የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር በባለፈው ሳምንት መጀመሪያ መጠናቀቁን ተከትሎ ክለቦች በተናጥል መዳሰሳችንን ቀጥለን የመጀመሪያውን ዙር በ13 ነጥብ ግርጌውን ይዞ ያጠናቀቀው ሀዲያ ሆሳዕናን የአጋማሽ ጉዞ ተመልክተናል።
የመጀመሪያ ዙር ጉዞ
በ2011 ከከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተቀላቀሉት ሦስት ቡድኖች አንዱ የሆነው ሀዲያ ሆሳዕና ለሊጉ አዲስ አይደለም። በ2008 ፕሪምየር ሊግ የተሳተፈው ሆሳዕና በወቅቱ ያሳደጉት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰን ወደ አሰልጣኝነት በማምጣት በከፍተኛ ሊጉ ምድብገሐ ስኬታማ የውድድር ጊዜ በማሳለፍ ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ በድጋሚ ቡድኑን ወደ ሊጉ መልሰውታል። በዚህም ቡድኑ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰን በዋና አሰልጣኝነት በማስቀጠል ነበር የውድድር ዓመቱን ጉዞውን የጀመረው። ዋና አሰልጣኙን ቀድሞ የለየው ሆሳዕና ወደ ዝውውር ገበያው ቀድሞ በመግባት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ የቻለ ሲሆን ስኬታማ ዝውውሮች ከፈፀሙት ቡድኖች ተርታ ቅድሚያ ሊያሰጠው የሚችል ክረምት ማሳለፉን መናገር ይቻላል።
ቡድኑ ከውድድሩ መጀመር ቀናት በፊት ሊጉን በሚመራው ዐቢይ ኮሚቴ ሜዳው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ለማከናወን ብቁ መሆኑ መቻሉ በመረጋገጡ ከሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ በሜዳው ጨዋታውን ማድረግ ጀምሯል። ገና ከጅምሮ የ2011 ቻምፒዮኑ መቐለ 70 እንደርታን ትግራይ ስታዲየም ላይ በመግጠም ሽንፈት ቢስተናግድም ጠንካራው መቐለን መፈተኑን ተከትሎ በቀጣይ ጨዋታዎች ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆን ይችላል ተብሎ ቢጠበቅም በሁለተኛ ሳምንት በሜዳው ከሀዋሳ ጋር በመጨረሻ ደቂቃ በቆጠረ ጎል ነጥብ ተጋርቶ ሲወጣ በተከታታይ በድሬዳዋ እና ፋሲል ከነመመ ከሜዳው ውጪ ተሸንፎ በሜዳው ከባህር ዳር ነጥብ በመጋራት እንዲሁም ከሜዳው ውጪ በኢትዮጵያ ቡና አስከፊ የ5-0 ሽንፈት አስተናግዶ እጅግ ደካማ የሆነ አጀማመር አድርጓል። ይህም ቡድኑ በ2008 እንደነበረው ተሳትፎ በደካማ አቋም ሊጉን በቶሎ ሊሰናበት ይሆን የሚሉ ጥያቄዎች እንዲነሱበት አድርጎ ነበር።
ከ7ኛው ሳምንት ጀምሮ ቡድኑ በተከታታይ ጨዋታዎች መነቃቃት በማሳየት ከገባበት ቀውስ ለማገገም ጥረት አድርጓል። በዚህም ሲዳማ ቡናን የሜዳው፤ በወቅቱ ጠንካራ አቋም ላይ የነበረው ወልዋሎን ደግሞ ከሜዳው ውጪ በመርታት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ተለያይቶ በሦስቱ ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ ሰብስቦ ከፍተኛ መሻሻል ማሳየት ችሎ ነበር። ሆኖም ወቅታዊው መነቃቃት ከሦስት ጨዋታዎች በላይ ሳይሻገር በተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሽንፈትን ቀምሷል። ይባስ ብሎ በ11ኛ ሳምንት በሜዳቸው በወልቂጤ ሽንፈት ባስተናገዱበት ወቅት በተከሰተ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ሁለት ጨዋታ መቀጣቱ ከውጤት መጥፋቱ ጋር ተደማምሮ ሁኔታዎችን አስቸጋሪ ያደረጋቸው ሲሆን ከወልቂጤው ሽንፈት በኋላ የአሰልጣኝ ሹም ሽር ለማድረግ ተገደዋል።
ከአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ስንብት በኋላ በሊጉ ልምድ ያላቸው ፀጋዬ ኪዳነማርያምን የቀጠረው ክለቡ በ12ኛው ሳምንት በሰበታ ከተማ ከሜዳው ውጪ ከተሸነፈበት ጨዋታ በመቀጠል በድቻ ሽንፈት ቢገጥመውም መጠነኛ መሻሻሎችን በማሳየት ከስሑል ሽረ ከሜዳው ውጪ ነጥብ ተጋርቶ በሜዳው (በቅጣት ምክንያት ሀዋሳ ላይ) ጅማ አባ ጅፋርን በመርታት ከግርጌው ባይላቀቅም ከበላዩ ካሉት ቡድኖች የነበረውን ልዩነት አጥብቦ ዙሩን ማጠናቀቅ ችሏል።
የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር
ቡድኑ በ2011 በከፍተኛ ሊጉ ተወዳዳሪ የነበረ በመሆኑ የውጤት ንፅፅር ማድረግ አስቸጋሪ ነው።
የቡድኑ አቀራረብ
በከፍተኛው ሊግ ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርግ ቡድን የሰሩት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ለዚህ አጨዋወት እንዲረዳቸው በክረምቱ ጥሩ ጥሩ አማካይ ተጫዋቾችን በማስፈረም የውድድር ዓመቱን ጀምረዋል። በአመዛኙ 3-5-2 እና 4-2-3-1/4-3-3 አሰላለፍን የሚመርጠው ቡድኑ ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ የሜዳውን ስፋት በመጠቀም የመስመር ላይ ሽግግር በማድረግ ለማጥቃት የሚሞክር ቡድን ሲሆን ግዙፎቹ አጥቂዎች ቢስማርክ አፒያ እና ቢስማርክ ኦፖንግ ላይ ያነጣጠሩ ተሻጋሪ ኳሶች የቡድኑ ዋንኛ መገለጫ ነበሩ። ለዚህም በአማካይ ስፍራ በኳስ ስርጭታቸው ጥሩ የሆኑት ይሁን እንደሻው እና አፈወርቅ ኃይሉን የሚጠቀም ሲሆን ታታሪዎቹ ሱራፌል ዳንኤል እና ሄኖክ ከርፊጮ በክንፍ ተጫዋችነት (wibg back) ወሳኙን ሚና ይጫወታሉ።
በሒደት ከውጤት መጥፋት ጋር በተያያዘ በርካታ አቀራረቦችን የሚጠቀመው ቡድኑ ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ ያደረገው ጨዋታ ጥቂት ቢሆንም አሰልጣኝ ፀጋዬ 4-4-2 ምርጫቸው የማድረግ ወደ ጎን እና ወደ ኋላ ጥሩ ከኳስ ውጪ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ሁለቱን ቢስማርኮች ከፊት አጣምረው ወደ መሐል ሜዳ ጠበብ ያለ የአማካይ ጥምረት በመፍጠር የውድድር ዘመኑን አጋምሰዋል።
በተጫዋቾች ምርጫ ረገድ በግብ ጠባቂ ስፍራ ታሪክ ጌትነት በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ላይ ሲሰለፍ ኢኳቶርያል ጊኒያዊው አቤር ኦቮኖ ቦታውን ተረክቦ በአመዛኞቹ ጨዋታዎች ላይ ጎሉን ጠብቋል።
በተከላካይ ስፍራ ቡድኑ እንደሚመርጠው አቀራረብ በየጊዜው የሚለዋወጥ ሲሆን በሦስት የመሐል ተከላካዮች ሲቀርቡ ፀጋዬ/በረከት – አዩብ – ደስታ በተደጋጋሚ የመሰለፍ እድሉን አግኝተዋል። በአራት ተከላካዮች በሚሰለፉበት ወቅት ደግሞ ፀጋዬ-አዩብ-ደስታ-ሄኖክ ቀዳሚ ተመራጮች ሆነው በአመዛኝ ጨዋታዎች ተሰልፈዋል።
በአማካይ ሥፍራ እምብዛም የማይለወጠው የይሁን እንደሻው እና አፈወርቅ ኃይሉ ጥምረት ሲሆን በ3-5-2 በሚቀርብባቸው ጨዋታዎች ከሁለት የክንፍ ተጫዋቾች እና ከአንድ የአጥቂ አማካይ (በኃይሉ ወይም አብዱልሰመድ) ጋር ጥምረት ይፈጥራሉ። በአራት ወይም በሦስት አማካይ ሲዋቀርም እንዲሁ ሁለቱ አማካዮች የቡድኑ መዋቅር እምብርት ሆነው አጋማሹን አሳልፈዋል።
በአጥቂ ስፍራ ሁለቱ ጋናዊያን አጥቂዎች ቢስማርክ ኦፖንግ እና ቢስማርክ አፒያ ጥምረት ፈጥረው የአንደኛውን ዙር አመዛኝ ጨዋታዎች ተሰልፈዋል። ሁለቱም ጎል የማስቆጠር ደመ ነፍስ የሌላቸውና የጎል ሪከርዳቸውም ያን ያህል አመርቂ ባለመሆኑ ፊት ላይ የሥልነት ችግር ቢያጋጥመውም ከአጠቃላይ ቡድኑ ጋር ያላቸው ውህደት፣ ከኳስ ውጪ ያላቸው እንቅስቃሴ እና (በተለይ አፒያ) በመከላከል ወቅት ቡድኑን የሚረዱበት መንገድ ጥሩ ነበር።
ጠንካራ ጎን
በቡድኑ የአንደኛው ዙር ጉዞ ጠንካራ የሚባለው ጎን ይህ ነው ብሎ መጥቀስ አስቸጋሪ ቢሆንም የአማካይ ክፍሉ የቡድኑ የተሻለ ጎን ነበር ማለት ይቻላል። ቡድኑ ያለ ተፈጥሯዊ የተከላካይ አማካይ መጫወቱ ተከላካይ ክፍሉ እንዲጋለጥ ቢያደርገውም የአማካዮቹ ታታሪነት፣ ጥሩ የኳስ ስርጭት ብቃት እንዲሁም የአማራጭ መብዛት በሁለተኛው ዙር ይበልጥ ማጎልበት ከተቻለ ዋንኛ የውጤታማነት ቁልፍ ሊሆን ይችላል።
የመስመር አጨዋወቱ ሌላው ሊጠቀስ የሚችል ጥንካሬ ነው። በዓመቱ የመጀመርያ ሳምንታት ከፍተኛ ብርታት በሚጠይቀውና በ3-5-2 ወሳኝ ሚና በሚጫወተው የክንፍ ተጫዋችነት የሚሰለፉት ተጫዋቾችን ብቃታቸውን አጉልተው ሊያወጡ የሚችሉበት አቀራረብ ይበልጥ መጠቀም ከተቻለ ሌላው ጠንካራ የመሆን አቅም ያለው የቡድኑ ክፍል ነው።
ደካማ ጎኖች
ምንም እንኳ በመጨረሻዎቹ ተከታታይ ጨዋታዎች መሻሻል ቢያሳይም የተከላካይ መስመሩ ደካማ እንደነበር የተቆጠሩበት ጎሎች ምስክር ናቸው። በጨዋታ በአማካይ 1.5 ጎሎች የሚቆጠርበት ሆሳዕና በአጨዋወትም ሆነ በተጫዋቾች ምርጫ ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን በመስጠት ረገድ ድክመት የነበረበት ሲሆን በተናጠል ተከላካዮቹ በተለይ ከፈጣን አጥቂዎች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ያላቸው ቅልጥፍና እንዲሁም እርስ በርስ ያላቸው ውህደት ጥያቄ የሚነሳበት ነው።
በራሱ ሜዳ በመደረጋቸው ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ያሳካው ሆሳዕና የተደራጀ የማጥቃት እቅድ ያለው ቡድን አለመሆኑ በሜዳው ነጥብ እንዳይሰበስብ አድርጎታል። ከሜዳው ውጪ እንደሌሎች የሊጉ ቡድኖች ውጤት ይዞ ለመውጣት የሚጥረው ቡድን በሜዳው ሲጫወት በተቃራኒው ሌሎች ቡድኖችም ክፍተት በቀላሉ በማይሰጥ ሁኔታ የሚከላከሉ በመሆኑ የመከላከል አጨዋወትን የማስከፈቱ መላ መዘየድ ላይ በአንደኛው ዙር ድክመት ተስተውሎበታል።
ዲሲፕሊን ሌላው የቡድኑ ደካማ ጎን ነው። ከፍተኛ የማስጠንቀቂያ ካርድ ከተመለከቱ ቡድኖች አንዱ የሆነው ሆሳዕና ተጫዋቾቹ በውሳኔዎች ላይ የሚያሰሙት ተደጋጋሚ ቅሬታ እና ከዳኛ ጋር የሚፈጥሩት ጭቅጭቅ ትኩረታቸውን ሲበታትነው ይስተዋላል። በሁለተኛው ዙር እያንዳንዱን ጨዋታ በጥንቃቄ መጫወት ለሚገባው ሀዲያ ሆሳዕና በዲሲፕሊን ምክንያት ተጫዋቾችን ማጣት ነገሮችን ሊያከብድበት ይችላል።
በሁለተኛ ዙር ምን ይጠበቃል?
ለሁለተኛ ዙር ቡድኒን ከወዲሁ የማጠናከር ሥራ የጀመረው ቡድኑ ክፍተቱን ሊደፍኑ የሚችሉ ጥሩ ዝውውሮችን እያደረገ እንደመሆኑ ጠንክሮ እንደሚመጣ ይጠበቃል። አሰልጣኝ ፀጋዬ በጉልህ በሚታዩት የተከላካይ አማካይ እና የአጥቂ ስፍራ ላይ ያስጀረሟቸው ተጫዋቾች ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚቀርቡ ናቸው። ባለ ብዙ ልምዱ ተስፋዬ አለባቸው ቡድኑን መቀላቀሉ የመሐል አማካዮቹ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ከመርዳት ባሻገር ለተከላካይ ክፍሉ ጥሩ ሽፋን እንደሚሰጥ ይጠበቃል። በአጥቂ ክፍሉ ላይም የሳሊፍ ፎፋና መምጣት ከሁለቱ ጋናዊያን ታታሪ አጥቂዎች ጥሩ ጥምረት እንዲፈጥር የሚያደርግና በአምናው ብቃቱ ላይ የሚገኝ ከሆነ የጎል ማስቆጠር ችግራቸውን ሊቀርፍ የሚችል ነው። በተቃራኒው በተከላካይ ሥፍራ ቡድኑ የሚቸገርበትን ክፍተት በአጨዋወት ለማሻሻል ካልጣሩ የአንጋፋው ቢንያም መምጣት ሰፊ ለውጥ ይፈጥራል ተብሎ አይጠበቅም።
የ1ኛ ዙር ኮከብ ተጫዋች
ይሁን እንደሻው፡ የአማካይ ሥፍራ ተጫዋቹ የቡድኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ማዕከል ነው ማለት ይቻላል። በረጅሙ የሚጥላቸው ኳሶች፣ የኳስ ስርጭቱ እና የቡድኑን ሚዛን ለመጠበቅ የሚያደርገው ጥረት በአንደኛው ዙር በአንፃራዊነት የቡድኑ ኮከብ እንዲሆን አድርጎታል። አሰልጣኝ ፀጋዬ ተጫዋቹ ይበልጥ አቅሙን አውጥቶ እንዲጠቀም የሚያደርጉ ከሆነም ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ለሚያደርገው ትግል ወሳኝ ተጫዋች መሆኑ አይቀሬ ነው።
ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች
ኢዩኤል ሳሙኤል፡ ዓምና በከፍተኛ ሊጉ ቡድኑ ላስመዘገበው ስኬት ቁልፍ ሚና ከተወጡ ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ኢዩኤል ዘንድሮ እንደከዚህ ቀደሙ በርካታ ጨዋታ ላይ የመሰለፍ እድል ባያገኝም ሜዳ ላይ በነበረባቸው ጨዋታዎች ጥሩ ተንቀሳቅሷል። በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ከመጀመርያው የተሻለ የመሰለፍ እድል የሚያገኝ ከሆነ የመስመር አጥቂው የተሻለ አበርክቶ እንደሚኖረው ተስፋ የሚጣልበት ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ