የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ክለቦች ዳሰሳ – ጅማ አባ ጅፋር

ቀጣዩ ዳሰሳችን የመጀመሪያውን ዙር በ18 ነጥቦች 13 ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀውና መፍትሄ ባልተገኘላቸው አስተዳደራዊ ተግዳሮቶች እየታመሰ የሚገኘውን የጅማ አባ ጅፋር የመጀመሪያ ዙር አጠቃላይ ጉዞ ይመለከታል።


የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

በ2010 የውድድር ዘመን ከከፍተኛ ሊግ ባደጉበት ዓመት ሳይጠበቁ የሊጉ ቻምፒየን በመሆን ደማቅ ታሪክ መፃፍ የቻሉት ጅማ አባ ጅፋሮች ዓምና እና ዘንድሮ በፋይናንስ ቀውስ ታጅበው ውድድራቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።

በክረምቱ ከበርካታ ቁልፍ ተጫዋቾች ጋር የተለያየው ቡድኑ ዘግይቶም ቢሆን ጳውሎስ ጌታቸውን በዋና አሰልጣኝነት በመቅጠር የቡድኑን የጥገና ሥራ ከሌሎች ክለቦች እጅጉን ዘግይቶም ቢሆን ወደ ገበያ በመግባት ለመስራት ሞክሯል። በዚህም ጥረታቸው በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ተጫዋቾች፣ በፕሪምየር ሊጉ ልምድ ያላቸው የተወሰኑ ተጫዋቾችን እንዲሁም የውጪ ዜጎችን በማስፈረም ከነባሮች ጋር በማዋሀድ ወደ ውድድር ገብተዋል።

ዓምና በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በጅማ ስታዲየም የተከሰተ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ወደ ዘንድሮ በይደር በተላለፈ ቅጣት መሰረት በመጀመሪያዎቹ የሊጉ ሳምንታት በሜዳው ማድረግ የነበረባቸውን ጨዋታዎች በአዳማ ስታዲየም ለማድረግ የተገደዱት ጅፋሮች በመጀመሪያው ሳምንት አሰልጣኝ ጳውሎስ የቀድሞ ቡድናቸው ባህር ዳር ከተማን ገጥመው በአቻ ውጤት ሲለያዩ በሁለተኛው ሳምንት በተመሳሳይ ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለ ግብ አቻ መለያየት ችለዋል።

ከሊጉ ጅማሮ አንስቶ ችግር ያላጣው ቡድኑ እስከ 4ኛ ሳምንት ድረስ በደካማ አስተዳደራዊ ሒደት ያስፈረማቸው ሦስት የውጭ ዜጋ ተጫዋቾችን ከስራ ፈቃድ ጋር የተያያዘ ጉዳያቸው በወቅቱ ማለቅ ባለመቻሉ የእነዚሁን ተጫዋቾች ግልጋሎት ማግኘት ሳይችል የቀረበት ሒደት አግራሞትን ያጫረ ነበር።

በ5ኛ ሳምንት ቅጣታቸውን ጨርሰው ወደ አዲሱ የጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የተመለሱት ጅማዎች በአዲሱ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ይፋዊ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን በአምረላ ደልታታና ብዙዓየሁ እንደሻው ግቦች በማሸነፍ አዲሱን ሜዳ በድል ሲያሟሹ በሊጉ እንዴት ይዘልቅ ይሆን ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ሊጉ ሲጀመር ተሰግቶለት የነበረው ቡድን ግሞቶችን አፋልሶ በመጀመሪያው አምስት ሳምንት የሊጉ ጉዞ ስድስት ነጥብ በመሰብሰብ ተስፋ ሰጪን የውድድር ዘመን ጅማሮ ማድረግ ችሏል።

በ6ኛው ሳምንት ወደ አደማ ተመልሶ ከአዳማ ከተማ አቻ የተለያየው ቡድኑ በአዲሱ ሜዳው ባደረገው ሁለተኛው ጨዋታ ወልቂጤ ከተማን በመርታት በሜዳው ድል ማድረጉን በ7ኛ ሳምንት ቢቀጥልም በተከታታይ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት በሰበታ እና ወላይታ ድቻ ሽንፈትን አስተናግዷል።

የተጫዋቾች ባልተከፈለ ደሞዝ ሳቢያ ልምምድ ማቆምና መጀመር የቡድኑ መገለጫ እስኪመስል ድረስ በድግግሞሽ መሰል ሒደቶች ውስጥ ሲመላለስ የከረመው ቡድኑ የሊጉ ደካማነት በሚያንፀባርቅ መልኩ ልምምድ ሳያደርግ ቀናት አስቆጥሮ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ነጥብ ያስመዘገበባቸው ሁኔታዎች ጭምር ያስመለከተ የመጀመሪያ ዙርን አሳልፈዋል።

በማስቀጠልም በ10 እና 11ኛ ሳምንት ተከታታይ ጨዋታዎች ከስሑል ሽረና ፋሲል ከተማ አቻ የተለያየው ስብስቡ በ12ኛ ሳምንት የዓምናው ሻምፒዮን መቐለ 70 እንደርታን በመርታት የተነቃቃ ቢመስለም በመጨረሻ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱን ሲሸነፍ በ14ኛ ሳምንት ደግሞ በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን መርታት ችሏል።



ቡድኑ ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር

ዓምና በዚሁ ወቅት ቡድኑ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ውስጥ በአምስቱ አሸንፎ፤ በስድስቱ አቻ ሲለያይ በአራት ጨዋታዎች ሽንፈትን አስተናግዶ በ21 ነጥብ 9ኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል። ይህም ከዓምናው አንፃር ቡድኑ በሰበሰበው ነጥብም ሆኖ ደረጃ ዝቅ ያለበት የውድድር ዘመን እያሳለፈ ይገኛል። ዓምና 14 ግቦችን አስቆጥሮ 17 ግቦችን ያስተናገደ ሲሆን በዘንድሮ የውድድር ዘመን ቡድኑ በሊጉ ሁለተኛ ዝቅተኛ ግብ (12) በማስተናገድ በመከላከሉ ረገድ መሻሻል አሳይቷል።

የቡድኑ አቀራረብ

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በሚታወቁበት ጥንቃቄ ላይ መሰረት ባደረገ አጨዋወት የተቃኘው ቡድኑ በብዛት በ4-2-3-1/ 4-5-1 አደራደር ጨዋታዎችን የሚያደርግ ሲሆን ቡድኑ በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጭ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ኳስን ለተጋጣሚ ቡድን ለቆ በራሱ ሜዳ ላይ በመቆየት የሚሰነዘርትን ጫና በመቋቋም በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክር ይስተዋላል።

ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያደርጉት ሽግግር ቀጥተኝነት መገለጫው የሆነው ቡድኑ በተለይ በመስመር አማካይነት የሚያሰልፋቸው ኤርሚያስ ኃይሉ፣ ሱራፌል ዐወል፣ አምረላ ደልታታ እና ብሩክ ገብረአብን አስደናቂ ፍጥነት በመጠቀም ተጋጣሚዎች ለማጥቃት ነቅለው ሲወጡ በሚተዋቸው ክፍት ቦታዎችን ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።

ዓምና በስብስቡ ከነበሩ ተጫዋቾች እና በክረምቱ ከለቀቃቸው የተጫዋቾች አንፃር የስብስብ ጥራት እና ጥልቀት ችግር ያለበት ቡድኑ ተጫዋቾች በማሸጋገሽ እየተጠቀመ ይገኛል። ለማሳያነት ተፈጥሯዊ የመሐል አማካዩ ኤልያስ አሕመድ ለፊት አጥቂዎቹ ቀርቦ በተለሞዶ 10 ቁጥር እየተባለ በሚታወቀው ሚና ሲጫወት ተስተውሏል።

በተጫዋቾች ምርጫ ረገድ በግብ ጠባቂ ስፍራ የዳንኤል አጃይን መልቀቅ ተከትሎ ያስፈረመው መሐመድ ሙንታሪን በወረቀት ጉዳዮች ባላሰለፈባቸው ጨዋታዎች እድል ያገኘው ሰዒድ ሀብታሙ ድንቅ ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን ሙንታሪ የሥራ ፈቃድ ጉዳዩን ካጠናቀቀ በኋላ ከሰዒድ ጋር እየተፈራረቁ ተጫውተዋል።

በተከላካይ ሥፍራ አሰልጣኝ ጳውሎስ በመጀመርያዎቹ ሳምንታት የወንድማገኝ – መላኩ – ከድር – ኤልያስ ጥምረትን ሲጠቀሙ በሒደት ጀሚል ያዕቆብ በቀኝ መስመር ተከላካይነት እንዲሁም አሌክስ አሙዙ በመሐል ተከላካይነት ሲሰለፉ ተስተውሏል። የቡድኑ ወሳኝ ቦታ የሆነው ይህ ሥፍራ ከጥቂት ለውጦች በቀር የጊዜው የማይቀያየር መሆኑ ለጥንካሬው አስተዋፅኦ አድርጓል።

በአማካይ ስፍራ ንጋቱ ገብረሥላሴ ከሄኖክ ገምታሳ ጋር ሲጣመሩ አብርሀም ታምራት እና ኤፍሬም ጌታቸው በቦታው ላይ ሌሎች አማራጭ ሆነው አገልግለዋል። ለተከላካዩ ሽፋን ለመስጠት እና ለመልሶ ማጥቃት ወሳኝ ከሆኑት ሁለት አማካዮች ፊት ኤልያስ አሕመድ በነፃ ሚና የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲመራ በግራ እና በቀኝ አምረላ፣ ብሩክ፣ ሱራፌል እና ኤርሚያስ እንዲሁም በአንዳንድ ጨዋታዎች ጀሚል በመሰለፍ ዙሩን አገባደዋል።

ፊት ላይ በአንድ አጥቂ የሚጫወተው ቡድኑ በወጥነት በዚህ ስፍራ ላይ እስካሁን የሚጫወት ተጫዋች ያገኘ አይመስልም። በዚህ ቦታ ላይ ያኩቡ መሐመድ እና ብዙዓየሁ እንደሻውን የሚጠቀመው ቡድኑ ከእነዚህ ተጫዋቾች በሚፈልገው ልክ ግልጋሎት እያገኘ ነው ብሎ ለመውሰድ ያስቸግራል። በዚህም በአንዳንድ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ደግሞ ሁለቱንም ከአሰላለፉ በማውጣት ያለተፈጥሯዊ አጥቂ ሲጫወት ተመልክተናል።

ጠንካራ ጎን

በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እንደ መመራቱ ቡድኑ በመከላከል ረገድ ያለው አደረጃጀት ጥሩ የሚባል ነው። ቡድኑ ከተጋጣሚዎች የሚሰነዘርን ጥቃት በመመከት ረገድ ጠንካራ መሆኑን አስመስክሯል። ለማሳያነትም ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር ካደረጋቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች ላይ በሰባቱ ምንም ግብ ሳይስተናግድ መውጣት ሲችል ዝቅተኛ ጎል በማስተናገድም የሚበለጠው በመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ነው።

የተጫዋች አጠቃቀም ሌላው የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። አሰልጣኝ ጳውሎስ ያላቸውን ጠባብ ስብስብ በአግባቡ ተጠቅመው በማሸጋሸግ አንደኛውን ዙር የጨረሱበት መንገድ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጠንካራ ጎን ነው። ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ያለውንም ክፍተት ተቋቁመው በአንፃራዊነት ከተረጋጉ ቡድኖች የተሻለ ጊዜ ማሳለፋቸውም እንደ ቡድን ያላቸውን የአዕምሮ ጥንካሬ ሊያሳይ የሚችል ነው።

ደካማ ጎኖች

ከሜዳ ውጭ ባሉ አስተዳደራዊ ጉዳዮች እየታመሰ የሚገኘው ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር በበርካታ አጋጣሚዎች ቡድኑ ከክፍያ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ተጫዋቾች ልምምድ ሲያቋርጡ እንዲሁም ቡድኑ በሊጉ በተቀመጠለት መርሐግብር መሰረት ጨዋታዎችን የማካሄድ ነገር ጥርጥሬ ውስጥ የገባባቸው አጋጣሚዎች ስለመኖራቸው ይታወሳል። በዚህ ማለቂያ በሌለው አዙሪት ውስጥ የሚሽከረከረው የክፍያ ጉዳይ በተጫዋቾች ተነሳሽነትና ውጤት ላይ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ስላለው የቡድኑ አመራር ጉዳዩን በአፋጣኝ እልባት ሊሰጡት ይገባል።

ቡድኑ ከፍተኛ የስብስብ ጥልቀት ችግር ያለበት ስለመሆኑ የመጀመሪያው ዙር በደንብ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል። ቡድኑ ከወገብ በላይ ባሉ የመጫወቻ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የማጥቃት ባህሪ የተላበሱ አማካዮች ከፍተኛ እጥረት አለበት። ለማሳያነት በፊት አጥቂነት እንዲሁም በአጥቂ አማካይ ቦታ ላይ የመስመር ተከላካዮችን ጭምር ለመጠቀም የተገደደባቸው አጋጣሚዎች የተስተዋሉ ሲሆን በአንፃሩ በርከት ያሉ የመሀል አማካዮች ቢይዝም የስብስብ ጥልቀትና የተጫዋቾች አለመመጣጠን በቀጣይ ቡድኑ ሊያርመው የሚገባ ይሆናል።

ጎል የማስቆጠር ችግሩ ሌላው ደካማ ጎኑ ነው። በጨዋታ በአማካይ 0.6 ጎል ብቻ የሚያስቆጥረው ቡድኑ እንደ መከላከል ጥንካሬው ባይሆን ኖሮ ከዚህ የከፋ ደረጃ ላይ በተገኘ ነበር። በአጨዋወት ደረጃ ብዙም የጎል እድል የማይፈጥር መሆኑ እንደ ዋንኛ ምክንያት የሚቆጠር ሲሆን የሚገኙትን ጥቂት እድሎች ወደ ጎል የሚለውጡ አጥቂዎች ክፍተትም ይታይበታል። ለዚህም በአጠቃላይ ከሁለት ጎሎች በላይ ያስቆጠረ ተጫዋች አለመኖሩ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

ሌላኛው የቡድኑ ችግር የሆነው እንደየጨዋታው ሁኔታ የማይቀያየረው የቡድኑ አቀራረብ ነው። ከጥቂት ጨዋታዎች በቀር ቡድኑ በተለይ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በአዎንታዊ አቀራረብ ጨዋታዎች ተቆጣጥረው ማሸነፍ እየቻለ ለጥንቃቄ በሚሰጡት የበዛ ግምት ቡድኑ ከማሸነፍ ይልቅ አለመሸነፍ ተቀዳሚ አላማው ሲሆን ይስተዋላል።

በተጨማሪም በተለይ በመጀመሪያው ዙር የቡድኑ የተጫዋቾች የስነምግባር ጉዳይ ሌላው ትኩረት የሚሻ ነው። የዳኛን ውሳኔ በፀጋ በመበቀልና በስሜት መነዳት የሚስተዋልባቸው የቡድኑ አባላት ጉዳይ ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። ውጥረት በሚበዛበት እና ውጤቶች በቀላሉ በማይገኙበት ሁለተኛው ዙር በካርዶች እና መሰል ቅጣቶች ተጫዋቾች ማጣት ቡድኑን ዋጋ ሊያስከፍለው ይችላል።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

ቡድኑ በበርካታ አስተዳደራዊ ውጥንቅቶች ውስጥ እንደመገኘቱ ዙሩን ይዞ ያጠናቀቀበት ደረጃ መጥፎ የሚባል አይደለም። በቀጣይም ቡድኑ ችግሮቹን ፈቶ ባለው የቡድን ስብስብ ላይ የተወሰኑ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች በዝውውር መስኮቱ የሚጨምር ከሆነ በሊጉ ከመውረድ ስጋት ርቆ የመጨረስ እድል አላቸው።

ለሁለተኛው ዙር ከወዲሁ ብሩክ ገብረአብን የለቀቀው ቡድኑ በማጥቃት ተጫዋቾች ላይ የሚያሻሽሉት ተጫዋቾች ማስፈረም ይኖርበታል። በተለይ ጎል የማስቆጠር ክፍተቱን በአግባቡ የሚደፍን ሁነኛ አጥቂ ቡድኑ ይሻል።

በሁለተኛው ዙር ቡድኑ ጠንካራ ተጋጣሚዎች ከሜዳው ውጪ ይጠብቁታል። ቡድኑ ከሜዳው ውጪ የሚፈልገውን ውጤት ይዞ መመለስ ላይ ጠንካራ ቢሆንም ከፋሲል፣ መቐለ፣ ወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ ከመሳሰሉ በሜዳቸው ጠንካራ ከሆኑ ቡድኖች ነጥብ መሰብሰብ ግድ ይለዋል። 

የመጀመሪያ ዙር ኮከብ ተጫዋች

ኤልያስ አሕመድ፡ የመሐል አማካዩ ኤልያስ በተጫዋቾች እጥረት ለተጠቃው የአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ስብስብ ሁነኛ የማጥቃት መነሻ ሲሆን ይስተዋላል። ተጫዋቹ አዲሱን የአጥቂ አማካይነት ሚና በፍጥነት በመላመድ የተሻለ የውድድር ዘመንን በምዕራብ ኢትዮጵያው ቡድን እያሳለፈ ይገኛል።

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች

ሰዒድ ሀብታሙ፡ ለሦስተኛ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂነት ወደ ጅማ አባ ጅፋር በክረምቱ ያመራው ሰዒድ ለእግርኳሱ አዲስ ባይሆንም ለፕሪምየር ሊጉ አዲስ ፊት ነው። ግብ ጠባቂው በዓመቱ መጀመርያ በድንገት ያገኘውን አጋጣሚ ተጠቅሞ በዘንድሮው የጅማ አባ ጅፋር ቡድን ክስተት መሆን ችሏል። በርከት ባሉ ጨዋታዎች ላይ ጋናዊውን መሀመድ ሙንታሪን ጭምር ወደ ተጠባባቂ ወንበር ማውረድ የቻለው ሰዒድ ቡድኑን እየታደገ ይገኛል። ለሁለተኛው ዙር የቡድኑ ውጤታማነት ተስፋ ከሚጣልባቸው ተጫዋቾች መካከልም ግንባር ቀደሙ ነው።

©ሶከር ኢትዮጵያ