ቶጓዊው አጥቂ ወደ ሰበታ ከተማ አምርቷል

ላለፉት ቀናት ከሰበታ ከተማ ጋር ልምምድ ሲሰራ የቆየው ጃኮ አረፋት ዛሬ ለክለቡ ፊርማውን አኑሯል።

በዓመቱ መጀመርያ ካመራበት ወልቂጤ ከተማ ጋር በስምምነት ከተለያየ በኋላ ላለፉት ቀናት ከሰበታ ከተማ ጋር ልምምድ እየሰራ የቆየው ጃኮ አረፋት ከቡድኑ ጋር ለመቆየት ፊርማውን ማኖሩን ተከትሎ በፍፁም ገብረማርያም ጫንቃ ወድቆ የነበረው የሰበታ ከተማን የግብ ማግባት ኃላፊነት ይጋራል ተብሎ ይጠበቃል።

በመርላን የተባለ ክለብ የእግር ኳስ ሕወቱ ከጀመረ በኃላ በአሸንቲ ጎልድ፣ ጋዝያንቴስፖር፣ አል አረቢ፣ ኢንተርባኩ እና ሌሎች በርካታ ክለቦች መጫወት የቻለው ይህ አጥቂ በ2009 የጎርጎርያን አቆጣጠር ሞናናን ለቆ ነበር ወደ ሀዋሳ ከተማ መፈረም የቻለው። ከዛ በኋላም በወላይታ ድቻ ፣ ባህርዳር ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ መጫወት ችሏል።

በመጀመርያ ዓመት የኢትዮጵያ ቆይታው ለኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ተፎካካሪ የነበረው ጃኮ ለሀገሩ ቶጎ ብሄራዊ ቡድን በሁለት ጨዋታዎች ተሰልፎ ተጫውቷል።

©ሶከር ኢትዮጵያ