ተስፋዬ በቀለ በመቐለ 70 እንደርታ ልምምድ እየሰራ ይገኛል

ባለፈው ዓመት መጨረሻ ከአዳማ ከተማ ጋር የተለያየው የመሐል ተከላካዩ ተስፋዬ በቀለ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ልምምድ ጀምሯል።

ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ቡና ፣ መከላከያ እና አዳማ ከተማ ጋር መጫወት የቻለው ይህ ተከላካይ በዛሬው ዕለት ከመቐለ ጋር ልምምድ የጀመረ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም ከክለቡ ጋር የሚያቆየው ውል የሚፈፅም ከሆነ የቡድኑን የተከላካዮች አማራጭ የሚያሰፋ ይሆናል።

በመጀመርያው ዙር እንደ ዐምናው ጠንካራ የተከላካይ ጥምረት መስራት ያልቻሉት ቻምፒዮኖቹ በሁለተኛው ዙር ጠንክሮ ለመቅረብ ሁለቱ ጋናውያን አልሀሰን ካሉሻ እና ሙሳ ዳኦን ወደ ስብስባቸው መቀላቀላቸው ይታወሳል።

ሌላ ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ዜና በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ጉዳት አስተናግደው የነበሩት ዮናስ ገረመው እና ያሬድ ከበደ ወደ ልምምድ ሲመለሱ አምበሉ ሚካኤል ደስታም በግሉ ቀላል ልምምድ ሰርቷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ