የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ክለቦች ዳሰሳ – ፋሲል ከነማ

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ባሳለፍነው ሳምንት መጠናቀቁን ተከትሎ ክለቦችን በተናጥል በመዳሰስ ላይ እንገኛለን። በዚህኛው ዳሰሳችንም የመጀመሪያውን ዙር በ26 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ፋሲል ከነማን የመጀመሪያ አጋማሽ ጉዞ ተመልክተነዋል።

የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

በ2011 በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ ጠንካራ ሆኖ የቀረበው ፋሲል ከነማ ዓመቱን ሙሉ በሜዳው ሳይሸነፍ ለዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ በመጨረሻው ጨዋታ ቻምፒዮንነቱን አሳልፎ የሰጠ ሲሆን ዓመቱ መጨረሻ ላይ በውበቱ አባተ ምትክ ሥዩም ከበደን በመቀጠር እንዲሁም ጋብሬል አሕመድ፣ ኦሲ ማዊሊ እና እንየው ካሣሁንን በጠንካራው ቡድኑ ላይ በማከል ለውድድር ቀርቧል።

ከሊጉ መጀመር አስቀድሞ በካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ በአዛም ተሸንፎ በጊዜ የተሰናበተው ፋሲል ከነማ በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የቅርብ ተቀናቃኙ መቐለን አሸንፎ ዋንጫ በማንሳት በጥሩ መነቃቃት ነበር የውድድር ዘመኑን የጀመረው።

የፕሪምየር ሊጉን የመጀመሪያ ጨዋታ ከሜዳ ውጪ ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ጎል ነጥብ በመጋራት የጀመረው ፋሲል ከነማ በሜዳው ከአስፈሪ እንቅስቃሴ ጋር ድሬዳዋ ከተማን 5-0 በማሸነፍ ጥሩ አጀማመር ያደረገ ቢመስልም በወልቂጤ 1-0 ተሸንፎ መልሶ ተቀዛቅዞ ነበር። ከዛ በኋላ በተደረጉ ጨዋታዎችም በሜዳው እያሸነፈ ከሜዳው ውጪ ነጥብ እየጣለ ዘልቆ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ተቃራኒ ውጤቶችን አስመዝግቧል። ከሜዳ ውጪ ለመጀመርያ ጊዜ መቐለ 70 እንደርታን አሸንፎ በሜዳው ደግሞ ለመጀመርያ ጊዜ ከጊዮርጊስ ነጥብ በመጋራት በ15ኛ ሳምንት የ2-0 መሪነታቸውን አሳልፈው ሰጥተው በሀዋሳ ከተማ 3-2 ተሸንፈው የቡድኑን የመከላከል እና ውጤት የማስጠበቅ ስነልቦና ጥያቄ ውስጥ በመክተት ነበር አንደኛውን ዙር ያጠናቀቁት ።

በሜዳቸው እጅግ አስፈሪ ከሆኑት ክለቦች መካከል ግንባር ቀደም የሆነው ፋሲል ከነማ ከአንድ የአቻ ውጤት በቀር ሁሉንም ጨዋታዎች ያሸነፈ ሲሆን ከሜዳ ውጭ ካደረጋቸው ጨዋታዎች በተቃራኒው አንዱን ብቻ ከማሸነፉ በቀር ሦስቱን ተሸንፎ ቀሪዎችን አቻ በመውጣት በ26 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የመጀመሪያውን ዙር አጠናቋል።

የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር

ቡድኑ ዘንድሮ ያሳካው ነጥብ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ጋር ካሳካው በአንድ ብልጫ ያለው ሲሆን ጎል በማስቆጠር ረገድም ከፍተኛ መሻሻል አሳይቶ በ10 የሚልቁ ጎሎችን አስቆጥሯል። በተከላካይ መስመር ግን ከአምናው አንፃር መዳከም አሳይቶ በ5 የበለጡ ጎሎች ዘንድሮ ተቆጥሮበታል።

የቡድኑ አቀራረብ

ሥዩም ከበደ ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወት ቡድን በመስራት የሚታወቁ አሰልጣኝ ቢሆኑም በፋሲል ከነማ የዘንድሮው ቆይታቸው ተቀያያሪ አቀራረብ በመጠቀም ሀሳባቸውን ለመረዳት ግራ የሚያጋባ ሆኖ ታይቷል። 

በዘንድሮው የውድድር ዓመት በጉዳት ምክንያት ስብስቡን በአግባቡ መጠቀም ያልቻሉት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ አብዛኛውን ጊዜ 4-3-3 አሰላለፍ ይዘው ወደ ሜዳ የሚገቡ ሲሆን ሜዳቸው ላይ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ለማጥቃት እና ለኳስ ቁጥጥር በሚያመች መልኩ መደበኛውን የ3 አማካዮች ቅርፅ ይጠቀማሉ። በዚህም ከሀብታሙ ወይም ጋብሬል ፊት ሁለት 8 ቁጥር አማካዮችን ማሰለፍ ሲያዘወትሩ ጥንቃቄ በሚያሻቸው የሜዳ ውጪ (አልፎ አልፎ በሜዳቸው) ጨዋታዎች ደግሞ የአማካይ ክፍሉን ቅርጽ በመገልበጥ 4-2-1-3 ወይም 4-2-3-1 በሚመስል አሰላለፍ ይቀርባሉ። በዚህም ሀብታሙ እና ጋብሬልን በማጣመር ለተከላካይ መስመሩ ሽፋን ለመስጠት ይሞክራሉ። 

በተጫዋቾች ምርጫ ረገድ ቡድኑ በአመዛኙ የሰዒድ-ኩሊባሊ-ያሬድ-አምሳሉን ጥምረት ቢጠቀምም በጉዳት ምክንያት ያለተፈጥሯዊ ቦታቸው ሰዒድን በመሀል ተከላካይነት፣ ዓለምብርሀን ይግዛውን በቀኝ መስመር ተከላካይነት ተጠቅመዋል። አምበሉ ያሬድ ባልነበረባቸው ጨዋታዎች ቡድኑ የመከላከል አቅሙ ከመዳከሙ በተጨማሪ የማጥቃት እንቅስቃሴን ከኋላ ለማስጀመር እክል ሲፈጥርባቸው ይስተዋላል። 

በአማካይ ክፍል እንደየአቀራረባቸው የሚለያይ ቢሆንም ሀብተሙ እና ጋብሬል በተከላካይ አማካይ፣ በዛብህ መለዮ እና ሱራፌል ዳኛቸው በመሐል አማካይነት አመዛኙን ጨዋታ ተሰልፈዋል። ከዓምናው አንፃር ዘንድሮ የተቀዛቀዘው ሱራፌል በነፃ ሚና የማጥቃት እንቅስቃሴውን ሲመራ በዛብህ መለዮ በሳጥን-ሳጥን እንቅስቃሴ ሚዛናዊ ማድረግ ሳይ ያተኩራል። 

በፊት መስመር ቀዳሚ ምርጫቸው ከሆነው ሙጂብ ቃሲም ግራ እና ቀኝ ሽመክት ጉግሳ በመደበኛነት፤ ኦሲ ማዊሊ እና ኢዙ አዙካ ደግሞ እየተፈራቁ የመጫወት እድል አግኝተዋል። ሁለቱ የውጪ ዜጎች በተደጋጋሚ በሁለተኛው አጋማሽ አንደኛው ሌላኛውን ቀይሮ ሲገባ መመልከት የተለመደ ነው።

ጠንካራ ጎን

ፋሲል ከነማ በሜዳው ላይ ያለው የበላይነት ጠንካራ ጎኑ ነው። በአጠቃላይ ካስመዘገበው 7 ድል ስድስቱ በሜዳው የተመዘገበ መሆኑ እና ከተሸነፈ ረጅም ጊዜያት ማስቆጠሩ ለዚህ እንደማሳያ የሚቆጠር ነው። ጠንካራ የደጋፊ መሰረት ያለው ክለቡ በሞቀ ድባብ ጨዋታዎችን ማድረጉ የተቃራኒ ቡድን ላይ ጫና በመፍጠር ለቡድኑ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማበርከቱ በተጨማሪ ቡድኑ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሜዳው እያስመዘገበው ያለው ተከታታይ ድል ተጫዋቾቹ የማሸነፍ አዕምሮ ገንብተው ወደ ሜዳ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። በዚህም ጥሩ ባልነበሩበት ጨዋታ ሁሉ ነጥብ ይዘው እንዲወጡ አድርጓቸዋል።

የቡድኑ ሥል የፊት መስመር ሌላው ጠንካራ ጎን ነው። ከአጠቃላይ 25 የቡድኑ ጎሎች 20 ያስቆጠሩት የፊት መስመር ተጣማሪዎች ቡድኑ በየትኛውም አጨዋወት ወደ ሜዳ ቢገባ የጎል እድል ለመፍጠር እና ለማስቆጠር የሚተጉ ናቸው። የሊጉን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት በ14 ጎሎች እየመራ የሚገኘው ሙጂብ ቃሲም አጋጣሚዎችን ወደ ጎል የመቀየር አቅሙን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ ሲገኝ ተጣማሪዎቹ ሽመክት ጉግሳ እና ማዊሊ/አዙካም በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ቡድኑ ለሚፈጥራቸው የለል እድሎች ዋንኛ መሳርያ ናቸው።

ደካማ ጎን

ከሜዳ ውጪ ለማሸነፍ መቸገር የቡድኑ ደካማ ጎን ነው። ከሜዳ ውጪ ድል ማስመዝገብ የሁሉም የሊጉ ክለቦች ድክመት ቢሆንም ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድን ጥቂት ጨዋታዎችን አሸንፎ መመለስ ግድ ይለዋል። በዚህ ዓመት አንድ ጨዋታ ብቻ ከሜዳው ውጪ ያሸነፈው ፋሲል ከነማ ለጨዋታዎች ሲቀርብ ያለው የአዕምሮ ዝግጁነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ ነው። ሰበታን 3-1 እየመራ በጭማሪ ደቂቃዎች ሁለት ጎሎች አስተናግዶ አቻ መለያየቱ፣ ከሀዋሳ ከተማ ጋር በተመሳሳይ 2-0 እየመራ 3-2 መሸነፉ እንዲሁም በስሑል ሽረ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ጎሎች መሸነፉ ቡድኑ ከሜዳ ውጪ ሲጫወት ያለበትን ችግር የሚያሳዩ ናቸው።

የኋላ ክፍሉ ዘንድሮ ከዓምናው ድክመት አሳይቷል። በ2011 በሙሉ የውድድር ዓመት 17 ጎሎች ብቻ ያስተናገደው ቡድኑ ዘንድሮ ገና ከወዲሁ 13 ጎሎች ያስተናገደ ሲሆን የተጫዋቾች ጉዳት እንዳለ ሆኖ አጨዋወቱም ጎሎችን ለማስተናገዱ እንደምክንያት ሊጠቀስ ይችላል። ዓምና በኳስ ቁጥጥር ጨዋታውን በራሱ መንገድ ሲከውን የነበረ በመሆኑ እምብዛም የጎል ሙከራ ሲስተናገድበት አይታይም። ዘንድሮ በአንፃሩ ኳስ ከመቆጣጠር ይልቅ ለቀጥተኛ አጨዋወት ትኩረት የሰጠው ቡድኑ በቀላሉ ለሙከራዎች ተጋላጭ ሲሆን በአንዳንድ ጨዋታዎችም የሚኬል ሳማኬ ብቃት ከዚህ በላይ ግብ እንዳያስተናግዱ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታው በቅጣት ምክንያት የመጀመሪያ የሜዳ ጨዋታውን ከሜዳ ውጭ ሊያደርግ የሚችለው ፋሲል ከነማ ከአዳማ ከነማ ፈተና ይጠብቀዋል። በተጨማሪም በሜዳቸው ጠንካራ ከሚባሉ የሊጉ ቡድኖች መካከል የሚመደቡት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ባህር ዳር፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡናን የመሳሰሉ ቡድኖችን ከሜዳው ውጪ የሚገጥም እንደመሆኑ ቀላል ጉዞ አይጠብቀውም።

ቡድኑ በአጠቃላይ ሲታይ የተሟላ የቡድን ስብስብ አለው ለማለት ያስደፍራል። በጉዳት ከሜዳ የራቁት ተጫዋቾቹ ቀስ በቀስ ወደ ሜዳ እየተመለሱ መሆኑም አማራጩን እንደሚያሰፉለት ይጠበቃል። አብዱረህማን ሙባረክ እና ሰለሞን ሀብቴ ወደ ሜዳ ከመመለሳቸው ባሻገር በተለያየ ጊዜ ተቀይረው በመግባት ክለቡን እያገለገሉ ያሉት ዓለምብርሃን ይግዛው፣ ዳንኤል ዘመዴ እና ኪሩቤል ኃይሉ ለሁለተኛው ዙር ጥሩ አማራጭ ይፈጥራሉ።

የ1ኛ ዙር ኮኮብ ተጫዋች

ሙጂብ ቃሲም፡ በፕሪምየር ሊጉ በ15 ጨዋታዎች 14 ግብ በማስቆጠር የግማሽ ዙር ከፍተኛ ግብ አግቢ በመሆን ያጠናቀቀው ሙጂብ በተለይ ፋሲል ከ7ኛ እስከ 14ኛ ሳምንት ነጥብ ይዞ በወጣባቸው ጨዋታዎች ላይ ወሳኝ ግቦችን በመስቆጠር ክለቡ ሁለተኛ ደረጃ እንዲይዝ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከተከላካይነት ወደ አጥቂ ስፍራ እንደመምጣቱ ቀስ በቀስ ቦታውን በመላመድ ድንቅ ጎል አስቆጣሪ መሆን የቻለው ሙጂብ ከቡድን አጋሮቹ የተሻለ የኳስ አቅርቦት ካገኘ ከዚህ የበለጠ አስፈሪ መሆን እንደሚችል እያሳየ ይገኛል።

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች

ዓለምብርሃን ይግዛው፡ ዓምና በውበቱ አባተ አማካይነት ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ ተቀይሮ በመግባት ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየው ዓለምብርሃን ይግዛው ዘንድሮ የተሻለ የመሰለፍ እድል ያገኘ ሲሆን በተለይ በያሬድ ባዬ ጉዳት ምክንያት ሰዒድ ሀሰን ወደ መሐል ተከላካይ ተሸጋሽጎ ዓለምብርሀን በቀኝ መስመር ተከላካይነት (ተፈጥሯዊ ቦታው አማካይ ነው)ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል። ወጣቱ ከወዲሁ በተለያዩ ቦታዎች የመጫወት ልምድ እያዳበረ መምጣቱ በሁለተኛው ዙር ለቡድኑ አማራጭ እንደሚያሰፋ ተስፋ ተጥሎበታል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ