በሊጉ ግምገማ ወቅት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ እንዳልከፈሉ ከተገለፁት ሰባት ክለቦች መካከል ስድስቱ ለውድድር የሚያስፈልገውን ገንዘብ መክፈል በመቻላቸው እግዱ እንደተነሳላቸው ታውቋል፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዓመት የመጀመሪያው ዙር ግምገማ በተደረገበት ወቅት የፕሪምየር ሊጉ ሼር ካምፓኒ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ሰባት ክለቦችን በመጥራት ውድድር ለማካሄድ የሚጠበቅባቸውን ክፍያ እንዳልከፈሉ በመጥቀስ የስምንት መቶ ሰባ ሺህ ብር ክፍያውን እስኪፈፅሙ ድረስ ከየካቲት 21 ጀምሮ ማንኛውንም ግልጋሎት እንደማያገኙ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
ይህን ተከትሎ ስድስቱ ቡድኖች ማለትም ሰበታ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ወልዋሎ፣ ስሑል ሽረ እና ሀዲያ ሆሳዕና የሚጠበቅባቸውን ክፍያ የፈፀሙ ቡድኖች ሲሆኑ ቀሪ ክፍያ የሚቀርባቸው ቡድኖችም ክፍያቸውን ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቅ መቻላቸው ተረጋግጧል። ይህን ዘገባ እስካጠናቀርንበት ሰዓት ድረስ ክፍያ ያልፈፀመው ብቸኛው ክለብ ጅማ አባ ጅፋር መሆኑም ታውቋል። አወዳዳሪው አካል በጉዳዩ ዙርያ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ የተጠቆመ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋርም እሁድ በ16ኛው ሳምንት ባህር ዳርን እስከሚገጥምበት ጨዋታ መዳረሻ ገንዘቡን ገቢ ካላደረገ የፎርፌ ውጤት እንደሚጠብቀው ለማወቅ ተችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ