የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያው ዙር መጠናቀቁን ተከትሎ ተሳታፊ ክለቦችን በተናጠል በመዳሰስ ላይ እንገኛለን። በዚህኛው ዳሰሳችንም የመጀመርያውን ዙር ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሦስት ነጥቦች ርቀው በሦስተኛነት ያጠናቀቁት ምዓም አናብስትን እንመለከታለን።
የመጀመርያ ዙር ጉዞ
ከቻምፒዮንስ ሊግ በጊዜ በመሰናበት እና በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በፋሲል ከነማ ተሸንፈው የውድድር ዘመኑን የጀመሩት ምዓም አናብስት በዝውውሩ ወቅት በቻምፒዮንነት ጉዟቸው ላይ ወሳኝ ሚና የተጫወቱት ሐይደር ሸረፋ እና ጋብሬል አሕመድን በመልቀቅ በአንፃሩ ኦኪኪ አፎላቢን ጨምሮ ጥቂት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ በመቀላቀል ነበር ዐምና ያሳኩትን ዋንጫ የማስከበር ከባድ ፈተና የጀመሩት።
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ብዙዎች ባስገረመ መልኩ ተከታታይ ዘጠኝ ጨዋታዎች አሸንፈው ከአስከፊው አጀማመር ወጥተው በሊጉ ዐናት ላይ በመቀመጥ ዙሩን ያጠናቀቁት ቻምፒዮኖቹ ዘንድሮ ግን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ውጤታማ ጊዜ ማሳለፍ አልቻሉም። ምንም እንኳ ከመሪው ጋር ያላቸው ልዩነት ሰፊ ባይሆንም በመጀመርያው ዙር ከሜዳቸው ውጪ ያስመዘገቧቸው ውጤቶች እና ከዋነኛ የዋንጫ ተፎካካሪዎቻቸው ጋር በተገናኙባቸው ጨዋታዎች የደረሰባቸው ሽንፈት ለጉዟቸው እንቅፋት እንደነበሩ ማንሳት ይቻላል። ቡድኑ ዋነኞቹ ከዋንጫ ተፎካካሪዎች ተብለው ከሚታሰቡ ክለቦች መካከል ሲዳማ ቡናን ከሜዳው ውጭ ቢያሸንፍም በቅዱስ ጊዮርጊስ (ውጪ) እና ፋሲል ከነማ (በሜዳው) ሽንፈት ገጥሞታል።
ካለፈው ዓመት በተላለፈ ቅጣት ምክንያት ሀዲያ ሆሳዕናን በሜዳቸው በዝግ ስታዲየም በማሸነፍ ዓመቱን የጀመሩት መቐለዎች በሁለተኛው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ሽንፈት አስተናግደው ከተመለሱ በኋላ በሜዳቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ደካማ እንቅስቃሴ አሳይተው ነጥብ ተጋርተው ቢወጡም ከሜዳቸው ውጭ ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ የደጋፊዎችን ተቃውሞ ጋብ ማድረጋቸው ይታወሳል። በአምስተኛ ሳምንት የቅርብ ተቃናቃኛቸው ወልዋሎን በማሸነፍ ደረጃቸው አሻሽለው ከሜዳቸው ውጭ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ቢገጥማቸውም በተከታታይ በሜዳቸው አዳማ ከተማን እና ሰበታ ከተማን፣ ከሜዳቸው ውጭ ደግሞ ወልቂጤ ከተማ አሸንፈው ሊጉን መምራት ጀምረው ነበር። ሆኖም ከአስረኛው ሳምንት በኋላ መንገራገጮች ያሳየው ቡድኑ በወላይታ ድቻ ሽንፈት አስተናግዶ ከተመለሰ በኋላ ስሑል ሽረ ተፈትኖ ድል ቢያደርግም በተከታታይ በጅማ አባ ጅፋር እና በፋሲል ከነማ ሽንፈት አስተናግዶ መሪነቱን አሳልፎ ሰጥቷል። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ሳምንታትም ሀዋሳ ከተማን በሰፊ ውጤት አሸንፎ ከሜዳው ውጭ በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት አስተናግዶ ዙሩን ደምድሟል።
የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር
በአማካይ ክፍል ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቹን ወደ ተቀናቃኝ ክለቦች ከመሸኘቱ ውጪ ከዐምናው ብዙም ያልተለወጠ የቡድን ስብስብ ያለው መቐለ 70 እንደርታ ዐምና በዚህ ሰዓት የውጤታማነት ጥግ ላይ ከነበረው ቡድኑ የዘንድሮው በብዙ ረገድ ደክሞ ቀርቧል ማለት ይቻላል። የመጨረሻ 7 ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ አንደኛውን ዙር በ35 ነጥብ አጠናቆ የነበረው ቡድኑ ዘንድሮ በ10 ነጥቦች አንሶ በ25 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። በጎል ረገድም ከዓምናው ዘንድሮ በ3 ያነሰ ጎሎች ሲያስቆጥር የተቆጠረበት ጎልም በ5 ከፍ ብሏል።
የቡድኑ አቀራረብ
በአብዛኛው የሁልጊዜ ምርጫቸው ከሆነው 4-4-2 የራቀ አደራደር ሲጠቀሙ የማይስተዋሉት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከጥቂት ጨዋታዎች በስተቀር በአመዛኙ ቀጥተኛ አጨዋወትን ነበር መርጠው ወደ ሜዳ የገቡት። ወደ መሐል ሜዳ የጠበበ የአማካይ ክፍል ቅርፅ ያለው እና ከመስመር የሚነሱ አማካዮች የማይጠቀመው መቐለ በተለይም የግዙፉ ናይጀሪያዊ አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ በክለቡ መኖር ለቀጥተኛ አጨዋወት ቅድሚያ እንዲሰጥ ያስገደደው ይመስላል። ሆኖም ቡድኑ ዮናስ ገረመው እና ያሬድ ከበደ የመሳሰሉ ለአጨዋወቱ ምቹ የሆኑ ተጫዋቾች መያዙ በብዙ ረገድ ተገማች እንዳይሆን አግዞታል። በተለይም ሁለቱ ተጫዋቾች ከጉዳት ነፃ ሆነው በተጣመሩባቸው ጨዋታዎች ቡድኑ ምንያህል ሰፊ የማጥቃት አማራጮች እንዳለው አሳይተዋል።
ጠንካራ ጎኖች
የባለፉት ሁለት ዓመታት የሊጉን የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋቾች በቡድናቸው ውስጥ የያዙት መቐለዎች በሊጉ አስፈሪ የማጥቃት ጥምረት ካላቸው ቡድኖች ይጠቀሳሉ። ከሌሎች የቡድኑ ክፍሎች አንፃር በጥራትም በአማራጭም የተሻለው ይህ የቡድኑ ክፍል በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች ከማይፈጥር የአማካይ ጥምረት ፊት ሆኖ የሚያሳየው ተጋድሎ እና ያለው የግብ መጠን ቡድኑ ምን ያህል አስፈሪ የማጥቃት ጥምረት እንዳለው ማሳያ ነው። ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ሥዩም ተስፋዬ እንደሚሰለፍበት የቀኝ የተከላካይ መስመር ሁሉ በግራ መስመርም ተመሳሳይ በማጥቃቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ከሆነ የቡድኑን የማጥቃት አማራጭ ሰፊ ያደርግለታል። በሊጉ በቀጥተኛ አጨዋወት ውጤታማነት በቅድሚያ የሚጠቀስ ጥሩ ጎን ያላቸው የገብረመድህን ኃይሌ መቐለዎች በአጨዋወቱ አተገባበር ላይ ያላቸው አቅም የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው።
ደካማ ጎኖች
መቐለዎች ከሌሎች የቡድናቸው ክፍሎች አንፃር ሲታይ ደካማ የአማካይ ክፍል አላቸው። በቁጥር ትንሽ ተጫዋቾች የያዘው ይህ የቡድኑ ክፍል ከቁጥሩ ማነስ በተጨማሪ የተጫዋቾቹ አቅም መመሳሰል እና አብዛኞቹ የመከላከል ባህሪ ያላቸው አማካዮች መሆን የአሰልጣኙ አማራጭ ጠባብ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ቡድኑ ደካማ የፈጠራ ምንጭ ያለው የአማካይ ስብስብ እንዲኖረው አድርጓል። ምንም እንኳ የአማካይ ክፍሉ የመቐለዎች ደካማ ጎን ተብሎ በዋነኝነት ቢጠቀስም ለስህተቶች ቅርብ የሆነው ተከላካይ ክፍሉም ሌላው የሚጠቀስ ደካማ ጎን ነው።
በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?
የሊጉን ክብር ለሁለተኛ ጊዜ ለማንሳት አቅደው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት ምዓም አናብስት በሁለተኛው ዙር በአማካይ ክፍል ላይ ያላቸው አናሳ የፈጠራ አቅም እና በመከላከል ላይ ያላቸው ደካማ አቅም ቀርፈው መቅረብ ግድ ይላቸዋል። የተጠቀሰው የአማካይ ክፍል ድክመት ለመቅረፍ የተከላካይ አማካዩ ሙሳ ዳኦ እና የአጥቂ አማካዩ አልሀሰን ካሉሻ ከወዲሁ ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉት መቐለዎች በሁለቱም ተጫዋቾች ፌርማ የተጠቀሱት ችግሮች ይቀርፋሉ ተብሎ ይታመናል።
ሙሳ ዳኦ ለተከላካዮች በቂ ሽፋን ሰጥቶ የሚጫወት ከሆነ የሳሳውን የቡድኑ ተከላካይ ክፍል ጥሩ ሽፋን ይሆናል ተብሎ ሲገመት ጥሩ የግብ ማግባት ክብረ ወሰን ያለው አልሀሰን ካሉሻም በጥሩ ጤንነት ቡድኑን ካገለገለ የቡድኑ የፈጠራ አቅም ከማጎለበት አልፎ በአማኑኤል እና ኦኪኪ ብቻ የተንጠለጠለውን የግብ ማግባት ድርሻ ይጋራል ተብሎ ይገመታል።
ከወዲሁ ሁለት ጥሩ ዝውውሮች የፈፀሙት መቐለዎች በቀጣይ ቀናትም እንደተገመተው ከተጫዋቾች ጋር በስምምነት የሚለያዩ ከሆነ ተጨማሪ ተጫዋቾች ያስፈርማሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ ክፍተቶቻቸው የሚድፍኑበት ዕድል ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።
የአንደኛ ዙር የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች
ያሬድ ከበደ – በቡድኑ ጥሩ በመንቀሳቀስ የሚጠቀሱ በርካታ ተጫዋቾች ቢገኙም በወጥነት ቡድኑን በማገልገል እና በአሰልጣኙ አጨዋወት ላይ ባለው ወሳኝነት ያሬድ ከበደ የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች ነው። የተጫዋቹ ብቃት ከጥሩ እና ወሳኝነት ያለው እንቅስቃሴ በዘለለ በቁጥሮች አለመደገፉ ሲታይ እንዴት የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ቢችልም ተጫዋቹ ባልተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ቡድኑ እንዴት እንደተቸገረ ሲታይ የተጫዋቹ ወሳኝነት ግልፅ ነው።
በቡድኑ ውስጥ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት እያገለገለ የሚገኘው የመስመር ተጫዋቹ ሥዩም ተስፋዬም ሌላው የሚጠቀስ ተጫዋች ነው።
ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች
አሸናፊ ሀፍቱ – ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ቡድኑ ተቀላቅሎ ዘንድሮ በቋሚነት ቡድኑን ማገልገል የጀመረው ሁለገቡ አሸናፊ ሀፍቱ ተስፋ የሚጣልባት ተጫዋች ነው። ምንም እንኳ ባለፈው ዓመት በአንደኛ ሊግ የደመቀው ክብሮም አፅብሀ፣ ፍፁም ተ/ማርያም እና ዐቢይ ተወልደ በቡድኑ ውስጥ ቢኖሩም ከተጠቀሱት ተጫዋቾች በተሻለ እንቅስቃሴ ያሳየው ዝምተኛው አሸናፊ ሀፍቱ ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች ነው። በትላልቅ ጨዋታዎች ሳይቀር አሰልጣኙን አሳምኖ በቋሚነት የተሰላፊነት ዕድል ያገኘ ሲሆን በመስመር ተከላካይነት፣ በመስመር ተጫዋችነት እና በፊት አጥቂነት መጫወት የሚችል ተጫዋች ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ