የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከእረፍት ሲመለስ ነገ ከሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች መካከል ፋሲል ከነማ ከ አዳማ ከተማ የሚያደርጉትን ጨዋታ የቅድመ ዳሰሳችን ይመለከተዋል።
በ14ኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ 2-2 በተለያየበት ጨዋታ በተፈፀመ የዲሲፕሊን ጥሰት ምክንያት አንድ የሜዳው ጨዋታን ከ150 ኪሜ ርቀት በላይ በሆነ ሜዳ እንዲያደርግ ቅጣት የተጣለበት ፋሲል ከነማ ነገ ቅጣቱን ባህር ዳር ላይ አዳማ ከተማን በመግጠም ተግባራዊ ያደርጋል። ባህር ዳር ከጎንደር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ነገ በርከት ያለ ተመልካች ጨዋታውን እንደሚከታተለው ይጠበቃል።
ፋሲል ከነማ ከአንደኛው ዙር የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ እንደማስመዝገቡ ወደ አሸናፊነት ተመልሶ የሊጉን መሪነት በጊዜያዊነት ለመረከብ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
የፋሲል ከነማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | አቻ | አሸነፈ | አሸነፈ | አቻ |
በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሚሰጠው ፋሲል በነገው ጨዋታ ተጋጣሚው ከሚመርጠው የጥንቃቄ አጨዋወት መነሾ ኳስ ለማግኘት ይቸገራል ተብሎ ባይገመትም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል በቂ የመቀባበያ እና የግብ እድል የመፍጠርያ ክፍተት ለማግኘት ሊቸገር ይችላል። በዚህም የሜዳውን ስፋት በመለጠጥ እና ጥሩ የማጥቃት ብቃት ያላቸው የመስመር ተከላካዮቹን በማሳተፍ እምብዛም የማይንቀሳቀሱት የአዳማ ተከላካዮችን ቅርፅ በመበታተን ቀዳዳዎችን መፈለግን አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። አጥቂው ሙጂብ ላይ ያነጣጠሩ ተሻጋሪ ኳሶችም ሌላው የጎል መፈለጊያ መንገዳቸው እንደሚሆን ይገመታል።
በነገው ጨዋታ ትኩረታቸውን ማጥቃት ላይ እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት ፋሲሎች ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚሚያደርጉት ሽግግር የተሻሉ እንደሆኑት ሁሉ በተቃራኒው ኳስ በሚያጡበት ጊዜ በቶሎ የመከላከል አደረጃጀታቸውን ካላስተካከሉ በፈጣኖቹ የአዳማ አጥቂዎች ሊቀጡ ይችላሉ።
ዐፄዎቹ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የሌለ ሲሆን በቅጣት ሽመክት ጉግሳን አያሰልፉም። ከእረፍት ዘግይተው ቡድኑን የተቀላቀሉት ሚኬል ሳማኬ፣ ጋብርኤል አሕመድ፣ ኦሲ ማውሊ እና ኢዙ አዙካም ከቡድኑ ጋር ልምምድ አለመስራታቸውን ተከትሎ የመሰለፍ አለመሰለፋቸው ሁኔታ አለየለትም።
የአዳማ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አቻ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ |
ከሜዳ ውጪ ችግሩ በተቃራኒ በሜዳ ላይ የተረጋጋ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው አዳማ ከተማ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የነበረውን ጥሩ ውጤት የማስቀጠል አላማ ይዞ የነገውን ጨዋታ ያደርጋል።
የአሸናፊ በቀለ ቡድን ከዚሀ ቀደም ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው ጨዋታዎች በተደራጀ ሁኔታ በመከላከል ቢያንስ አንድ ነጥብ አሳክቶ ለመመለስ ወደ ሜዳ የሚገባ ቡድን እንደመሆኑ በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ አቀራረብ ይጠበቃል። ከአራቱ ተከላካዮች ፊት በሁለት የተከላካይ አማካዮች የኋላ መስመሩን በሚጋርደው ቡድኑ በራሱ የሜዳ ክፍል በዛ ብሎ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የበረከት ደስታ እና ቡልቻ ሹራን ፍጥነት በመጠቀም የጎል ዕድል ለመፍጠር እንደሚተጋ ይጠበቃል።
ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን በመጠቀም ማጥቃትን የሚያዘወትረው ቡድኑ የፋሲል ተከላካዮች ወደ መሐል ሜዳ ተጠግተው ለመከላከል የሚሞክሩ በመሆኑ ክፍተቱን ለመጠቀም መጣሩ አይቀሬ ቢሆንም የዳዋ ሆቴሳ መሰለፍ አጠራጣሪ መሆን ለዕቅዳቸው መሳካት እንቅፋት ሊሆን ይችላል።
አዳማዎች በነገው ጨዋታ ከጃኮ ፔንዜ ጋር እየተፈራረቀ ግቡን የሚጠብቀው ደረጄ ዓለሙን በሀዘን ምክንያት የማይጠቀም ሲሆን ዳዋ ሆቴሳ በጡንቻ መሳሳብ ጉዳት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው ተብሏል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ስምንት ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ የተሸናነፉ ሲሆን በስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ጎሎችን የም በግንኙነቶቹ አስቆጥረዋል።
– ዘንድሮ በመጀመርያው ዙር አዳማ ላይ ተገናኝተው 0-0 ተለያይተዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-3-3)
ሚኬል ሳማኬ
ሰዒድ ሀሰን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባዬ – አምሳሉ ጥላሁን
ሱራፌል ዳኛቸው – ሀብታሙ ተከስተ – በዛብህ መለዮ
ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ዓ/ብርሀን ይግዛው
አዳማ ከተማ (4-2-3-1)
ጃኮ ፔንዜ
ሱሌይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – መናፍ ዐወል – ሱሌይማን መሐመድ
አማኑኤል ጎበና – አዲስ ህንፃ
በረከት ደስታ – ከነዓን ማርክነህ – ዱላ ሙላቱ
ቡልቻ ሹራ
© ሶከር ኢትዮጵያ