ያለከልካይ በነገሱበት ውድድር ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዋንጫ የራቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከጨዋታ ጨዋታ አስገራሚ መሻሻልን በማሳየት የመጀመሪያውን ዙሩን በ28 ነጥብ በመሪነት ማጠናቀቅ ችለዋል። ተከታዩ ዳሰሳችን የመጀመሪያ ዙር ጉዟቸው ምን ይመስል እንደነበር ይመለከታል።
የመጀመሪያ ዙር ጉዞ
በውድድር ዘመኑ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን በማሳየት ጥሩ እድገትን ያሳየ ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ ስለመሆኑ ያለ ጥርጥር መናገር ይቻላል። የውድድር ዘመኑ ዓይን መግለጫ የሆነው የ14ኛው አዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አሸናፊ በመሆን በተሻለ መነቃቃት ሊጉን ይጀምራሉ ተብለው የተጠበቁት ፈረሰኞቹ ከግምቶች በተቃራኒ በመጀመሪያዎቹ አምስት የጨዋታ ሳምንታት ሲቸገሩ የተስተዋለበት ወቅት ነበር። በመከላከሉ ረገድ ጥሩ የነበረው ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ አራት ሳምንታት መረቡን ሳያስደፍር መውጣት ቢችልም በተቃራኒው የግብ እድሎችን ለመፍጠር እጅጉን ሲቸገር ተስተውሏል። በዚህም በመጀመሪያዎቹ አምስት ጨዋታዎች ሁለት ብቻ ግቦችን ማስቆጠሩ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ምን ያህል ደካማ እንደነበረ ማሳያ ነበር።
በ6ኛ ሳምንት ቡድኑ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የአምናው ቻምፒየን መቐለ 70 እንደርታን አስተናግዶ 2-1 የረታበት ጨዋታ አጠቃላይ የቡድኑን መንፈስ ያነቃቃና ቡድኑ በአንደኛው ዙር ማጠቃለያ ይዞት ላጠናቀቀው የአንደኝነት ደረጃ ቁልፍ ጨዋታ ነው ብሎ ማንሳት ይቻላል። ግቦችን ለማስቆጠር ሲቸገር የከረመው ቡድኑ አቤል ያለው እና ሳልሀዲን ሰኢድ ባስቆጠሯቸው ግቦች መቀለን ሲያሸነፉ ስለድክመቱ ብዙ ሲባልለት የነበረው የአጥቂ መስመር የመሻሻል ፍንጮችን ማሳየት የጀመረበት ጨዋታ ነው ብሎ መጥቀስ ይቻላል።
በዚህ ድል ይነቃቃል ተብሎ የተጠበቀው ቡድኑ የታየውን ፍንጭ ለማስቀጠል በተወሰነ መልኩ ተቸግሯል። በተለይ የቡድኑ ሁነኛው ግብ አዳኝ ሳልሀዲን ሰዒድ በተደጋጋሚ ጉዳት መቸገር እንዲሁም ጌታነህ ከበደ ከጉዳት መልስ የቀደመ አቋሙን ለማግኘት መቸገሩ ቡድኑን ወጣ ገባ እንዲል አስገድዶታል። በዚህም የቡድኑ ደጋፊዎች በቡድኑ አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቮጅኖቨ እና በተጫዋቾቻቸው ላይ ተደጋጋሚ ተቃውሞዎችን ማሰማታቸውን ተከትሎ እና በክለቡ አመራሮች ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው አሰልጣኙ ተጫዋቾቻቸው ከገቡበት የስነ ልቦና ጫና እንዲወጡ የልምምድ ስፍራቸውን ቢሾፍቱ ወደሚገኘው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ከቀየሩ ወዲህ ሙሉ ለሙሉ የተቀየረ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመመልከት በቅተናል።
ቡድኑ በ10ኛ ሳምንት አማካዩ ሀይደር ሸረፋ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ባህር ዳር ከተማን በሜዳቸው ከረቱበት ጨዋታ ወዲህ እጅግ ድንቅ ሳምንታትን በማሳለፍ አንደኛውን ዙር በ28 ነጥብ በመሪነት ለማጠናቀቅ በቅተዋል።
በመጨረሻዎቹ 5 የጨዋታ ሳምንታት ከሜዳ ውጭ ለማሸነፍ ተቸግሮ የቆየው ቡድኑ ከሜዳው ውጭ ወልዋሎ አ/ዮ በሰፊ የግብ ልዮነት እንዲሁም ጠንካራውን ፋሲል በጎንደር ለማሸነፍ ቀርቦ በስተመጨረሻ ደቂቃዎች በተቆጠረችበት ግብ አቻ የተለያየባቸው እንዲሁም በሜዳው ሲዳማ ቡና ላይ የግብ ናዳ ያዘነበባቸው ጨዋታዎች ቡድኑ የነበረበት ከፍተኛ መነቃቃት ማሳያ ናቸው።
የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር
ቡድኑ ዐምና በዚህ ወቅት ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ውስጥ ሰባት ጨዋታዎችን አሸንፎ፣ በሶስቱ ደግሞ ተሸንፎ እንዲሁም በቀሪዎቹ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ በ26 ነጥቦች አጋማሹን በሦስተኛ ደረጃ ያጠናቀቀ ሲሆን ይህም ቡድኑ በንፅፅር ከዐምናው በተሻለ ጉዳና ላይ እንደሚገኝ ማሳያ ነው። በአጠቃላይ በተመሳሳይ ወቅት ዐምና አስራ ስምንት ግቦችን አስቆጥሮ በአንፃሩ ሰባት ግቦችን ብቻ አስተናግዶ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ቁጥሮቹ በመከላከሉ ረገድ ከዐምናው አንፃር ድክመቶች እንዲሁም በማጥቃቱ ረገድ መሻሻሎች ስለመኖራቸው ቁጥሮች ይመሰክራሉ።
የጨዋታ አቀራረብ
ቡድኑ በአመዛኙ በ4-3-3 / 4-2-3-1 እንዲሁም አንዳንዴ 4-4-2 በሚመስል አደራደር ወደ ሜዳ ሲገባ በተደጋጋሚ ይስተዋላል።
ቡድኑን በሊጉ ጅማሬ የቡድኑን የመጀመሪያ ሁለት ተመራጭ ግብጠባቂዎች በጉዳት ማጣቱን ተከትሎ በድንገት ያገኘውን እድል በመጠቀም ከተስፋ ቡድን አድጎ ባለፉት ዓመታት በቂ የመሰለፍ እድል ሳያገኝ የቆየው ባህሩ ነጋሽ የመጀመሪያዎቹን 8 ሳምንታት በማገልገል ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ አሳይቷል። ምንም እንኳን በሒደት ከጉዳት ባገገመውና ግብ ከመጠበቅ በዘለለ ቀጥተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴን በማስጀመር ሆነ የተሻለ የተከላካይ መስመሩን የመምራት አቅም ባለው ኬንያዊው ፓትሪክ ማታሲ ቦታውን ቢያስረክብም።
በመከላከል አደረጃጀቱ እጅግ ጠንካራና በቀላሉ የማይበገረው ቡድኑ በዋነኝነት ጋናዊው ኤድዊን ፍሬምፖንግ የዚህ አደረጃጀት ዋነኛ የጀርባ አጥንት ነው። ምንም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች አጣማሪዎቹ ሲቀያቀሩ ቢስተዋልም በፍጥነት ከአስቻለው ታመነ፣ ሰልሀዲን በርጌቾ እና ምንተስኖት አዳነ ጋር በተጣመረባቸው ጨዋታዎች ጥሩ ተግባቦት በመፍጠር የተሻለ ጊዜን አሳልፏል።
የመስመር ተከላካዮች የበለጠ የማጥቃት ነፃነት ያላቸው ቢሆንም ቡድኑ ከሁለቱ የመስመር ተከላካዮች በቂ ግልጋሎት አግኝቷል ብሎ መናገር ያስቸግራል። በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ ከመስመር ተከላካዮች እግር የተሻሙ ኳሶች ወደ ግብነት ሲቀየሩ ብናስተውልም አሁንም ተጫዋቾቹ ካላቸው የማጥቃት ነፃነት አንፃር በማጥቃቱ ላይ ያላቸው አበርክቶ ይበልጥ መሻሻል ይኖርበታል።
በአማካይ ክፍሉ ላይ ከአንድ ጨዋታ በስተቀር ሙሉዓለም መስፍን በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ቡድኑን በተከላካይ አማካይነት ያገለገለ ሲሆን ተጫዋቹ ከሌሎቹ ዓመታት በተሻለ በበርካታ የጨዋታ ቅፅበቶች ወደፊት በመጠጋት የማጥቃቱን እንቅስቃሴ ለማገዝና ከፍ ያለ የሜዳውን ክፍል የማካለል ብርታቱ ጨምሮ ተስተውሏል። በየጨዋታው ይዘው እንደሚገቡት ቅርፅ የሙሉዓለም አጣማሪዎቹ የሚቀያየሩ ቢሆንም ሀይደር ሸረፋ በበርካታ ጨዋታዎች ለሙሉዓለም መስፍን ቀርቦ ከጥልቅ እየተነሳ የማጥቃት ሒደትን ለማስጀመር ይሞክራል።
ለዓመታት የቡድኑ ያልተፈታ የሚባለውን የቡድኑን መሐል ለመሐል የሚደረግ የፈጠራ ሒደት የሚመራ ፈጣሪ አማካይ ችግር ለመቅረፍ በማለም በክረምቱ ሀይደር ሸረፋ ፣ አቤል እንዳለ እና የአብስራ ተስፋዬን ወደ ቡድኑ ቢቀላቀሉም ከሀይደር ውጭ ሁለቱ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ጉዳት ቡድኑን በመጀመሪያ ዙር በሚገባ ማገልገል ሳይችሉ ቀርተዋል። ሀይደር ሸረፋም ቢሆን ከጥልቅ እየተነሳ የሚያደርጋቸው ጥረት ጥሩ የሚባሉ ቢሆንም በሂደት ከቡድኑ ጋር ይበልጥ እየተዋሃደ ሲመጣ አገልግሎቱ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል።
የቡድኑ የፊት መስመር በጉዳትና አቋም መውረድ ቢታመስም በተለይ የአቤል ያለው – ጌታነህ ከበደ – ጋዲሳ መብራቴ ጥምረት እጅግ ድንቅ የሚባል ሳምንታት ማሳለፋቸው አይዘነጋም። በአጥቂዎቹ አስደናቂ ፍጥነት የተነሳ ጥልቀትን ማጥቃት ተቀዳሚ ምርጫው የሆነው ቡድኑ ከሶስቱ ተጫዋቾች ጥምረት የተሻለ ግልጋሎትን በተለይ በመጀመሪያው ዙር አግኝቷል።
ጠንካራ ጎን
የአሰልጣኝ ሰርዳን ዠቮጅኖቨ ስብስብ ከሳቸው በፊት በነበሩት ወቅት እንደነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ የመከላከል አደረጃጀታቸው አሁንም የነበረውን ጥንካሬ በማስቀጠል ረገድ ተሳክቶላቸዋል። በሊጉ ዝግተኛ ግብ ያስተናገደው (11) ቡድኑ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ባለማስተናገድ በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ ጥሩ የመከላከል ክብረወሰን ባለቤት ነው። በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት አሰልጣኙ ለመከላከል ከሚሰጡት የተጋነነ ትኩረት ጋር በተያያዘ በርከት ካሉ የክለቡ ደጋፊዎች ጠንካራ ተቃውሞን ቢያስተናግዱም በሒደት ከተረጋጋው የመከላከል አደረጃጀታቸው ጎን ለጎን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ላይ መሻሻሎችን ማምጣት ችለዋል።
ለወትሮው በትጋት ደረጃቸው ላይ ጥያቄ ይነሳባቸው የነበሩት ጋዲሳ መብራቴና ጌታነህ ከበደ ዘንድሮ ፍፁም የተሻሻሉበትን ዓመት እያሳለፉ ነው። ሁለቱም ተጫዋቾች ጊዮርጊስን ከተቀላቀሉ ወዲህ በቆይታቸው ክለቡን በበቂ ሁኔታ እንዳላገለገሉ ቢታመንም ዘንድሮ ግን በጣም የተሻለ ጊዜን በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ። ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ተመዘግዛጊው አቤል ያለው ግቦችን ከማስቆጠር በዘለለ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል።
ደካማ ጎን
ቡድኑ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከሜዳው ውጭ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ውስጥ አንዱን ብቻ ሲያሸንፍ በአንዱ ተሸንፎ በቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። እንደ አብዛኛዎቹ ቡድኖች ከሜዳ ውጭ ቡድኑ በሚያደርገው ጨዋታ ግቦችን ለማስቆጠርና ለማሸነፍ የሚቸገረው ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ለዋንጫ እንደመጫወቱ በእነዚሁ ወሳኝ የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ላይ ያለውን ክብረወሰን ማሻሻል የግድ ይለዋል።
ሌላኛው ቡድኑ በፍጥነት መፍትሔ መስጠት የሚሻው የአጥቂ መስመሩን እንቆቅልሽ መፍታት ነው። ሰልሀዲን ሰዒድ ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት ማጋጠሙ ሳቢያ በሂደት ለቡድኑ የግብ ማግባት ጥያቄ ምላሽ ይዞ የመጣው የአቤል ፣ ጌታነህ እና ጋዲሳ ጥምረት ሳልሀዲን ሰዒድ ከጉዳት በማገገሙ የተነሳ ከመሀል አንድ ተጫዋች ሲቀነስ ይስተዋላል። ምንም እንኳን ሳልሀዲን ሰዒድ ሀገሪቱ አለኝ ከምትላቸው ምርጥ አጥቂዎች አንዱ ቢሆንም በተደጋጋሚ ጉዳት ከማስተናገዱ አንፃር በሂደት እየተብላላ ጥሩ ግስጋሴ ላይ የነበረውን የአጥቂ መስመር ላይ የተጫዋቾች ለውጥ ማድረግ ከባድ ዋጋ እንዳያስከፍል ያሰጋል። ይህን ሁኔታ ለመፍታት አሰልጣኙ ጌታነህ ከበደ ከተፈጥሯዊ የ9 ቁጥር ሚናው ወደ ኃላ ተስቦ እንዲጫወት ሲደረግ የተስተዋለ ይህ ለዘመናት ሰልሀዲንና ጌታነህን በአንድነት ማሰለፍ አይቻልም ለሚለው መላ ምት መፍትሔ ይሰጥ ይሆን? የሚለው በሁለተኛው ዙር የሚታይ ነው።
የቡድኑ አጠቃላይ የተጫዋቾች የማገገም ሒደት (Recovery) እና ከጉዳት መልስ ያለ የተጫዋቾች አጠቃቀም በራሱ መፈተሽ የሚገባው ስለመሆኑ ተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት እና ከጉዳት መልስ ዳግም ወደ ሜዳ ለመመለስ የሚደረገው ጥድፊያ አንዱ ማሳያ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው አስቻለው ታመነ ጉዳቱ በቂ ጊዜ ተወስዶ ማገገም ሲገባው እንዲሁም በተደጋጋሚ ሳልሀዲን ሰዒድ ከተደጋጋሚ ጉዳት መልስ በፍጥነት ወደ ሜዳ የተመመለሱባቸው ሁኔታዎች ከጥቅሞቻቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዘኑ ነበሩ። ቡድኑ ከነበረበት ጫና አንፃር ተጫዋቾቹን ወደ ሜዳ በፍጥነት ለመመለስ የነበረው ጉጉት ከግምት ውስጥ ቢገባም ጥድፊያው በድጋሚ ተጫዋቾቹ ጉዳታቸው እንዲያገረሽ ሲያደርግ ተመልክተናል። በተጨማሪም በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ረዘም ባለ ጊዜ ጉዳት ያጣው ቡድኑ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጥያቄ የሚነሳበት አጠቃላይ የህክምና ክፍልም መፈተሽ ቡድኑ ከፍ ባለ ደረጃ እየተፎካከረ ለማስቀጠል ወሳኝ ነው።
ሌላኛው በመጀመሪያ ዙር የቡድኑ ችግር የነበረው አጥቂዎቹ የሚፈልጉትን የመሮጫ ክፍተት ከተከላካይ መስመራቸው ጀርባ ከሚተዉ ቡድኖች አንፃር ሲቸገር ባይስተዋልም ወደ ኃላ ተሰብስበው የሚከላከሉ ቡድኖችን ለማስከፈት በጣሙን ተቸግሮ ይስተዋላል። መሰል አቀራረቦች በተለይ በሁለተኛው ዙር ውድድሩ እየከረረ ሲመጣ በተደጋጋሚ ማጋጠሙ ስለማይቀር የማስከፈቻ መንገዶች ላይ ቡድኑ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል።
በሁለተኛ ዙር ምን ይጠበቃል?
ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረበት 1990 ወዲህ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ከሊጉ ክብር ተራርቆ የማያውቀው ቡድኑ ለሦስተኛ ዓመት ከዋንጫ ላለመራቅ ከፍተኛ ትግል ይጠብቀዋል።
እንዳለፉት ሁለት ዓመታት ሁሉ ጠንካራ የመከላከል ሪከርድ ያለው ቡድኑ ዘንድሮ ለዋንጫው እስከ መጨረሻው በሚያደርገው ትግል ውስጥ ላለፉት ሁለት ዓመታት ይቸገርበት የነበረውን ወሳኝ ግብ አግቢዎችን በተደጋጋሚ ጉዳት የማጣትና የአቋም መዋዠቅ የማይከሰት ከሆነ ለዋንጫው የተሻለ እድል ያላቸው ናቸው።
የ1ኛ ዙር ኮከብ ተጫዋች
ኤድዊን ፍሪምፖንግ፡ ቡድኑ ውጤቱ በተሻሻለባቸው የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ጌታነህ ከበደ፣ አቤል ያለው እና ጋዲሳ መብራቴ ድንቅ እንቅስቃሴ ቢያሳዩም ከዓመቱ መጀመር አንስቶ በወጥነት ቡድኑን ያገለገለው ጋናዊው ተከላካይ ነው። ጊዮርጊስ ከአስከፊው አጀማመር አንሰራርቶ እስከ ሰንጠረዡ አናት መቆናጠጥ ባለው ጉዞ ውስጥ ከጠንካራው የመከላከል አደረጃጀት ጀርባ ያለው ቁልፉ ሰው ይህ ጋናዊ የመሐል ተከላካይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ጨዋታዎች ተጀምረው እስኪጠናቀቁ በላቀ ንቃት የሚጫወተው ይህ ጋናዊ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች እና በአየር ላይ ኳሶች የሚቀመስ አይደለም። በቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር በአሰልጣኙ ሁሌም ቢሆን ተቀዳሚው ተመራጭ የሆነው ፍሪምፖንግ አጣማሪዎቹ ቢቀያየሩም በፍጥነት በመላመድ ቡድኑን ወጥነት ባለው መልኩ እያገለገለ ይገኛል።
ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች
አብርሃም ጌታቸው፡ ምንም እንኳን የተትረፈረፈ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ባሉት ቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ በቂ የመሰለፍ እድል ማግኘት በተለይ እንደ አብርሃም ላሉ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾች ከባድ ቢሆንም ወደ ሜዳ በገባባቸው እጅግ ውስን ደቂቃዎች ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች ስለመሆኑ ምልክቶችን አሳይቷል። ቡድኑ ሲዳማ ቡናን በሰፊ የግብ ልዩነት ሲረታ በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ለተቆረችው የአቡበከር ሳኒ ግብ አመቻችቶ ማቀበል የቻለው አብርሃም ከፊቱ ብሩህ ጊዜ ያለ ይመስላል።
© ሶከር ኢትዮጵያ