ቅድመ ዳሰሳ | ወልዋሎ ከ ሰበታ ከተማ

በ16ኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ ወልዋሎ በሜዳው ሰበታ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

አዲስ አሰልጣኝ ቀጥረው በርካታ ተጫዋቾች በማስፈረም ወደ ሁለተኛው ዙር የገቡት ወልዋሎዎች በአዲሱ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ እየተመሩ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የወልዋሎ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ

በነገው ጨዋታ የመጀመርያ ጨዋታቸው የሚያደርጉት አሰልጣኝ ዘማርያም ይዘውት የሚገቡትን አጨዋወት ለመገመት እጅግ ከባድ ነው። ሆኖም በውጤት ማጣት ውስጥ የሚገኘውን ቡድን ለቀናት ብቻ ልምምድ ያሰሩት አዲሱ አሰልጣኝ ከባለፈው የቡድኑ አቀራረብ ላይ ብዙም ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም።

ቡድኑን የመዘጋጃ በቂ ጊዜ ያልነበራቸው አሰልጣኙ ከቀድምት ክለቦቻቸው በመነሳት በቀጣይ ኳስን ለመቆጣጠር የሚሞክር እና በሚያጠቃበት ጊዜ መስመሩን በደምብ የሚጠቀም ቡድን ይሰራሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይህን አጨዋወት ነገ ይተገብሩታል ተብሎ አይገመትም። በዚህም ቡድኑ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች በመነሳት በመስመር እና በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሚያጠቃት ቡድን ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ የወረቀት ጉዳዮች ካልተጠናቀቁለት ብሩክ ገብረአብ ውጪ በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።

የሰበታ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

በመጨረሻው ሳምንት በሲዳማ ቡና በጠባብ ውጤት የተሸነፉት ሰበታ ከተማዎች ከአስራ ሁለተኛው ሳምንት በኃላ ያጡትን ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት አልመው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል።

ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በቅጣት እና በግል ጉዳት ምክንያት ወደ ዓዲግራት ይዘው ያልተጓዙት ሰበታዎች የወሳኝ ተጫዋቾቻቸው አለመኖር በወሳኙ የሜዳ ውጭ ጨዋታ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል።

በአብዛኛው ኳስ ይዞ መጫወት ምርጫው ያደረገ በአንዳንድ አጋጣሚዎችም ቀጥተኛ አጨዋወት የሚጠቀም ቡድን ያላቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በነገው ጨዋታ ኳስን ለመቆጣጠር አልመው ይገባሉ ተብሎ ይገመታል። ቡድኑ በአጨዋወቱ ወሳኝ ሚና ያለው መስዑድ መሐመድ በግል ጉዳይ ምክንያት ቢያጣም ገና ያልተደራጀው ተጋጣሚው ወልዋሎ ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ አልሞ ይገባል ተብሎ ስለማይታሰብ የተሻለ ኳሱን የመቆጣጠር ዕድል ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል። የመጫወቻ ሜዳው አመቺነትም ሌላው ቡድኑ ኳስን ለማንሸራሸር ምክንያት ይሆነዋል ተብሎ ይገመታል።

ሰበታዎች በነገው ጨዋታ ባኑ ድያዋራ በቅጣት (ከሲዳማ ቡና ጋር ባየው ቀይ ካርድ)፣ መስዑድ መሐመድ እና ዳንኤል አጄይ በግል ጉዳይ ፣ አዲሱ ፈራሚ ጃኮ አረፋት በወረቀት ጉዳዮች ምክንያት አይሰለፉም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ በ1ኛው ሳምንት ተገናኝተው ሰበታ ከተማ 3-1 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

ዓብዱልአዚዝ ኬይታ

ገናናው ረጋሳ – ዓይናለም ኃይለ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሐንስ

አመለ ሚልኪያስ – ዮናስ በርታ

ያሬድ ብርሀኑ – ራምኬል ሎክ – ኢታሙና ኬይሙኔ

ጁንያስ ናንጂቡ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረማርያም

ኢብራሂም ከድር – አንተነህ ተስፋዬ – አዲስ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

ታደለ መንገሻ – ደሳለኝ ደባሽ – ዳዊት እስጢፋኖስ

ናትናኤል ጋንቹላ – ፍፁም ገብረማርያም – ሲይላ ዓሊ

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ