ካልተከፈለ ደሞዝ ጋር ከተያያዙ ጉዳዮች ጋር እየታገለ የመጀመሪያውን 19 ነጥቦችን ሰብስቦ 9ኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀው አዳማ ከተማ የመጀመሪያው ዙር ጉዞን በተከታዩ ፅሁፋችን የምንዳስስ ይሆናል።
የመጀመሪያ ዙር ጉዞ
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ አሰልጣኝነት መንበሩ በማምጣት እና ላለፉት ዓመታት በስብስቡ ውስጥ ከነበሩ ተጫዋቾች ብዙ ለውጥ ሳያደርግ በርከት ያሉ የመሐል አማካዮችን በማስፈረም ወደ ውድድር የቀረበው አዳማ ከተማ የሊጉን የመጀመሪያውን መርሐግብሩን ጠንካራውን ፋሲል ከተማን በሜዳው አስተናግዶ ያለ ግብ አቻ በመለያየት ነበር የጀመረው። በሁለተኛው ሳምንት ደግሞ አዲስ አዳጊው ወልቂጤ ከተማን በሜዳው ያስተናገደው ቡድን በዳዋ ሆቴሳ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ቢያሳካም ከ3ኛ እስከ 6ኛ ሳምንት ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ከሰበታ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ፣ ስሑል ሽረ እና ጅማ አባጅፋር ጋር በአቻ ውጤት ሊያጠናቅቅ ችሏል።
በ7ኛ ሳምንት ከሜዳቸው ውጭ በመቐለ 70 እንደርታ የመጀመሪያ ሽንፈታቸውን ሲያስተናግዱ በአንድ ሳምንት ልዩነት በድሬዳዋ ከተማም የተሸነፉበት ሒደት የሚዘነጋ አይደለም። በተለይም ከድሬዳዋው ጨዋታ በፊት በነበሩት ቀናት ባልተከፈለ ደሞዝ ምክንያት ልምምድ ሳይሰሩ ቆይተው ይባስ ብሎ ከጨዋታው ሰዓታት ሲቀረው ወደ ድሬዳዋ አቅንተው በጠባብ ውጤት የደረሰባቸው ሽንፈት አግራሞትን ያጫረ ነበር።
ከድሬዳዋው ሽንፈት መልስ በነበሩ ተከታታይ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት ቡድኑ በክለቡ አመራር በተከፉት ደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ ድጋፍ ታግዘው ሆሳዕናን ቢረቱም በቀናት ልዩነት በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ግብ ከባህር ዳር አንድ ነጥብ ይዘው ከመመለስ ተሰናክለዋል። በቀጣዩ 12ኛ ሳምንት መርሐግብር ደግሞ ከአስደናቂ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ኢትዮጵያ ቡናን 3-0 መርታት ችለዋል።
በኢትዮጵያ ቡናው ድል የተነቃቁ የመሰሉት አዳማዎች ወደ ሀዋሳ አቅንተው ከሲዳማ ቡና ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገው 3-2 በሆነ ጠባብ ውጤት ቢሸነፉም በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት ወልዋሎን ረተው በመጨረሻ ሳምንት መርሐግብራቸው ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከሜዳቸው ነጥብ ተጋርተው የመጀመሪያ ዙሩን በ9ኛ ደረጃ ለማጠናቀቅ በቅተዋል።
የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር
ከዓምና አንፃር በበርካታ መመዘኛዎች ደካማ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው ቡድኑ ዓምና በዚህ ወቅት ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች በአምስቱ አሸንፎ በሰባት ጨዋታዎች አቻ እንዲሁም በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ተሸንፎ በ22 ነጥቦች 6ኛ ደረጃን ይዞ ዙሩ ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ወቅትም 14 ጎሎች አስቆጥሮ አስር ግቦች ስለማስተናገዱ ቁጥሮቹ ያሳያሉ። ዘንድሮ ቡድኑ በ3 ዝቅ ያለ ነጥብ አስመዝግቦ በሁለት ዝቅ ያለ ጎል ሲያስቆጥር የተቆጠረበት ጎል ግን በአንድ ዝቅ ብሏል።
የቡድኑ አቀራረብ
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በአመዛኙ 4-2-3-1 እና 3-5-2 አደራደርን ምርጫቸው አድርገው አንደኛውን ዙር የተጠቀሙ ሲሆን በጥልቀት መከላከል እና ከወገብ በላይ የሚገኙ ፈጣን ተጫዋቾችን ብቃት ያማከለ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት መገለጫቸው ነበር። አሰልጣኙ ለወትሮም ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሚሰጡ በመሆኑ ከተከላካዮች ፊት በርከት ያሉ አማካዮችን የሚጠቀሙ ሲሆን በተለይ ከሜዳቸው ውጪ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ከኳስ ጀርባ መሆንን ያዘወትራሉ። በዚህ ተመራጭ አቀራረባቸው በ3-5-2 ሲቀርቡ የክንፍ ተጫዋቾች፣በ4-2-3-1/4-3-3 ሲቀርቡ ደግሞ ከፊት የሚሰለፉት ተጫዋቾች ትጋት እና ፍጥነት ዋንኛ መሳርያቸው ነበር።
በተጫዋቾች ምርጫ በኩል አሰልጣኙ በግብ ጠባቂነት ቶጎዊው ጃኮ ፔንዜ እና ደረጀ ዓለሙን እያፈራረቁ ሲጠቀሙ በመሐል ተከላካይ ሥፍራ ላይ እንደሚመርጡት አቀራረብ ቢለያይም በአመዛኙ ጨዋታዎች ላይ ከምኞት ደበበ፣ መናፍ ዐወል እና ቴዎድሮስ በቀለ አንዱን በማሳረፍ (በ4 ተከላካዮች ሲጫወቱ) አልያም ሁሉንም በአንድ ላይ (በ3 ተከላካይ ሲጫወቱ) ይጠቀማሉ። የመሐል ተከላካዮቹ በአየር ላይ ኳሶች ወቅትም ሆነ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት በቀላሉ የማይበገሩ ሲሆን በመስመር ተከላካይነት የሚጠቀማቸው ሁለቱ ሱሌይማኖች (ሱሌይማን ሰሚድ እና ሱሌይማን መሐመድ) የመስመር አማካዮችን በማጥቃቱ ወቅት የሚረዱበት መንገድ በጥሩነቱ የሚጠቀስ ነው።
ከአራቱ ተከላካዮች ፊት ተመሳሳይ ሚናን መወጣት የሚችሉ ሁለት ተጫዋቾችን በአንድነት በመሐል አማካይነት የሚጠቀመው ቡድኑ እነዚህን ተጫዋቾች መጠቀሙ የመከላከል ጥንካሬውን ሲጨምርለት በማጥቃቱ ረገድ ግን በውስን ሰዎች ላይ ጥገኛ እንዲሆንም አድርጎታል። ቡድኑ አልፎ አልፎ በአምስት ወይም በሦስት አማካዮች በሚጫከትበት ወቅት ከነዓን ማርክነህ / ፉአድ ፈረጃን ሲጠቀም የቡድኑን የፈጠራ አቅም ሲሻሻልም ይስተዋላል።
ከፊት አጥቂዎቹ ጀርባ ሦስቱ የአጥቂ አማካዮች በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ላይ ለተመረኮዘው የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ከፍ ያለ ሚናን ይወጣሉ። በተለይም በሁለቱ መስመሮች አድልተው የሚጫወቱት በረከት ደስታ እና ቡልቻ ሹራ ፍጥነት ለተጋጣሚዎች እጅግ ፈታኝ ሆኖ ቀጥሏል። በተመሳሳይ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ከፊት ሆኖ የሚመራው አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ ከተከላካይ ጀርባ በሚገኘው ጥልቀት የሚጣልለትን ኳስ በመጠቀም ጥቃቶች የማሳለጥ እና ግብ የማስቆጠር ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
ጠንካራ ጎን
በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ አወቃቀር ያለው ቡድኑ የሊጉ ሦስተኛው ጥቂት (13) ግብ የተቆጠረበት ቡድን ነው። በመከላከል ወቅት በተለይ መሐል ለመሀል ለሚሰነዘሩ የተጋጣሚ ጥቃቶች ጠጣር የሆነው ቡድኑ መከላከሉ በዋነኝነት በጥንካሬነት የሚጠቀስ ነው። አሰልጣኙ በመከላከል ላይ ያላቸው እምነት፣ የመከላከል ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾች በብዛት መሠለፍ እና በጋር በርካታ ጨዋታ በመሰለፍ የሚመጣ ውህደትና መረጋጋት ለቡድኑ የኋላ ክፍል ጥንካሬ ትልቅ ድርሻን ይወስዳሉ።
ሌላኛው የቡድኑ ጥንካሬ ተብሎ የሚጠቀሰው ከወገብ በላይ የሚገኙት የቡድኑ ተጫዋቾች በማጥቃት ሽግግር ወቅት ያላቸው አስደናቂ ፍጥነት ለተጋጣሚ ቡድኖች ለመቋቋም እጅግ ፈታኝ ሲሆን ይስተዋላል። በረከት ደስታ እና ቡልቻ ሹራ በግሩም ታታሪነት እና ፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል በቀላሉ የሚደርሱ ሲሆን በሊጉ በመስፈንጠር አቅሙ ተወዳዳሪ ከሌለው ዳዋ ሆቴሳ ጋር የፈጠሩት ጥምረት ይበልጥ እንደ አጨዋወት ድጋፍ ቢያገኝ ለሊጉ ቡድኖች እጀሰግ ፈታኝ መሆን የሚችል ነው።
ደካማ ጎን
የቡድኑ ዋነኛ ችግር ከሚባሉት ጉዳዮች አንዱ ለተጋጣሚዎች የበዛ ክብር በመስጠት ለሁሉም ቡድኖች በተመሳሳይ የጥንቃቄ አጨዋወት መቅረቡ ቡድኑን በእጅጉ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል። ቡድኑ ከወገብ በላይ ካሉት የተጫዋቾች ጥራት አንፃር ራሳቸውን እንዲገልፁ እድሉን ሲያገኙ ለተጋጣሚ ምን ያህል አደገኛ እንደሚሆኑ በመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ የታየ ቢሆንም አሰልጣኙ ግን ይህን ሂደት በቀጣይነት ከመከተል ይልቅ በጣም በአሉታዊ አቀራረብ የተጫዋቾች ራሳቸውን የመግለፅ አቅምን በሚገድብ አጨዋወት መቀጠልን ምርጫቸው ማድረጋቸው ቡድኑን ዋጋ እያስከፈለ ስለሚገኝ ይበልጥ ጉዳዮ ትኩረት ተሰጥቶት ቢታረም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ይረዳዋል።
ቡድኑ ከሚከተለው ጥንቃቄ መር አጨዋወት መነሾ ተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶች በዝተውበት ይስተዋላል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች በ7ቱ በአቻ ውጤት የተለያየው ቡድኑ ለማጥቃት ጥቂት ድፍረት ማሳየት ቢችል ምናልባትም ከመሪዎቹ ተርታ የሚያሰልፈውን ውጤት ባሳካ ነበር።
ቡድኑ በሜዳው የነበረው ሞገስ ከዓምና ጀምሮ እየተሸረሸረ የመጣ ይመስላል። ቡድኖች አዳማን ለመግጠም ወደ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲመጡ እንደቀደሙት ጊዜያት ፈርተው የምጣታቸው ነገር እየተሸረሸረ የመጣ ሲሆን ምንም እንኳን በሜዳው ሽንፈት ባያስተናግድም ተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶች ማስመዝገቡ የቡድኑን የሜዳ ላይ ተጠቃሚነት ጉዳይ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ የከተተው ይመስላል።
አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሌላው የቡድኑ ደካማ ጎን ነው። ከደሞዝ ጋር በተገናኘ በተደገማሚ ልምምዶች ሲያቋርጥ የሚታየው ቡድኑ ሙሉ ትኩረቱን በሜዳ ላይ እንዳያደርግ እክል ፈጥሮበታል።
በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?
አስቸጋሪውን ወቅት መጥፎ በማይባል ውጤት ያመለጠው ቡድኑ ወጥ ወደሆነ የውጤት ጎዳና ለመሸጋገር ከሜዳ ውጪ ያለውን ችግር መቅረፍ ይኖርበታል። ምናልባትም በነገው ዕለት ከዩናይትድ ቤቨሬጅስ ጋር የሚፈረመው የስፖንሰርሺፕ ስምምነት የፋይናንስ ችግሩን በማቃለል ትኩረቱን ቡድኑን ወደማሻሻል እንደሚያሸጋግር ይጠበቃል።
ጥቂት ተጫዋቾችን ቢለቅም አሁንም የተሟላ ስብስብ ባለቤት በመሆኑ አሰልጣኝ አሸናፊ በአግባቡ ስብስቡን በመጠቀም እና አቀራረባቸው ላይ የሚታየውን ጥንቃቄ በመቀነስ በሁለተኛው ዙር የተሻሻለው አዳማ ከተማን ማስመልከት ይጠበቅባቸዋል።
የመጀመሪያው ዙር ኮከብ ተጫዋች
ዳዋ ሆቴሳ፡ በግለሰቦች ላይ ጥገኛ በሆነው የማጥቃት እንቅስቃሴ መሪ ተዋናይ የሆነው ዳዋ ለቡድኑ ውጤት ማማር የእሱ ሚና እጅግ የጎላ ነው። የቡድኑ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ዳዋ ከቆሙ ኳሶችም ሆነ በእንቅስቃሴ በሚገኙ የግብ እድሎችን በመቀየር ረገድ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን ከጉዳት ነፃ ከሆነ በሁለተኛው ዙር የቡድኑ ሁነኛ ሰው ሆኖ እንደሚቀጥል እርግጥ ነው።
ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች
መናፍ ዐወል፡ ግዙፉ ተከላካይ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በተሻለ እያገኘ የሚገኘውን እድል ተጠቅሞ ስሙን እየተከለ ይገኛል። ከቁመቱ ግዝፈት በማይጠበቅ መልኩ ቀልጣፋ የሆነው መናፍ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች እንዲሁም አየር ላይ ኳሶች ወቅት ያለው ከእድሜው የበሰለ የውሳኔ አሰጣጥ እጅግ አስገራሚ ናቸው። ለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በአሁን ወቅት በስብስባቸው ከሚተማመኑባቸው ተጫዋቾች ከቀዳሚው ተርታ የሚመደበው መናፍ ይበልጥ ራሱን እያሻሻለ ይገኛል።
© ሶከር ኢትዮጵያ