በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ የመጀመርያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው አርባምንጭ ከተማ መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል ሲያስመዝግብ ጌዴኦ ዲላ፣ ስልጤ ወራቤ እና ሺንሺቾም አሸንፈዋል።
አርባ ምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማን ከቂርቆስ ያገናኘው ጨዋታ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የምድብ ሐ መሪ መሆኑን ተከተሎ በርካታ ደጋፊዎች የተገኙበት ጨዋታ በርካታ የጎል ሙከራዎች የታዩበት ነበር። በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉት አርባምንጮች በ7ኛው እና 16ኛው ላይ ደቂቃ በአቦነህ ገነቱ የርቀት ሙከራዎች፣ በኤደም ኮድዞ በ11ኛው ደቂቃ ላይ በግንባሩ ገጭቶ ወደውጭ የወጣበት እንዲሁም በ22ኛ ደቂቃ ወርቅይታደስ ከርቀት ሞክሮ በተከላካዮች የተመለሰበት እና አሸናፊ ኤሊያስ ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በግብ ጠባቂው የተመለሰበት የመጀመርያው አጋማሽ የሚያስቁጩ ሙከራዎች ነበሩ። በአንፃሩ እንግዶቹ ተጠቃሽ ሙከራ በዚህ አጋማሽ ማድረግ ሳይችሉ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታው ላይ በጥሩ የኳስ ቅብብልና በፍጥነት ላይ ያተኮረ አጨዋት ይዘው ወደ ሜዳ የገቡት ባለሜዳዎቹ ግብ ለማስቆጠር የተለያዩ ጫናዎችን በመፍጠር በተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በ60ኛ ደቂቃ ላይ ኤደም ወደ ጎል የመታውን ኳስ ተከላካዮች ሲመልሱበት የተመለሰውን ኳስ አብነት በቀላሉ ወደ ጎል ቀይሮት አርባምንጭ ከነማን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላም አርባምንጭ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ቢሞክሩም የቂርቆስን ተከላካዮች ለማለፍ በመቸገራቸው ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በአርባምንጭ አሸናፊነት ተጠናቋል። (ሪፖርት በፋሪስ ንጉሴ)
ወራቤ ላይ ስልጤ ወራቤ በከድር ታረቀኝ ሁለት ግቦች ነጌሌ አርሲን 2-0 በማሸነፍ ደረጃውን ሲያሻሽል ከመድን ጋር ያለውን ተስተካካይ ጨዋታ በአሸናፊነት የሚያጠናቅቅ ከሆነም ነጥቡን ወደ መሪዎቹ የሚያስጠጋበት እድል ያመቻቻል።
ሺንሺቾ ላይ ሺንሺቾ ከመድን ያደረጉት ጨዋታ ረጅም ደቂቃ ያለ ግብ ቢዘልቅም የማታ ማታ በ90ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሪም ታምሩ ባለሜዳዎቹን ጮቤ ያስረገጠች ግብ አስቆጥሮ ሺንሺቶ 1-0 አሸንፏል።
ባቱ ላይ ባቱ ከተማ ከኮልፌ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል። ለኮልፌ ደሳለኝ ወርቁ የመሪነቱን፤ ለባለሜዳዎቹ አቤል ሀብታሙ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሯል።
ሀዋሳ ላይ የካን የገጠመው ደቡብ ፖሊስ 2-0 ማሸነፍ ችሏል። ምትኩ ማመጫ እና የኋላሸት ሰለሞን የፖሊስ ጎሎች ባለቤቶች ናቸው።
ዲላ ላይ ጌዲኦ ዲላ ከቡታጅራ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በተጨማሪ ደቂቃ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች በዲላ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በውዝግቦች ታጅቦ የተካሄደው ይህ ጨዋታ ቡታጅራ በበላይ ገዛኸኝ ግብ ቀዳሚ ቢሆንም በተጨማሪ ደቂቃ የቀድሞ የቡታጅራ አጥቂ የነበረው ክንዴ አቡቹ ለዲላዎች ሁለቱንም ግብ በማስቆጠር አሸናፊ መሆን ችለዋል። ጨዋታው በነበሩ ውዝግቦች ከአንድም ሁለት ጊዜ ለመቋረጥ ተገዶ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ