዲና ጀማል፣ ስመወርቅ ድፋዴ እና ቱሪስት ለማ ሙከራዎችን አድርገዋል።

ቡዙም ማራኪ ያልነበረውና የጎል ሙከራ እምብዛም ባልታየበት ሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ሙከራ በ57ኛ ደቂቃ ላይ የአርባምንጭ የፊት አጥቂ በሰርካለም ባሳ አማካኝነት የተደረገ ሲሆን ከመስመር በኩል ቱሪስት ለማ አመቻችታ ያሻገረችውን ኳስ ሰርካለም ሳትጠቀም ቀርታለች። ከዚህ ሙከራ በኋላ አዲስ አበባዎችም በቤተልሄም ሰማኸኝ የሚያስቆጭ ሙከራ አድርገዋል።

በተወሰነ መልኩ መነቃቃት የፈጠሩት እንግዳዎቹ በድጋሚ በአንድ ሁለት ቅብብል የአርባምንጭ ተከላካዮችን አልፈው በግሩም ሁኔታ በቤተልሄም ሰማኸኝ አማካኝነት የመጀመርያውን ጎል አስቆጥረዋል።ጠከጎሉ መቆጠር በኋላ ሁለቱም ክለቧች የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን የጨዋታው መገባደጃ ላይ መስከረም ኢሳያስ በሰራችው ስህተት የፍፁም ቅጣት ለአዲስ አበባዎች የተሰጠ ሲሆን የተሰጠውን ከፍ/ቅ ምትም እታገኝ ሴፋ ወደ ጎል ቀይራለች። ጨዋታውም በአዲስ አበባ ከነማ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባንክ ሜዳ ላይ መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቐለ 70 እንደርታን አስተናግዶ 3-0 አሸንፏል። ረሒማ ዘርጋው፣ ሽታዬ ሲሳይ እና ገነሜ ወርቁ የድል ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

ወደ ድሬዳዋ ያመራው ጌዴኦ ዲላ ድሬዳዋን 2-1 አሸንፎ ተመልሷል። እፀገነት ግርማ ሁለቱንም የድል ጎሎች ስታስቆጥር አሰቤ ሙሶ የባለሜዳዎቹን ብቸኛ ጎል አስቆጥራለች።

በሰሞነኛ ግሩም አቋም ላይ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች በሜዳቸው መከላከያን 4-0 አሸንፈዋል። ነፃነት መና ሦስት ጎሎችን አስቆጥራ ሐት-ትሪክ ስትሰራ ምስር ኢብራሂም በቀድሞ ክለቧ ላይ ቀሪዋን ጎል አስቆጥራለች።

© ሶከር ኢትዮጵያ