የ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ አራት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው ሶሎዳ ዓድዋ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ፌዴራል ፖሊስ ሲያሸንፉ ኮምቦልቻ ከደሴ ነጥብ ተጋርቷል።
ኦሜድላ ሜዳ ላይ ገላን ከተማን ያስተናገደው ፌዴራል ፖሊስ 1-0 አሸንፏል። በጨዋታው ኳስን ከራሱ ግብ በመመስረት ለመጫወት የሚጥረው ገላን ከተማ በባለሜዳው ጫና በመፍጠር እንዲሁም ገላን በተለዋዋጭ አጨዋወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉበት የመጀመሪያ አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ነበር። በ8ኛው ደቂቃ የፌዴራሉ ብሩክ ከግራ መስመር ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለለትን ኳስ በቀኝ አጥብቦ ከገባ በኋላ ከጠበበ አንግል ኳሱን አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ከግቡ አናት በላይ የሰደዳት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር።
በ14ኛው ደቂቃ የገላን የተከላካይ ስህተት ታክሎበት በቁመቱ ለግላጋው አብነት ደምሴ ያገኘውን አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም የፌዴራል ፖሊስን የአሸናፊነት ግብ ገና በጊዜ ማስቆጠር ችሏል። ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄድ የኦሜድላ ጥረት መዳከም የተነሳ በተሻለ ወደ ጨዋታው መግባት የቻሉት ገላኖች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የማጥቃት አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉበት አጋማሽ ነበር።
በጨዋታው በቶሎ ጎል ማስቆጠራቸውን ተከትሎ ገላኖች ኳስን ይዞ በመጫወት የጎል እድል ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም የጠራ የግብ እድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ፖሊሶች የግብ ክልላቸውን ከመጠበቅ በዘለለ በራሳቸው መገለጫ አጨዋወት እድሎችን ለመፍጠር ሲተጉ በአንፃራዊነት ገላኖች የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደ ፊት ተጭነው ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በሒደት ተቀዛቅዘዋል።
በ49ኛው ደቂቃ የገላኑ ብሩክ እንዳለ ለዳዊት ተፈራ ያቀበለውን ኳስ ዳዊት ከሳጥኑ ውጭ በመምታት እጅጉን ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር። እንዲሁም ብሩክ እንዳለ በ57ኛው ደቂቃ ከኋላ መስመር የተሻገረውን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በፌዴራሎች በኩልም በመልሶ ማጥቃት በ63ኛው ደቂቃ በነብዩ ሐመድ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገዋል።
ጨዋታው በፌዴራል ፖሊስ የ1ለ0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ፖሊሶች ያላቸውን ነጥብ 13 በማድረስ በግብ ክፍያ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በመበለጥ ዘጠነኛ ደረጃ ተቀምጠዋል።
በሌሎች ጨዋታዎች ኤሌክትሪክ በሜዳው ወልዲያን 2-1 ማሸነፍ ችሏል። ለእንግዶቹ አንጋፋው ተጫዋች አንዱዓለም ንጉሴ አስቆጥሮ መሪ መሆን ቢችሉም ሳዲቅ ተማም እና ሀብታሙ ረጋሳ አስቆጠረው ኤሌክትሪክ እንዲያሸንፍ ረድተዋል።
ዓድዋ ላይ ሶሎዳ ዓድዋ አክሱምን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ለዓድዋ መሐሪ አድሓኖም፣ ሙሉዓለም በየነ እና ኃይልሽ ፀጋዬ ጎሎቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቹች ናቸው።
ተጠባቂው የወሎ ኮምበልቻ እና የደሴ ጨዋታ ያለምንም ግብ ሲጠናቀቅ የ11ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ቀጣይ ሀሙስ ተደርገው የመጀመሪያ ዙር የሚጠናቀቅ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ