የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ክለቦች ዳሰሳ – ኢትዮጵያ ቡና

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር የክለቦች ዳሰሳችን ቀጣይ የምንመለከተው ክለብ የመጀመሪያውን ዙር በ18 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀውና በጨዋታ መንገዱ አነነጋጋሪ ሆኖ የቀረበው ኢትዮጵያ ቡናን ይመለከታል።

የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

ለዘመናት በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ የክለቡ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰደውን የጨዋታ መንገድ ዳግም እንዲመለስ ለዘመናት ሲደረጉ የነበሩ ግፊቶችን ተከትሎ በክረምቱ ከተጫዋችነት አንስቶ በ1995/96 የውድድር ዘመን ክለቡን በማሰልጠን ተስፋ ሰጪ የሆነ እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከክለቡ ከተለያየ በኋላ ያለፉትን 16 ዓመታት በሀገረ አሜሪካ ቆይታ ያደረገው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ዳግም ወደ ክለቡ በመመልስ፤ ደጋፊዎችም ከወትሮው በተሻለ በተስፋ በማድረግ ውስጥ ሆነው የተጀመረ የውድድር ዘመን ነበር።

ከዓምናው የቡድኑ ስብስብ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ የተቀየረው ቡድኑ ከተጫዋቾች ምልመላ ጨምሮ የተለየን መንገድ በመከተል ያለ ምንም የውጭ ሀገር ተጫዋች እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ የመጫወት ልምድ በሌላቸው ተጫዋቾች የተገነባ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማሳየቱ (ከግማሽ ፍፃሜ ቢሰናበትም) ቡድኑ በሊጉ በምን መልኩ ይቀርብ ይሆን? መከተል ለሚፈልገው የጨዋታ መንገድ ምቹ ሳላለመሆናቸው የሚነገርላቸው የክልል ሜዳዎች ላይ ቡድኑ እንዴት ይዘልቀው ይሆን? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በበርካቶች ዘንድ በጉጉት የተጠበቀ የውድድር ዘመን ነበር።

በመጀመሪያው ሳምንት ከሜዳው ውጪ በስሑል ሽረ ሽንፈት በማስተናገድ የውድድር ዘመኑን የከፈተው ቡድኑ በሁለተኛው ሳምንት በሜዳው ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በቂ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ተቸገሮ ያለ ግብ አቻ ሲለያይ በቀጣይ በሦስተኛ ሳምንት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር 1-1 በተለያየበት ጨዋታ ከአጫጭር ቅብብሎች ውጭ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ረጃጅም ኳሶችን መጠቀም መጀመራቸው ትኩረት የሚስብ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። ከ4ኛ ሳምንት ጀምሮ እስከ 10ኛ ሳምንት በነበሩት የጨዋታ ሳምንታት ደግሞ ቡድኑ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እጅግ የተሻለ የነበረበት ሲሆን በእነዚህ ወቅት ባደረጋቸው ሦስት የሜዳ ጨዋታዎች በድምሩ 11 ግቦችን በማስቆጠር ያሸነፉባቸው እንዲሁም ከሜዳቸው ውጭ ከባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከተማ ጋር ቢሸነፉም ድንቅ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያሳዩባቸው ጨዋታዎች ተጠቃሽ የቡድኑን መሻሻል ማሳያዎች ነበሩ።

በ11ኛው ሳምንት በሸገር ደርቢ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ከተሸነፉበት ጨዋታ አንስቶ ቡድኑ በተከታታይ ጨዋታዎች እጅጉን ተቸግሮ በተጋጣሚዎቹ ሲፈተን የተስተዋለ ሲሆን በተስፋ የውድድር ዘመኑን የጀመሩትና በሒደት ቡድናቸው ላይ በተመለከቱት መሻሻሎች በተስፋ የተሞሉትን ደጋፊዎችን አንገት ባስደፋው ተከታታይ ውጤት አልባ ጎዞ በተጋጣሚ በቀላሉ የሚተነበየውና የኃልዮሽና የጎንዮሽ ቅብብል ያበዛል የሚባለውን የቡድናቸው አጨዋወት የተወሰኑ የቡድኑ ደጋፊዎችን ወደ ተቃውሞ እንዲሁም ተጫዋቾች ከፍ ወዳለ ጫና ውስጥ ገብተው የሰነበቱ ቢሆንም በዙሩ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች የተሻሻለን እንቅስቃሴ በማሳየት በሽንፈት የጀመሩትን ዙር በድል ለማጠናቀቅ በቅተዋል።

የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር

ዓምና በዚህ ወቅት በፈንሳዊው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ይመራ ከነበረው ኢትዮጵያ ቡና የዘንንሮው የውጤት መቀዛቀዝ አሳይቷል ማለት ይቻላል። ዓምና በ22 ነጥብ 8ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ የዘንድሮው በአራት ነጥቦች ዝቅ ብሏል። በተቃራኒው ዓምና በአንደኛው ዙር 11 ግቦችን ብቻ ሲያስቆጥር ዘንድሮ 20 ግቦችን በማስቆጠር የተሻሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴን እያስመለከተ ሲገኝ ዘንድሮ ቡድኑ ከሚከተለው ለስህተት የተጋለጠ አጨዋወት ጋር ተዳምሮ ከዐምናው 5 ተጨማሪ ግቦችን ያስተናገደበት ሒደት መመልከት ይቻላል።

የቡድኑ አቀራረብ

እንደ አብዛኛዎቹ በኳስ ቁጥጥር ለመጫወት እንደሚያስቡ ቡድኖች 4-3-3 (በአሰልጣኙ እሳቤ 5-3-3) ለመጫወት የሚሞክር ሲሆን ከኳስ ውጭ ደግሞ በአመዛኙ በ4-5-1 / 4-2-3-1 ቅርፅ ለመከላከል የሚሞክር ቡድን ስለመሆኑ ከመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች መመልከት ተችሏል።

ቡድኑ ከግብጠባቂ በስተቀር አብዛኛው የመጀመሪያ ተመራጭ ተሰላፊ ተጫዋቾቹ ተመሳሳይነት ያላቸው ስለመሆኑ የ15 ሳምንት የመጀመሪያ ዙር ምስክር ነው። በዚህ ስፍራ ላይ ተክለማርያም ሻንቆ እና በረከት አማረን በማፈራረቅ የሚጠቀም ሲሆን ግብ ከመጠበቅ በዘለለ ኳስን እንዲያስጀምሩ ከፍ ያለ ኃላፊነት የተጣለባቸው ሁለቱ ግብጠባቂዎች ከአብዛኛዎቹ የሀገራችን በረኞች አንፃር ከፍ ያለ የራስ መተማመን ደረጃ ላይ ስለመሆናቸው ባያጠያይቅም ረጃጅም ኳሶችን የማቀበል ስኬታቸው ግን አሁንም ስራ የሚፈልግ ነው። 

በተከላካይ መስመር በተወሰኑ አጋጣሚዎች ኃይሌ ገ/ተንሳይ ወደ መጀመሪያ ተመራጭ ከመጣባቸው ጨዋታዎች ውጭ ፈቱዲን ጀማል እና ወንድሜነህ ደረጀ በመሐል ተከላካይነት እንዲሁም አህመድ ረሺድ እና አሥራት ቱንጆ በቀኝ እና ግራ የመስመር ተከላካይነት የሚሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው። የመስመር ተከላካዮቹ አህመድ እና አሥራት ቡድኑ በሜዳው ስፋት በተሻለ ሁኔታ እንዲያጠቁ ከማስቻል ባለፈ በተለይ አህመድ ረሺድ በሜዳው የላይኛው ክፍል የሚያደርጋቸው ድንገተኛ የማፈትለክ ሩጫዎች በተደጋጋሚ ለተጋጣሚ ቡድኖች አደጋ ሲፈጥሩ ይስተዋላል። ሁለቱ የመሐል ተከላካዮች እጅግ የተረጋጉ እና ከኳስ ጋር ምቾት የሚሰማቸው ሲሆኑ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅትም ያላቸው የማሸነፍ ንፃሬ ከፍ ያለ ነው። 

ቡድኑ ውድድሩን ሲጀምር ዓለምአንተ ካሳን በ6 ቁጥር ሚና ሲጠቀም የሰነበተ ቢሆንም በተጫዋቹ በጫና ውስጥ ሆኖ የኳስ ምስረታ ሒደት የማስቀጠሉ ሁኔታ ደካማ ከመሆኑና በቀላሉ በሚደርስበት ጫና ስህተቶችን ሲሰራ መስተዋሉ አሰልጣኝ ካሳዬ አምበሉ አማኑኤል ዮሐንስን በዚህ ስፍራ ወደመጠቀም መጥተዋል። ከአማኑኤል / ዓለምአንተ ፊት የሚገኙት ሁለቱ የአጥቂ አማካዮች ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን እና ታፈሰ ሰለሞን ይበልጥ ኳሱ ወደ ተቃራኒ የሜዳ አጋማሽ ከደረሰ ወዲህ ተፅዕኗቸው ከፍ ቢልም ቡድኑ ከሁለቱ 8 ቁጥሮች ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ያክል አግኝቷል ብሎ ለመናገር ግን አያስደፍርም።

ኢትዮጵያ ቡና ከሁሉም የቡድኑ ክፍሎች ውስጥ ትክክለኛ ቀመር ያልተገኘት የአጥቂ መስመሩ ጥምረት ይመስላል። በአመዛኙ የሊጉ ጨዋታዎች እንዳለ ደባልቄን በ9 ቁጥር አጥቂነት የተጠቀመው ቡድኑ ተጫዋቹ ሳጥኑን ከማጥቃት ይልቅ ጀርባውን ለጎል ሰጥቶ ቅብብሎሾችን የማስቀጠልና ሌሎች ተጫዋቾች ወደ አደገኛ ቀጠና እንዲገቡ ከሚያደርገው ጥረት በአሰልጣኙ በተደጋጋሚ ሲሞካሽበት ቢሰማም ከእነዚህ በዘለለ የግብ ማግባት ኃላፊነቱን በበቂ ደረጃ ተወጥቷል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። በመጨረሻ ሳምንታት ግን ፈጣኑና ያለውን ሳይሰስት ለቡድኑ የሚሰጠው አቡበከር ናስር የፊት አጥቂነቱን ሚና ከእንዳለ ተረክቧል። አቡበከር ምንም እንኳን በተደጋጋሚ ጉዳት የተነሳ በበቂ መልኩ ቡድኑን ማገልገል እየቻለ ባሆንም ጤነኛ በሆነባቸው ወቅቶች የቡድኑን የፊት መስመር ግርማ ሲያላብስ ይስተዋላል።

በመስመር አጥቂነት ቡድኑን እየተጠቀማቸው የሚገኙት ሚኪያስ መኮንን እንዲሁም አቤል ከበደ / ሐብታሙ ታደሰ ቡድኑ በማጥቃት ሽግግር ወቅት መተግበር ለሚያስበው የሜዳውን ሰፋት በመለጥጥ በሚደረገው የማጥቃት ሽግግር ውስጥ ከፍ ያለ ሚናን ይወጣሉ። በተለጠጠ አቋቋም ከወደ መስመር መነሻቸውን የሚያደርጉት የመስመር አጥቂዎች ወደ መሀል እየሰበሩ በመግባት ተደጋጋሚ አደጋዎችን ሲፈጥሩ ይስተዋላል።

በአጨዋወት ደረጃ ከአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጀምሮ ቡድኑ ይተችበት የነበረው ኳሶችን ከኋላ ጀምረው ወደ ተጋጣሚ የአደጋ ክልል ለመድረስ የሚፈጅባቸው ጊዜ እጅግ ዘለግ ያለመሆኑ ስለመሆኑ የነበረ ቢሆንም በተለይ ከዙሩ አጋማሽ በኋላ የታፈሰ ሰለሞን ከጉዳት መመለስን ተከትሎ ተጫዋቹ ይህን ቀርፋፋ ሂደት ለማፍጠን ወደፊት ቅብብሎችን በማድረግ አይነተኛ ሚናን ሲወጣ ተስተውሏል። በተጨማሪም ከተፈጥሯዊ ቦታው ወደ 8 ቁጥር ሚና ተገፍቶ ይጫወት የነበረው አማኑኤል ዮሐንስ አይነተኛ ሚና ነበረው። በተለይ በእነዚሁ ሳምንታት አብዛኛዎቹ ቡድኖች ተቀዛቅዘው በሚቀርቡበት በሁለተኛው አጋማሾች ላይ በተሻለ መልኩ ከፍ ባለ ትጋትና ከተጋጣሚ ቡድኖች በመጀመሪያ አጋማሽ ለሚገጥማቸው ፈተና ምላሽ ሰጥተው ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት በሁለተኛው አጋማሽ በርከት ያሉ የግብ እድሎችን በመፍጠር ግቦችን ማስቆጠር የቻሉባቸው አጋጣሚዎችም ተስተውለዋል።

ቡድኑ መገለጫው ከሆነው ተጠጋግቶ መጫወት እና አጫጭር ቅብብሎች አንፃር ረጃጅም ኳሶችን አልፎ አልፎ ሲጠቀም የሚስተዋል ሲሆን ይህም ከተጫዋቾች ደመነፍስ ወይስ የአሰልጣኙ ፍላጎት የሚሉ ሀሳቦች መንሸራሸር የጀመሩበት ወቅት ነበር ይህ የአንደኛው ዙር።

ጠንካራ ጎን

የአሰልጣኝ ካሳዬው ኢትዮጵያ ቡና በእስካሁን ጉዞው ውስጥ ያለው ዋነኛ ጠንካራ ጎን እና ለኢትዮጵያ እግርኳስ እንደ አጠቃላይ ያስተዋወቀው አዲስ ነገር ተብሎ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ጉዳይ ቢኖር በተጫዋቾች ላይ ከፍ ያለ የራስ መተማመን ስሜት በማስረፅና ተጫዋቾች በጫና ውስጥ እንኳን ቢሆኑም እንዲተገብሩት በተፈለገው የጨዋታ መንገድ በፅናት እንዲቆሙ ማድረግ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ጥንካሬው ነው።

በግልፅ የሚታይን ኳስን መሰረት ያደረገና በአጫጭር ቅብብሎች የተመሰረተን የጨዋታ መንገድ ለመተግበር ሲታትር የሚታየው ቡድኑ በዘፈቀደ ባልተጠኑ አጨዋወቶች ውስጥ ምን አስበው ሜዳ እንደገቡ እንኳን በማይታወቁ ቡድኖች በተሞላው ሊጉ ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ ቡና ምን ማድረግ እንደሚፈልግ በግልፅ የሚታወቅ እንዲሆም ከስህተቶች የፀዱ ባይሆንም የፈለጉትን ነገር ለመተግበር የሚሄዱበትን ርቀት በግልፅ የሚታይ ቡድን ማግኘት ከባድ ነው።

በማጥቃት ሽግግር ወቅት ቡድኑ የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም የሚያደርገው ጥረት ጥሩ የሚባል ነው። መስመር ተከላካዮችና የመስመር አጥቂዎች በተናበበ ሒደት በዚህ እንቅስቃሴ ለመጠቀም የሚሞክሩበት መንገድ ጥሩ የሚባል ነው።

ደካማ ጎን

የቡድኑ አንደኛውና ዋነኛው ድክመት ተገማች የሆነ የተጫዋቾች ምርጫና በቀላሉ በተቃራኒ ቡድኖች አጨዋወቱን በመተንተን የመፍትሔ ስልቶች እንዲነድፉ የተመቸ የጨዋታ መንገድ ነው። ለዚህም የቅዱስ ጊዮርጊስና የወልቂጤ ከተማ በቂ ማሳያ ናቸው። በሒደት ግን በመጠኑም ቢሆን ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት በመጣል ሌላ አይነት የማጥቃት መንገድን ለማስተዋወቅ እየሞከረ ያለው ቡድኑ በሁለተኛው ዙር በመሰረታዊነት የያዙትን ሀሳብ ሳይለቁ ተጨማሪ ተገማች ያልሆኑ መንገዶችን በመፈለግ መቅረብ ይኖርባቸዋል።

ቡድኑ ወደራሳቸው የሜዳ ክልል ሰብሰብ ብለው ከሚጫወቱ ቡድኖች ጋር ሲጫወት በቀላሉ ኳሶችን እየመሰረተ በመውጣት ኳሱን በተደጋጋሚ ወደ መሀል ሜዳ ይዘው መድረስ ቢችሉም የተቸመቸመን የተከላካይ ክፍል ለማስከፈት በሜዳው ስፋት ለመጫወት ቢሞክሩም ሳጥን ውስጥና አካባቢው ላይ ከአህመድ ረሺድ ውጭ በስፋት ከኳስ ውጭ ድንገተኛ እንቅስቃሴ አለመኖርና በመሰል ሒደቶች የሚገኙ ውስን እድሎችን በመጠቀም ረገድ ችግሮች ይስተዋሉበታል። በተቃራኒው ቡድኖች ገፍተው በቡና የሜዳ አጋማሽ ኳስን እንዳይመሰርቱ ጫና በሚያሳድሩበት ወቅት ወደ 2-3-5 በተጠጋ ቅርፅ ኳሱን ለመመስረት በሚያደርጉት ጥረት ወቅት ብዙ ችግሮች ሲገጥሙት ይስዋላል።

አንደኛው ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ከግብጠባቂው በተወሰነ መልኩ ወደፊት ጠጋ ባለ አቋቋም ለጥጠው ኳሶችን ለማስጀመር ቢቀበሉም በተለይ 6 ቁጥሩ ቀርቦ እስካልተቀበላቸው ድረስ ከፊታቸው የሚገኙት የተከፈቱ የሜዳ ክፍሎች ተጠቅሞ ኳሶችን ከግብ ክልላቸው እየነዱ ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት እምብዛም አናሳ መሆኑ የምስረታ ሂደታቸው እጅግ ዘገም ያለና በርከት ያሉ ከግብጠባቂ ወደ መሀል ተከላካዮች እና ከመሀል ተከላካዮች ወደ ግብጠባቂ የሚደረጉ ተደጋጋሚ ቅብብሎች ይስተዋላሉ።

ሌላኛው በምስረታ ሂደት ወቅት የሚስተዋለው ችግር የተከላካይ አማካያቸው በተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች ቁጥጥር ስል በሚውልበት ወቅት ብቸኛው የኳስ መስርቶ መውጫ አማራጫቸው የሚሆኑት ሁለቱን የመስመር ተከላካዮችን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እምብዛም ውጤታማ አይደሉም ፤ ይህም በዋነኝነት ከግብ ጠባቂዎቹ የኳስ ማሰራጨት አቅም ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው። ምንም እንኳን ግብጠባቂዎቹ በንፅፅር የተሻለ ኳስን በእግር የማቀበል አቅም እንዳላቸው ቢታመንም በተለይ በተንጠልጣይና ረጃጅም ኳሶችን የማቀበል ስኬታቸው ግን በደንብ በልምምድ እየዳበረ መሻሻል እንዳለበት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች የጠቆሙ ነበሩ።

በጥቅሉ እንደጅምር የኳስ ምስረታቸው ተስፋ ሰጪ ነገሮች ቢኖሩትም በተሻለ ተለዋዋጭ መልኮች ቢቃኙና ተጋጣሚ እንደሚቀርብበት ሁኔታ የሚቀያየሩና ቢሆኑ ቡድኑ የተለያዮ ተጋጣሚዎች በምስረታ ወቅት ሊደቅኑበት የሚችሉትን ስጋቶች በስኬት የመወጣት እድሉ ከፍ ያለ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው።

በተመሳሳይ ቡድኑ ኳስን በመቆጣጠሩ ረገድ ብዙ ጥረቶችን ቢያደርግም እነዚህን ቅብብሎች በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ አደገኛ ቀጠናዎች ላይ ለመድረስ የሚፈጅባቸው እጅግ ዘለግ ያለ ጊዜ መሆኑ ሌላኛው ችግር ነው። ምንም እንኳን መሰል ሂደቶች ለመዳበር ጊዜ የሚፈልጎ ቢሆንም በራስ ሜዳ አጋማሽ የሚደረጉ ቅብብሎች እራስ ላይ አደጋ ከመጋበዝ በዘለለ ጠቀሜታቸው አናሳ ነው።

ሌላኛው በመጀመሪያ ዙር የተመለከትነው ችግር ሁለቱ 8 ቁጥሮች በተለይ የተጋጣሚ ቡድኖች የመከላከል አወቃቀር ውስጥ በመስመሮች መካከል የሚገኙትን ክፍት ቦታዎችን አጠቃቀም ረገድ ችግሮች ይስተዋላሉ።

በሁለተኛ ዙር ምን ይጠበቃል?

ቡድኑ ምንም እንኳን ከክለቡ የበላይ አመራሮች የሽግግር ጊዜ ላይ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ይህ ነው ተብሎ የተቀመጠ የውጤት መለኪያ ባይኖርም ከደጋፊዎቹ ፍላጎትና ቡድኑ ለመከተል የሚያስበው አጨዋወት በሒደት እየዳበረ የሚሄድ ከመሆኑ አንፃር በተለይ ቡድኑ በሁለተኛው ዙር በሜዳቸው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ነጥቦችን በተሻለ በመሰብሰብ በሊጉ ሰንጠረዥ ላይ ከወገብ በላይ ማጠናቀቅ ግዴታ ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይታመናል።

ምንም እንኳን ከሊጉ አስቸጋሪ ባህሪ አንፃር የሜዳ ውጭ ጨዋታዎችን የማሸነፍ እድሉ ወደ ባለሜዳው ያጋደለ ቢሆንም በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሆኑ ክለቦች ጋር ከሜዳቸው ውጭ ያላቸውን ጨዋታዎች ከመጨረሱ አንፃር በሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው የተሻለ ነጥብ የማግኘት እድሉ የሰፋ ይመስላል።

የ1ኛ ዙር ኮከብ ተጫዋች

ወንድሜነህ ደረጀ፡ በክረምቱ ባህርዳር ከተማን ለቆ ኢትዮጵያ ቡና የተቀላቀለው የመሀል ተከላካዩ ወንድሜነህ ደረጀ በኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያ ዙር ጉዞ ውስጥ በጉልህ የሚታይ አሻራን እያሳረፈ ይገኛል። በሁሉም ጨዋታዎች በመጀመሪያ ተሰላፊነት የጀመረው ተከላካዮ ለስህተት በቀረበውና ብዙ ግላዊ ሀላፊነት (Risk) መውሰድ በሚጠይቀው የቡድኑ አጨዋወት ውስጥ በአስገራሚ የራስ መተማመንና ስኬታማ በሆነ የኳስ ቅብብሎቹ ጥድፊያዎችና የተጋነነ የራስ መተማመን በሚስተዋልበት የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር ስክነትን በማላበስ አይተኬ ሚናን በመጀመሪያው ዙር ተወጥቷል። በተጨማሪም በመከላከሉ ረገድ ወሳኝ ሰዓት የሚያቋርጣቸው ኳሶች ለቡድኑ አለኝታ ነበር።

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች

ሀብታሙ ታደሰ፡ በሊጉ ጅምሮ በቂ የመሰለፍ እድል እያገኘ ያልነበረውና በክረምቱ ከከፍተኛ ሊጉ ክለብ ወልቂጤ ከተማ ቡድኑን የተቀላቀለው ሀብታሙ ታደሰ በሂደት በተጫዋቾች ጉዳትና ቅጣት በታመሰው የኢትዮጵያ ቡና የፊት መስመር ያገኛቸውን የመጫወቻ እድሎች በአግባቡ በመጠቀም ራሱን እያስተዋወቀ ይገኛል። በ6ኛው ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕና በሰፊ ግብ ባሸነፉበት ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት የመጀመሪያ የሊግ ግቡን ያስቆጠረው ሀብታሙ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች (ከአዳማው በስተቀር) በሁሉም ጨዋታዎች ላይ አቅሙን እያስመሰከረ ይገኛል። ከመስመር አየተነሳ ተጫዋቾችን ለመቀነስ የማይቸገረው ሀብታሙ በቀጣይ እራሱን እያጎለበተ የሚሄድ ከሆነ ለኢትዮጵያ ቡና በፊት መስመር በቀጣይ አመታት ከፍ ባለ ደረጃ ያገለግላል ተብሎ ይጠበቃል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ