የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ክለቦች ዳሰሳ – ወልቂጤ ከተማ

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር የክለቦች ዳሰሳን በተናጠል መዳሰሳችንን ቀጥለን በዚህኛው ፅሁፋችን የመጀመሪያውን ዙር በ19 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ወልቂጤ ከተማን የአጋማሽ ጉዞ ተመልክተናል።


የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

በ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ ማድረግ የቻለው ወልቂጤ ከአሰልጣኝ ቅጥር ጀምሮ ድፍረት የሚጠይቅ ውሳኔ በማሳለፍ በፕሪምየር ሊጉ ልምድ የሌላቸው ደግአረግ ይግዛውን በመቅጠር ጉዞውን የጀመረ ሲሆን በሊጉ ከፍተኛ የመጫወት ልምድ ያላቸው በርካታ ተጫዋቾች፣ እድል ያላገኙ ተስፈኛ ወጣቶች እንዲሁም በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉ ተጫዋቾችን በማስፈረም በተጨማሪም አንጋፋው አዳነ ግርማን በተጫዋች/ምክትል አሰልጣኝነት ወደ ቡድኑ በመቀላቀል ነበር ወደ ውድድር የገቡት።

ቡድኑ ከውድድሩ መጀመር ቀናት በፊት ሊጉን በሚመራው ዐቢይ ኮሚቴ ሜዳው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ለማከናወን ብቁ መሆኑ ባለመቻሉ ውድድሮችን በአማራጭነት ያቀረበው ባቱ ከተማ የሚገኘው የሼር ኢትዮጵያ ስታዲየም ላይ አንድ ጨዋታ ካደረገ በኋላ በድጋሚ በአወዳዳሪው ትዕዛዝ የሜዳ ለውጥ አድርጎ በሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ ሁለት ተጨማሪ የሜዳው ጨዋታዎችን አከናውኖ ከስድስተኛው ሳምንት ጀምሮ ነበር በሜዳቸው መጫወት የቻለው።

በመጀመርያው ሳምንት የሊጉ ውጤታማ ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስን ባቱ ላይ ገጥሞ ያለ ጎል የተለያየው ቡድኑ በሁለተኛው ሳምንት ወደ አዳማ አምርቶ 1-0 ተሸንፎ በሦስተኛው ሳምንት ሆሳዕና ላይ ጠንካራው ፋሲልን 1-0 በመርታት በሦስቱ ሳምንታት የተለያዩ ውጤቶች አስመዝግቦ ውድድሩን ጀምሯል። ከዛ በኋላ በተደረጉ ጨዋታዎች ደካማ እንቅስቃሴ ያደረገው ክለቡ በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ እስከመቀመጥ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ከ10ኛው ሳምንት ጀምሮ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ደረጃውን በአንድ ጊዜ ከወገብ በላይ ማስቀመጥ ችሏል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ በሜዳው በሲዳማ ቡና ተሸንፎ ከሜዳው ውጪ ከቡና እና ወልዋሎ ጋር ነጥብ ተጋርቷል። በተለይም ከወልዋሎ ጋር በሁለት የግብ ልዩነት እየተመሩ አቻ የተለያዩበት ጨዋታ የቡድኑ የአዕምሮ ደረጃ የታየበት ነበር።

ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባሻገር ከሜዳ ውጪ ጉዳዮች ትኩረት ስቦ የቆየው ቡድኑ በመጀመርያው ዙር ሦስት የሜዳው ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ ከማድረጉ በተጨማሪ ከሲዳማ ቡና ጋር በተደረገው ጨዋታ በተከሰተው የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት የተላለፈበት ቅጣት እንዲሁም ጥያቄ ሲነሳበት የቆየው የመጫወቻ ሜዳው ብቁነት ጉዳይም በመጀመርያው ዙር የሚነሱ ጉዳዮች ነበሩ።

የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር

ቡድኑ ዓምና በከፍተኛ ሊግ እንደመወዳደሩ ከዘድሮው ጋር ንፅፅር ስስጥ ማስገባት አስቸጋሪ ነው።

የቡድኑ አቀራረብ

በከፍተኛ ሊግ ቡድኖች ሲሰሩ በቆዩት አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው የሚመራው ወልቂጤ ከተማ የአንደኛው ዙር አቀራረብ እንደየተጋጣሚዎቹ አቀራረብ ተለዋዋጭ እንደነበር ተስተውሏል። ቡድኑ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሚሰጥ ቡድን ከማስመልከቱ በተጨማሪ አሰልጣኙ በአውሥኮድ እና ኢኮሥኮ የሰሯቸው ቡድኖች የኳስ ቁጥጥር መለያቸው የነበረ መሆኑ በሊጉም ይህን ያስቀጥላሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ሆኖም በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች በአጨዋወቱ አመርቂ ውጤት ያላስመዘገበው ቡድኑ ከተጋጣሚው አንፃር አጨዋወቱን ለመቃኘት ሞክሯል። አሰልጣኙ በአመዛኙ ፈጣን ሽግግር እና ቀጥተኛ ኳሶች ላይ ያተኮሩ ሲሆን 4-3-3፣ 4-4-2 እና 3-5-2 የተጫዋቾች አደራደርን እያፈራረቁ ሲጠቀሙ ተስተውሏል።

ቡድኑ በተለይ በላይኛው የሜዳ ክፍል የያዛቸው ተጫዋቾች ፍጥነት እና ተክለ ሰውነት ለቀጥተኛ አጨዋወቱ ተመራጭነት አስተዋፅኦ ያደረጉ ሲሆን ቡድኑ ያስቆጠራቸው ጎሎችም የዚህ አቀራረብ መገለጫ ነበሩ። ከመስመር በተለይም ከአዳነ በላይነህ እና ጫላ ተሺታ የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች እንዲሁም ከተከላካይ በቀጥታ የሚጣሉ ኳሶች የቡድኑ ሁነኛ የማጥቃት መሳርያ ነበሩ።

በተጫዋቾች ምርጫ ረገድ ግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ የመጀመርያዎቹን ጨዋታዎች የተሰለፈው ሶሆሆ ሜንሳህ በሒደት በይድነቃቸው ኪዳኔ ሲተካ በተከላካይ ቦታ ላይ በጉዳት ምክንያት ወጥ ጥምረት መመልከት አልተቻለም። በመደበኝነት ከተጫወተው ዐወል መሐመድ ጋር ዳግም ንጉሴ እና ቶማስ ስምረቱ እየተፈራረቁ የተጫወቱ ሲሆን ዳግም ንጉሴ በጉዳት ምክንያት ይበልጣል ሽባባው ባልተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ላይ በቀኝ መስመር ተሰልፎ አገልግሏል። አቤኔዘር አቴ እና አዳነ በላይነህ በግራ መስመር እየተፈራረቁ መጫወት ችለዋል።

የቡድኑ የአማካይ ክፍል እንደሚመርጠው አቀራረብ ሲወሰን የሚስተዋል ሲሆን አልሳሪ፣ አዳነ ግርማ፣ ፍፁም ተፈሪ፣ ኤፍሬም ዘካርያሰ፣ በቃሉ ገነነ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ እና በረከት ጥጋቡን እንደመያዛቸው በየጨዋታው የተለያዩ ጥምረቶች ታይተዋል። በአጥቂ መስመርም ዓመቱ መጀመርያ ላይ ሲጠቀምበት የነበረው ጃኮ አራፋት የአጨዋወት ባህርይ ለቡድኑ የማጥቃት ቅርፅ ስልነት ሲሰጠው ያልታየ ሲሆን በሒደት ወደ መጀመርያ አሰላለፍ የተመለሰው አሕመድ ሁሴን ይበልጥ ሌላው ቀስ በቀስ እድል ካገኘው ሳዲቅ እና ከቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ጫላ ተሺታ ጋር ጥሩ መናበብ መፍጠርች ችሏል።

ጠንካራ ጎን

የአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ቡድን ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ የሚኖረው ጥንካሬ አስገራሚ ነው። አጠቃላይ ቡድኑ በአጋማሹ ይዞ ካጠናቀቀው 19 ነጥቦች ውስጥ 12 ከሜዳ ውጪ የተገኙ መሆናቸው (በመጀመርያዎቹ ሳምንታት በባቱ እና ሆሳዕና ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ጨምሮ) ከሜዳው ሲወጣ ያለውን ጥንካሬ የሚያሳዩ ናቸው። ከሜዳው ውጪ ለተጋጣሚ ተገማች ባልሆነ እና በተደራጀ ሁኔታ የሚቀርበው ወልቂጤ በጠንካራ መከላከል እና ቀጥተኛ አጨዋወት ባለሜዳዎችን ሲፈትን ይስተዋላል ።

በጨዋታ 0.7 ጎል ብቻ የሚያስተናግደው የተከላካይ ክፍሉን ጥንካሬ ማንሳት የግድ ነው። ዝቅተኛ ግብ በማስተናገድ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ ከአማካይ ክፍል የሚሰጠው ሽፋን እና የማጥቃት ተጫዋቾች ኳስ ከእግራቸው ስትወጣ መልሶ ለማግኘት ያላቸው ተነሳሽነት እንዲሁም የቡድኑን ተከላካዮች የተናጠል ጥንካሬ ለኋላ ክፍሉ ጥንካሬ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ደካማ ጎኖች

በራሳቸው ሜዳ (ወልቂጤ ላይ) ባደረጓቸው ጨዋቻዎች መሰብሰብ ከነበረባቸው 15 ነጥቦች ያሳኩት 6 ነጥብ ብቻ ነው። በጨዋታ ቀናት በሜዳም ሆነ ከዛ ከሜዳ ውጭ ያለው ጫና ተጫዋቾቹ በሜዳ ላይ የሚጠበቅባቸውን እንዳያበረክቱ እክል የፈጠረባቸው ይመስላል። በተለይ ግብ ከማስቆጠር ጉጉት የሚፈጠር የጥድፊያ እና ያልተጠና እንቅስቃሴ የተነሳ የሚባክኑት ንፁህ የጎል እድሎች ለዚህ እንደ ማሳያ የሚሆኑ ናቸው።

የጎል ማስቆጠር ችግር የቡድኑ ሌላው ደካማ ጎን ነው። በጨዋታ በአማካይ ከአንድ ጎል በታች የሚያስቆጥረው ቡድኑ እንደተከላካይ መስመሩ ጥንካሬ ባይሆን ኖሮ የውድድር ዘመኑ ጉዞው የከፋ በሆነ ነበር። በተለይ በሜዳው ሲጫወት በርካታ ኳሶችን የሚያመክነው የፊት መስመር ባለፉት ጨዋታዎች ላይ መሻሻል ቢያሳይም የአማራጭም ሆነ የስልነት ችግር በሰፊው ታይቶበታል።

ሚዛኑን ያልጠበቀው የቡድን ስብስብ ሌላው የቡድኑ የመጀመርያ ዙር ደካማ ጎን ነበር። ቡድኑ በርካታ ተጫዋቾች ቢኖሩትም በየሥፍራው የተመጣጠነ ስብስብ ነበራቸው ለማለት አያስደፍርም። በመስመር ተከላካይ ቦታ ላይ በቀኝ መስመር ይበልጣል ሽባባው ሲጎዳ በተፈጥሯዊ የቦታው ተጫዋች ለመተካት የተቸገረው ቡድኑ በአጥቂ እና የመስመር አጥቂ ስፍራ ላይም በቂ የተጫዋቾች አማራጭ አለመያዙ በመጀመርያ ዙር ታይቷል።

የአማካይ ስፍራ ላይ በየጨዋታዎቹ የሚታየው የመፈራረቅ ሁኔታ ለቡድኑ ውሕደት እክል ሲፈጥር ታይቷል። በአንፃራዊነት የተትረፈረፈ የተጫዋቾች አማራጭ ያለው ቦታው ለማፈራረቅ የተመቸ ቢሆንም በጋራ በርካታ ጨዋታ ከመሰለፍ በሚመጣ መግባባት በሚገባ የተደራጀ እንዳይሆን አድርጎታል።

በሁለተኛ ዙር ምን ይጠበቃል?

በተከፈተው የዝውውር መስኮት ተጫዋቸች ለማስፈረም እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ወልቂጤ በተከላካይ እና አጥቂ ስፍራ ላይ ያለውን የአማራጭ እጥረት መቅረፍ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ወልቂጤ ከተማ ይበልጥ ፈታኝ በሆነው ሁለተኛው ዙር የተጣለበት ቅጣት ከፀና የመጀመርያ 6 ተከታታይ ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ ለመጫወት ይገደዳል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው፣ ከአዳማ ከተማ ደግሞ በቅጣት ምክንያት በገለልተኛ ሜዳ፤ ቀጥሎም ከፋሲል እና ሰበታ ከሜዳው ውጪ እንዲሁም በድጋሚ በቅጣት ምክንያት ከወላይታ ድቻ በገለልተኛ ሜዳ በመጨረሻም ከስሑል ሽረ ከሜዳው ውጪ ይጫወታል። ከሰንጠረዡ ወገብ እስከ ግርጌ ድረስ ያለው የነጥቦች ልዩነት ጥቂት ብቻ መሆኑም ከነዚህ ስድስት ጨዋታዎች በርከት ያለ ነጥብ ይዞ መውጣት ግድ ያደርግበታል።

የጎል እድሎችን በመፍጠር ረገድ ጥሩ የሆነው ቡድኑ በሁለተኛው ዙር እድሎችን ወደ ግብነት መቀየር ላይ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል። በእርግጥ የፊት መስመሩ አሕመድ ሁሴን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ከተመለሰ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ላይ መሻሻል ያሳየ ቢሆንም ቡድኖች ይበልጥ ጠንክረው በሚቀርቡበት ሁለተኛው ዙር ስልነት ጨምሮ መቅረብ ይጠበቅበታል።

የ1ኛ ዙር ኮከብ ተጫዋች

ጫላ ተሺታ፡ ከሦስት ዓመታት በፊት በ17 ዓመት በታች የኢትዮጽያ ብሔራዊ ቡድን ካሸበረቁት ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ጫላ ተሽታ ዘንድሮ በተቀላቀለው ወልቂጤ ከተማ ወደ ትልቅ ተጫዋችነት የመሸጋገር ጉዞውን ጀምሯል። የመጀመርያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ያልተሰለፈው ጫላ በ3ኛው ሳምንት ፋሲልን ሲረቱ ያገኘውን እድል በአግባቡ በጠመቀም ድንቅ እንቅስቃሴ ካደረገ በኋላ በተከታታይ 12 ሳምንታት በመጀመርያ ተሰላፊነት ድንቅ ግልጋሎት አበርክቷል። ፈጣኑ የመስመር አጥቂ የቡድኑ ዋንኛ የማጥቃት መሳርያ ሲሆን በግል ጥረቱ ከሚፈጥራቸው የጎል እድሎች በተጨማሪ አራት ጎሎች በማስቆጠር እና ሁለት በማመቻቸት ቡድኑ ካስቆጠራቸው አጠቃላይ ጎሎች ግማሹ ላይ ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት ችሏል።

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች

አሕመድ ሁሴን፡ ዓምና በከፍተኛ ሊጉ የመጀመርያ የወልቂጤ ቆይታውን ያደረገውና ለጎል አስቆጣሪነት ሲፎካከር የቆየው አሕመድ ዘንድሮ ለሊጉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለመላመድ ተቸግሮ የቆየ ቢሆንም በሒደት ወደ መጀመርያ አሰላለፍ በመመለስ ወሳኝ ተጫዋች መሆን ችሏል። ፍጥነቱ እና ለግላጋ ቁመናው በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች አራት ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን ለቡድኑ በሁለተኛ ዙር የአጨራረስ እና ቦታ አያያዝ ብቃቱን አሻሽሎ ከቀረበ ለቡድኑ እጅግ ጠቃሚው ተጫዋች መሆን ይችላል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ