ከፍተኛ ሊግ ለ | ነቀምቴ ነጥብ ሲጥል መከላከያ፣ ኢኮሥኮ እና ጨንቻ አሸንፈዋል

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ሁሉም የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂዶ ነቀምቴ ነጥብ ጥሏል። ጋሞ ጨንቻ በአስደናቂ ጉዞው ሲቀጥል መከላከያ፣ ኢኮሥኮ፣ ሀላባ እና ቤንችማጂም አሸንፏል።


መከላከያ 1-0 ሻሸመኔ ከተማ


(ዳንኤል መስፍን)

በመከላከያ ሜዳ በተካሄደው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ ተጠባቂው የመከላከያ ከሻሸመኔ ከተማ ጨዋታ ወጣቱ አጥቂ መሐመድ አበራ ብቸኛ ጎል መከላከያ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፏል። ብዙም ማራኪ ያልነበረው የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በሻሸመኔ በኩል ከጨዋታው ነጥብ ለመውሰድ መከላከልን ቀዳሚ ምርጫቸው በማድረግ በመልሶ ማጥቃት የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር ቢያስቡም እቅዳቸው የተሳካ አልነበረም።

በመከላከያ በኩል የተከላካይ ቁጥራቸውን በሦስት አድርገው በመስመር በኩል ተደጋጋሚ ጥቃት ለመሰንዘር ቢሞክሩም ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ለመፍጠር ተቸግረዋል። ያም ቢሆን ፍሬው ሰለሞን ከርቀት የመታው እና ዳዊት ማሞ ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት የሞከሩትን ኳሶች በአንጋፋው ግብጠባቂ ሲሳይ ባንጫ አማካኝነት ዳነባቸው እንጂ ጥሩ ሙከራዎች ሆነው ያለፉ ናቸው። ጨዋታው ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ 44ኛው ደቂቃ ላይ ከዋናው ዳኛ እይታ ውጭ የሻሸመኔው አጥቂ ከማል አቶም ዘነበ ከበደን በመማታቱ በረዳት ዳኛው ጠቋሚነት በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። ሆኖም ይህን የዕለቱን ዳኛ ውሳኔ የሻሸመኔ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች በመቃወም በተፈጠረ ግርግር ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዷል።

ሻሸመኔዎች ቴክኒካል ክስ በማስያዝ በጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መከላከያ በሻሸመኔ የሜዳ ክፍል ላይ በማመዘን ጎል ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። 48ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ወጣቱ አጥቂ መሐመድ አበራ ከመስመር አሻግሮት ፍሬው ሰለሞን በግንባሩ የጨረፈው እና ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ታኮ የወጣው ሙከራ የጥረታቸው መጀመርያ ነበር። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ያደረጉት ቅያሪ ፍሬ አፍርቶ ተቀይሮ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴን በጥሩ ሁኔታ የለወጠው መሐመድ አበራ ከመስመር ወደ ሳጥን በመግባት የመታው ኳስ በሻሸመኔ ተከላካዮች ተጨርፎ በ63ኛው ደቂቃ የመከላከያ የመጀመርያ ጎል ሊቆጠር ችሏል።

የፊት መስመሩን ይመሩ የነበሩት ሦስቱ ተስፈኛ ወጣቶች መሐመድ አበራ፣ አቤል ነጋሽ እና ዊልያም ሰለሞን በቡድኑ ውስጥ በተሻለ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች በላይ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን ትልቁን ድርሻ ሲወስዱ ተመልክተናል። ሻሸመኔዎች በቁጥር ማነሳቸው የቡድኑ እንቅስቃሴ ላይ ተፅእኖ በማድረጉ ወደ መከላከያ የግብ ክልል ለመድረስ አልቻሉም ነበር። ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ በ83ኛው ደቂቃ ዊልያም ሰለሞን ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ቢፈጥርም የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሁለተኛ ጎል መሆን የሚችል ሲሆን የዳኛው የጨዋታ መጠናቀቂያ ፊሽካ ሲጠበቅ ሻሸመኔዎች አቻ መሆን የሚችሉበትን ዕድል ፀጋዬ ጎሳይ አግኝቶ ያልተጠቀመበት የሚያስቆጭ ነበር። በመጨረሻም ጨዋታው በመከላከያ 1–0 በሆነ ጠባብ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ኢኮሥኮ 2-1 ሀምበሪቾ

(ቴዎድሮስ ታከለ)

አሰልቺ በነበረው እና የሚቆራረጡ የቅብብል ሒደቶችን ባየንበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከባለሜዳው ኢኮስኮ ይልቅ በግብ ሙከራ እንግዳው ሀምበሪቾ የተሻለ ቢሆንም ያገኙትን ዕድል ለመጠቀም ጥረት በማድረጉ ረገድ የአሰልጣኝ በፀሎት ቡድን የተሻሉ ነበሩ፡፡ ተሻጋሪ ኳሶች ከሁለቱም ቀኝ እና ግራ መስመር በዝተው በታዩበት በዚህ አጋማሽ ገና 2ኛው ደቂቃ የኢኮስኮ ግብ ጠባቂ ገመቹ በቀለ የሰራውን ስህተት ተከትሎ አጥቂው ዳጌም ማርቆስ አግኝቷት ሳይጠቀምበት የቀረችሁ አስቆጪ ሙከራ የመጀመሪያዋ የጨዋታው ሙከራ ነበረች፡፡

የሀምበሪቾው አጥቂ ቢኒያም ጌታቸው በተደጋጋሚ ከተሻጋሪ ኳሶችም ሆነ በግል ጥረቱ ግቦችን ለማግኝት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ማድረግ ቢችሉም የአጨራረስ ክፍተት ቡድኑን ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ሆኖም በሀምበሪቾ በግብ ሙከራ ቢበለጡም በመልሶ ማጥቃት የተዋጣላቸው ኢኮስኮዎች ግብ አግኝተዋል፡፡ 33ኛው ደቂቃ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ያሬድ ዳሪዛ ግብ ጠባቂው ሄኖክ ወንድማገኝን አልፎ ማራኪ ግብ ከመረብ አሳርፎ ቡድኑን መሪ አድርጓል፡፡ ከግቡ በኃላ እጅግ የተዳከመ እንቅስቃሴን በሁለቱም በኩል መመልከት ብንችልም በግብ ሙከራ የተሻለ የነበረው ሀምበሪቾ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተዳከመ መልኩ ለዕይታ ማራኪ ያልነበረ ሲሆን አልፎ አልፎ ከሚታዩ ጥቂት ብልጭታዎች ውጪ ወጥነት ያለው የቡድኖቹን የማጥቂያ መንገድ ማየት አልቻልንም፡፡ ሆኖም በተጫዋቾች የግል አቅም ላይ የተመረኮዘው አጨዋወታቸው ግቦች እንዲቆጠሩ ምክንያት ነበሩ፡፡ የሀምበሪቾው አጥቂ ቢኒያም ጌታቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች እያደረገ መረጋጋት ባለመቻሉ ግብ ለማስቆጠር አልቻለም። የሀምበሪቾን የተከላካይ ክፍል ድክመት በመልሶ ማጥቃት በመጠቀም የተዋጣላቸው ኢኮስኮዎች 52ኛው ደቂቃ ያሬድ ደርዘ በሚገርም ብቃት የሰጠውን ኳስ አቤል ማርቆስ ብልጠቱን ተጠቅሞ ግብ አስቆጥሮ የባለሜዳውን የግብ መጠን ከፍ አድርጓል፡፡

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ሙሉ ኃይላቸውን ተጠቅመው ግብ ለማግኘት የታተሩት ቀይ ለባሾቹ በተለይ ወንድሜነህ ዘሪሁን ለውጠው ወደ ሜዳ ካስገቡ በኃላ በርካታ አጋጣሚ የፈጠሩ ሲሆን ግብ አስቆጥረውም ከጨዋታ ውጪ በሚል ከተሻረባቸው በኃላ ወንድሜነህ ዘሪሁን እጅግ ማራኪ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑ ከባዶ መሸነፍ አድርጎ ጨዋታው በኢኮሥኮ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ የኢኮስኮው አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ እና የሀምበሪቾው አቻቸው አለማየሁ አባይነህ በተላለፈባቸው ቅጣት የተነሳ ጨዋታውን አልመሩም፡፡

ጨንቻ ላይ ጋሞ ጨንቻ አሁንም በሜዳው የማይቀመስ መሆኑን ያሳየበትን የ6-0 ድል ካፋ ቡና ላይ አስመዝግቧል። በድሉ ሰለሞን ሦስት ጎሎች በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሲሰራ ታደለ በቀለ፣ ማቲዮስ ኤልያስ እና ዘላለም በየነ አንድ አንድ አስቆጥረዋል።

ሀላባ ላይ ሀላባ ከተማ ከ አዲስ አበባ ያደረጉት ጨዋታ በኃይሉ ወገኔ በ77ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ በርበሬዎቹ ሶስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል።

የምድቡ መሪ ወደ ነቀምቴ ከተማ ወደ ጅማ አምርቶ ከጅማ አባ ቡና ጋር ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተለያይቷል።

ሚዛን ላይ ሶዶ ከተማን የገጠመው ቤንች ማጂ በና 3-2 ማሸነፍ ችሏል። ኦኒ ኦጁሉ ሦስቱንም ጎሎች አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ በመስራት ለቤንች ማጂ ውጤታማነት ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ