ድሬዳዋ ከተማ የተከላካይ አማካዩን ይስሀቅ መኩሪያን አምስተኛ ተጫዋች በማድረግ አስፈርሟል፡፡
ዓምና በዓመቱ መጀመርያ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ቢያመራም ከደመወዝ ጋር በተያያዘ ሰጣገባ ውስጥ ገብቶ የነበረው ይህ ተጫዋች ወደ ሰበታ ከተማ በማምራት ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በሰበታ ከተማ በክረምቱ የዝግጅት ወቅት ኮንትራት እየቀረው ከተለያየ በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሶ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ያመራ ሲሆን በተከላካይ አማካይ ፍሬድ ሙሸንዲ ጋር ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ቡና ታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው መጫወት የቻለው ይህ የአማካይ ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ይስሀቅ መኩሪያ ቡናማዎቹን ከለቀቀ በኋላ በባህር ዳር ከተማ፣ ፋሲል ከነማ፣ ጅማ አባጅፋር እና ሰበታ ከተማ ተጫውቶ በማሳለፍ ከሁለት ክለቦች ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደግ ችሏል፡፡
ቀደም ብለው ኩዌክ አንዶህ፣ ፉይሴኒ ኑሁ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ እና ምንያምር ጴጥሮስን ያስፈረሙት ብርቱካናማዎቹ በቀጣይም ተጨማሪ ተጫዋች ለማስፈረም በሒደት ላይ መሆናቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡
©ሶከር ኢትዮጵያ