ሀዋሳ ከተማ በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ምትክ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሾሟል

የሀዋሳ ከተማ ቦርድ አሰልጣኝ አዲሴ ካሳን ከአሰልጣኝነት ሲያነሳ ከ20 ዓመት ቡድኑ አሰልጣኝ ብርሀኑ ወርቁን ጊዜያዊ አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

በአስራ አምስተኛው ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ በፋሲል ከተማ ሲመሩ በነበረበት ወቅት ከደጋፊው ተቃውሞ የገጠማቸው አሰልጣኝ አዲሴ ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ 3ለ2 በመርታት ሙሉ ሶስት ነጥብ ካሳካ በኋላ ስልካቸውን ዘግተው ለሳምንት ከክለቡ የራቁ በመሆኑ ቦርድ ባደረገው ስብሰባ አሰልጣኙን ለማሰናበት መወሰኑን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ጠሃ አሕመድ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

በአሰልጣኝ አዲሴ ምትክ ብርሀኑ ወርቁ (ፈየራ) ጊዜያዊ አሰልጣኝ በማድረግ መሾሙን ስራ አስኪያጁ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የቀድሞው የክለቡ የመሐል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ብርሀኑ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ በተጫዋችነት ያሳለፈ ሲሆን በሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማም ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ መጫወት ካቆመ በኋላ ያለፉትን አራት ዓመታት የሀዋሳ ሴቶች ቡድን ረዳት እንዲሁም ከ2010 ጀምሮ ደግሞ ከ17 እና 20 የሀዋሳ ቡድኖችን በማሰልጠን ያሳለፈ ሲሆን በሁለቱም ቡድን ቆይታው የእርከኖቹን የሊግ ዋንጫ አሳክቷል፡፡ አሰልጣኝ ብርሀኑ ከነገ ማለዳ ጀምሮ ቡድኑን በመረከብም ቀጣይ ጨዋታዎችን በጊዜያዊነት ይመራል ተብሏል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ