ነገ 9 ሰዓት በባህር ዳር ስታዲየም የሚደረገውን የባህር ዳር ከተማ እና የጅማ አባጅፋርን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
የሊጉ አወዳዳሪ አካል ቡድኖች ለውድድር የሚያበቃ ክፍያ ካልከፈሉ ለጨዋታ እንደማይቀርቡ መገለፁን ተከትሎ ሁሉም ክለቦች ክፍያቸውን ሲያጠናቅቁ ጅማ አባ ጅፋር አለማጠናቀቁን ተከትሎ ጨዋታው የመደረጉ ነገር አጠራጣሪ ሆኖ ቆይቷል። ቡድኑ ወደ ባህር ዳር ያመራ ቢሆንም ክፍያውን ስለማጠናቀቁ ከዐቢይ ኮሚቴውም ሆነ ከክለቡ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
የመጀመሪያውን ዙር የሊጉ ጨዋታ 5ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ባህር ዳር ከተማዎች የሁለተኛውን ዙር በጥሩ መንፈስ ለመጀመር እና የሜዳ ላይ አልሸነፍ ባይነታቸውን ለማስቀጠል 9 ሰዓትን ይጠባበቃሉ።
የባህር ዳር ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ |
በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ቡድኑ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች እጅግ ጠንካራ ነው። በተለይ ቡድኑ በጀብደኝነት ከማጥቃቱ በዘለለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመያዝ ጨዋታዎችን ሲያከናውን ይታያል። እርግጥ ይህ የጨዋታ መንገድ ከእለት ወደ እለት እየተቀዛቀዘ ቢመጣም ቡድኑ በሜዳው እጁን ሳይሰጥ ቆይቷል። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ የሜዳው ላይ ጨዋታዎች በፍጥነት በማጥቃት ለመጫወት እንደሚዘጋጅ ይገመታል።
ከምንም በላይ በነገው ጨዋታ ቡድኑ መስመሮችን በመጠቀም ሊንቀሳቀስ እንደሚችል ይታሰባል። በተለይ ጅማዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው የሚጫወቱ እና ግጥግጥ ብለው የሚከላከሉ ከሆነ ቡድኑ የመስመር ላይ አጨዋወቱን ሊያጠናክር ይችላል። ለዚህ አጨዋወት ደግሞ ሁነኛ መሳሪያ የሆነው ግርማ ዲሳሳ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከሚሮጣቸው ሩጫዎች በተጨማሪ የሚያሸንፋቸው የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ቡድኑን ሊጠቅሙ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ በመስመሮች መካከል በመገኘት አደገኛ ነገሮችን የሚፈጥረው ፍፁም ዓለሙ ለባለሜዳዎቹ ልዩነት ፈጣሪ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ቡድኑ የቆሙ ኳሶችን እና ተሻጋሪ ኳሶችን የመጠቀም ብቃቱ በመጨመሩ መፍትሄዎችን በሌላ መንገድ ሊያመጣ ይችላል።
በጉዳት እየታመሰ የሚገኘው ቡድኑ አሁንም በጉዳት ላይ የሚገኙ ወሳኝ ተጨዋቾቹን ሙሉ ለሙሉ ባለማግኘቱ ሊቸገር ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በመጀመሪያ ዙር የነበረበትን የግብ ማስተናገድ አባዜ ቀርፎ ካልቀረበ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ስል ለሆኑት የጅማ ተጨዋቾች እጅ ሊሰጥ ይችላል።
የጣናው ሞገዶቹ በነገው ጨዋታ የወሰኑ ዓሊ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ማማዱ ሲዲቤን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኙም። ከዚህ በተጨማሪ የመስመር ተጨዋቹ ዜናው ፈረደ ወደ ሜዳ መግባት አጠራጣሪ ነው ተብሏል።
የጅማ አባ ጅፋር ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | አቻ |
የአንደኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታን በሽንፈት ያጠናቀቁት ጅማ አባጅፋሮች ከተደቀነባቸው የወራጅ ቀጠና ስጋት ለመውጣት እና የመጀመሪያ የሜዳቸው ውጪ ድል ለማስመዝገብ ባህር ዳር ገብተዋል።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ዝቅተኛ ግብ የተቆጠረባቸው ጅማዎች (12) በነገውም ጨዋታ በሚታወቁበት ጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት እንደሚጫወቱ ይገመታል። በተለይ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት የሚከተለውን ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት በመተግበር እንደሚንቀሳቀስ ይታሰባል። ከምንም በላይ ቡድኑ ባህር ዳሮች በላይኛው የሜዳ ክፍል በምቾት የኳስ ቅብብሎችን እንዳያደርጉ እና ክፍተቶችን እንዳይጠቀሙ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
የአሰልጣኝ ጳውሎስ ተጨዋቾች በመከላከሉ ረገድ የተወጣለት እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉት ሁሉ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችም ጥሩ ናቸው። በተለይ ቡድኑ ፈጣን ሽግግሮችን በአግባቡ በማከናወን የተጋጣሚን ጊዜ ከባድ ለማድረግ ይጥራል። ከምንም በላይ ጅማዎች ነገ የኤሊያስ አህመድ ብቃት የሚሹ ይመስላል። ይህ ታታሪ ተጨዋች የመልሶ ማጥቃት ሂደቶችን ከማፋጠኑ ጎን ለጎን የሚያቀብላቸው ቁልፍ ኳሶች ባለሜዳዎቹን ሊፈትን ይችላል።
በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው ጅማ (10) በነገው ጨዋታ ግብ አካባቢ ያሉ ችግሮቹን ካልቀረፈ አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረቦችን በየጨዋታው በማስመልከት የጨዋታ መንገዱን ከሚገባው በላይ ለተጋጣሚ ያስጠናው ቡድኑ ነገ አቀራረቡን መለወጥ አለበት።
ጅማዎች አሌክስ አሙዙ፣ አብርሃም ታምራት እና መላኩ ወልዴን በቅጣት ምክንያት ሳይዙ ባህር ዳር ገብተዋል፡፡ በተጨማሪም ጋናዊው አጥቂ ያኩቡ መሀመድ እና ግብ ጠባቂው ሙንታሪም ከእረፍት ባለመመለሳቸው ከቡድኑ ጋር አይገኙም፡፡
የእርስ በእርስ ግንኙነት
በሊጉ ሦስት ጊዜ ተገናኝተው ሁለት ጨዋታ አቻ ሲለያዩ አንድ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር አሸንፏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)
ሀሪስተን ሄሱ
ሳላምላክ ተገኝ – አዳማ ሲሶኮ – አቤል ውዱ – ሚኪያስ ግርማ
ሳምሶን ጥላሁን – ዳንኤል ኃይሉ – ፍፁም ዓለሙ
ግርማ ዲሳሳ – ስንታየሁ መንግሥቱ – ዜናው ፈረደ
ጅማ አባጅፋር (4-2-3-1)
ሰዒድ ሀብታሙ
ጀሚል ያዕቆብ – ከድር ኸይረዲን – ኤፍሬም ጌታቸው – ኤልያስ አታሮ
ንጋቱ ገ/ሥላሴ – ሄኖክ ገምቴሳ
ተመስገን ደረሰ – ኤልያስ አህመድ – ኤርሚያስ ኃይሉ
ብዙዓየው እንዳሻው
© ሶከር ኢትዮጵያ