ወልዋሎ የአራት ተጫዋቾች ዝውውር አጠናቀቀ

በዝውውር መስኮቱ በርካታ ተጫዋቾች ያስፈርማሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ወልዋሎዎች የአራት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀዋል።

ከፈረሙት መካከል ዐመለ ሚልኪያስ አንዱ ነው። መቐለን ለቆ ባለፈው ዓመት ወደ አዳማ ከተማ ያመራው ዐመለ ከአዳማ ጋር በመለያየት ዘደ ቢጫ ለባሾቹ አምርቷል። ከዚህ ቀደም በአርባምባጭ ከተማ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና መጫወት የቻለው አማካዩ ጥቂት የአማካይ አማራጮች ላላቸው ወልዋሎዎች ጥሩ ግብአት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላው ቡድኑን የተቀላቀለው አማካይ ሃይማኖት ወርቁ ነው። ከዚህ ቀደም ለባህር ዳር ከተማ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ ሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ መጫወት የቻለው ይህ አማካይ ከድቻ ከለቀቀ በኋላ ከክለብ ነፃ የነበረ ሲሆን ከወራት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመለስ ይሆናል።

ሦስተኛው የቡድኑ ፈራሚ ዐወል አብደላ ነው። ከቀናት በፊት ከወላይታ ድቻ ጋር በስምምነት የተለያየው የቀድሞው የመከላከያ እና ሲዳማ ቡና ተከላካይ የሳሳውን የቢጫዎቹ ተከላካይ መስመር ለማሻሻል ወደ ቡድኑ አምርቷል።

አራተኛው ወደ ወልዋሎ ያመራው ተጫዋች ያሬድ ብርሀኑ ነው። ከመቐለ ጋር ውሉን ማጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ለማምራት ተቃርቦ የነበረው የመስመር ተጫዋቹ ወደ ወልዋሎ ማምራትን ምርጫው አድርጓል።

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ