በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ሲካሄዱ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኤሌክትሪክ አሸንፈዋል። አዳማ ከተማ ደግሞ በሜዳው ነጥብ ጥሏል።
መከላከያ ሜዳ ላይ ባለሜዳው መከላከያ ንግድ ባንክን ገጦሞ 1ለ0 ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ከቅብብል አልያም ከተሻጋሪ ኳስ ወደ አጥቂዎቹ ሲጣሉ በነበሩ አጋጣሚዎች ጫናን ለማሳደር ሞክረዋል፡፡ በተለይ ጥቅጥቅ ያለው በብርቱካን ገብረክርስቶስ እና ትዕግስት ያደታ የሚመራው የባንኮች የመሀል ሜዳ ወደ ሽታዬ እና ረሂማ ላይ ላነጣጠረው የማጥቃት ሂደታቸው ምቹዎች ነበሩ፡፡ ሽታዬ ሲሳይ ጎልታ በታየችበትም ጨዋታ በግሏ ወደ ግብ ክልል በመድረስ በርካታ ጊዜዋን ያሳለፈች ሲሆን 13ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል ፍጥነቷን ተጠቅማ ወደ ግብ ያሳለፈችውን ረሂማ ዘርጋው አስቆጥራ ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ መረጋጋቱ በመግባት በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ንግድ ባንክ ሳጥን በተወሰነ መልኩ ለመጠጋት ሙከራን አድርገዋል፡፡ በተለይ ከቀኝ መስመር ወደ መሀል እየገባች በጥረቷ መከላከያን አቻ ለማድረግ ስትጥር የነበረችሁ አረጋሽ ካልሳ ሁለት ጊዜ ከሳጥን ውጪ የመታችሁ እጅግ ጠንካራ ኳሶች አንደኛው የላይኛው የግቡ ብረት ሲመልስባት ሌላኛዋን ደግሞ ንግስቲ መዐዛ እንምንም አውጥታዋለች፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መከላከያዎች ወደ ተመጣጠነ እንቅስቃሴ ራሳቸውን መልሰው ልክ እንደ ንግድ ባንክ የመጀመሪያው አጋማሽ የአጠቃቅ ሲስተም ለመተግበር ሙከራን ቢያደርጉም የላላ የፊት መስመር በመኖሩ ሊሳካላቸው አልቻለም በተለይ ኳስን ወደፊት ተስበው በሚጫወቱበት ወቅት ተጫዋቾች ተበታትነው ኳስን ለመቀበል ጥረት ስለሚያደርጉ እምብዛም ያለሙትን በተግባር ማዋል ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ንግድ ባንክ የመከላከያን የቅያሪ ስህተት በሚገባ ተጠቅሟል፡፡ አሰልጣኛቸውን በሀዋሳው ጨዋታ በቅጣት ያጡት ባለሜዳዎቹ የቀኝ መስመር ተከላካይዋ ዘቢብን ለውጠው ማስወጣታቸው ለሽታዬ ሲሳይ ምቹ ቦታን የፈጠረ ነበር። በዚህም ሂደት መሀል ሽታዬ በተደጋጋሚ በቀኝ በኩል በግሏ ከተሻጋሪ አልያም ወደ ሳጥን ይዛ የምትገባቸው ኳሶች የመጨረሻው ማረፊያው የተበላሸ ይሁን እንጂ አስፈሪ ዕድሎችን በተደጋጋሚ ፈጥራለች፡፡ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት 1ለ0 የንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
አዳማ ከተማ በሜዳው ከድሬዳዋ ጋር አንድ አቻ ተለያይቷል። ሰናይት ቦጋለ ለአዳማ ስታስቆጥር ታደለች አብርሀም የእንግዶቹን አስቆጥራለች። አቃቂ ቃሊቲ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሌላው ዛሬ የተደረገ ጨዋታ ሲሆን ኤሌክትሪኮች በፋና ዘነበ፣ መሳይ ተመስገን እና በራስ ላይ በተቆጠረ ጎል አማካኝነት 3-2 አሸንፈዋል። ለአቃቂ ፀባኦት መሐመድ፣ ሰላማዊት ጎሳዬ ሲያስቆጥሩ በኤሌክትሪክ በኩል ሰርካለም ኃይሉ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥታለች።
የ10ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ነገም ሲቀጥሉ መቐለ ከ አርባምንጭ እንዲሁም ጌዴኦ ዲላ ከ ሀዋሳ ከተማ ይጫወታሉ።
©ሶከር ኢትዮጵያ