አጥቂው ሳምሶን ቆልቻ እና ተከላካዩ ዐወል አብደላ ከጦና ንቦቹ ጋር ተለያይተዋል፡፡
በአሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ እና ረዳቶቹ እየተመሩ ትናንት በሶዶ ስታዲየም ለሁለተኛው ዙር የፕሪምየር ሊግ ቀጣይ ጨዋታዎች ዝግጅት የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረሙ ሲሆን ክለቡን ከአቋም ጋር በተገናኘ በተጠበቀው ልክ ማገልገል ባለመቻላቸው ሁለት ተጫዋቾች ከክለቡ ጋር የስድስት ወራት ውል እየቀራቸው በስምምነት ለቋል፡፡
ወደ ቀድሞው ክለባቸው ተመልሰው ከ2011 ጀምሮ መጫወት የጀመሩት አጥቂው ሳምሶን ቆልቻ እና የመሐል ተከላካዩ ዐወል አብደላ ናቸው ከክለቡ የተለያዩት። ከዚህ ቀደም በክለቡ መጫወት ከቻለ በኋላ ወደ ደሴ ከተማ፤ ቀጥሎም በ2010 ወደ ጅማ አባ ጅፋር አምርቶ ከቡድኑ የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ሳምሶን ዘንድሮ በክለቡ የመሰለፍ እድል ሳያገኝ ቆይቷል። በተመሳሳይ በመከላከያ እና ሲዳማ ቡና ቆይታ አድርጎ ወደ ቀድሞው ቡድኑ ተመልሶ ያለፉትን 18 ወራት በጦና ንቦቹ ቤት ቆይታ የነበረው ተከላካዩ ዐወል አብደላ እንደ ሳምሶን ሁሉ በዚህ ዓመት በመጀመሪያው ዙር የክለቡ ጨዋታዎች ላይ ለመሰለፍ ሲቸገር ተመልክተናል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ