ቅድመ ዳሰሳ| ሀዲያ ሆሳዕና ከ መቐለ 70 እንደርታ

ሀዲያ ሆሳዕና ከቅጣት መልስ በአብዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም መቐለ 70 እንደርታን የሚገጥሙበት ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

አዲስ አሰልጣኝ ከቀጠሩ በኋላ በጥሩ መነሳሳት ላይ የሚገኙት ነብሮቹ በቅጣት ምክንያት ሁለት የሜዳቸውን ጨዋታዎች ሀዋሳ ላይ ካደረጉ በኋላ ወደ ሜዳቸው በሚመለሱበት ጨዋታ ጥሩ ጉዟቸውን በማስቀጠል ሦስት ነጥብን ለማግኘት አልመው ይገባሉ ተብሎ ይገመታል።

የሀዲያ ሆሳዕና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ

በዝውውር መስኮቱ ሦስት ተጫዋቾች ያስፈረሙት ሆሳዕናዎች ሁለቱ አዳዲስ ፈራሚዎቻቸውን በነገው ጨዋታ አለማግኘታቸውን ተከትሎ በቋሚ አሰላለፍ ላይ ብዙም ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስር ኳስን መሰረት አድርገው እና እንደየአስፈላጊነቱ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት የሚያደርጉት ሆሳዕናዎች በነገው የሜዳቸው ጨዋታም ከባለፉት ጨዋታዎች የራቀ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎም አይገመትም።

ሆኖም ከተጋጣሚው አንፃር ሲታይ ከኳስ ጋር ምቾት የሚሰማቸው አማካዮች ያሏቸው ሆሳዕናዎች አጨዋወታቸን ይበልጥ የኳስ ቁጥጥር ላይ ይተመሰረተ የሚያደርጉበት ዕድል የሰፋ ነው። በዚህም ቡድኑ ጥሩ ባልነበረበት ወቅትም ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የቡድኑ የአማካይ ጥምረት በነገው ጨዋታ በተሻለ የማጥቃት ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ሲጠበቅ በአንፃሩ ቡድን በሁለት የአጥቂ ጥምረት ለሚጫወተው እና የመስመር አጨዋወትን ይከተላል ተብሎ የሚጠበቀውን የመቐለን ስል የማጥቃት ክፍል ላለመጋለጥ በተከላካይ ክፍሉ ላይ ለውጥ ማድረግ ሳይኖርበት አይቀርም።

ከዚህ በተጨማሪ የሚገኙትን ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ትልቅ ክፍተት የነበረው የአጥቂ ክፍሉ በዚ ጨዋታ ድክመቱን በሚገባ አርሞ ካልገባ ቡድኑ ከዚ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ሊቸግረው ይችላል።

ሆሳዕና በነገው ጨዋታ አዲስ ፈራሚዎቹ ሳሊፍ ፎፋና እና ተስፋዬ አለባቸውን በወረቀት ጉዳዮች አለመጠናቀቅ ምክንያት አያገኝም።

የመቐለ 70 እንደርታ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

በመጨረሻው የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ወደ ድሬ አቅንተው በጨዋታው መገባደጃ በተቆጥረባቸው ግብ ተሸንፈው የተመለሱት ቻምፒዮኖቹ ከመሪዎቹ ላለመራቅ ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት ብቸኛ አማራጫቸው ነው።

ከሜዳቸው ውጭ ቀጥተኛ እና የመስመር አጨዋወቶች ሲተገብሩ የቆዩት መቐለዎች በነገው ጨዋታ ጉዳት ላይ የነበሩት ዮናስ ገረመው እና ያሬድ ከበደን ጨምሮ አዲስ ፈራሚው ካሉሻ አልሀሰንን ማግኘታቸውን ተከትሎ በአማካይ ጥምረቱም ሆነ በአጠቃላይ የጨዋታ አቅራረብም ለውጥ ማድረጋቸው አይቀሬ ነው። በዚህም ቡድኑ ከባለፉት የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች በተለየ በአጨዋወት ላይ ለውጥ ያደርጋል ተብሎ ሲጠበቅ ተጋጣሚው ረጃጅም ኳሶች ለማምከን የማይቸገሩ ግዙፍ ተከላካዮች ያሉት እንደመሆኑ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከቀጥተኛ አጨዋወት ይልቅ በመስመር የሚያጠቃ ቡድን ይዘው ይቀርባሉ ተብሎ ይገመታል።

ሆኖም ቡድኑ ግዙፉ ናይጀርያዊው አጥቂ በጨዋታው አጋጣሚዎች የተሻለ የሀምሳ ሀምሳ ኳሶች ማሸነፍ የሚችል ከሆነ ረጃጅም ኳሶች የመጠቀሙ ነገርም እንዳለ ነው።

መቐለዎች በነገው ጨዋታ በግሉ ልምምድ ጀምሮ ለጨዋታ ብቁ ያልሆነው ሚካኤል ደስታ እና የወረቀት ጉዳዮች ያልጨረሰው ሙሳ ዳኦን ሳይዙ ወደ ሆሳዕና አምርተዋል።

በጨዋታው ሁለቱ ኢኳቶርያል ጊንያውያን ወንድማማቾ ፊሊፕ ኦቮኖ እና አቤር ኦቮኖ በተቃራኒ ይፋለማሉ።

እርስ በርስ ግንኙነት

– በአንደኛው ሳምንት በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ተገናኝተው መቐለ 70 እንደርታ 2-1 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ 

ሀዲያ ሆሳዕና (4-4-2)

አቬር ኦቮኖ

ፀጋሰው ዴማሞ – ደስታ ጊቻሞ – አዩብ በቀታ – ሄኖክ አርፊጮ

ሱራፌል ዳንኤል – አፈወርቅ ኃይሉ – ይሁን እንደሻው – በኃይሉ ተሻገር

ቢስማርክ አፒያ – ቢስማርክ ኦፖንግ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፊሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – ቢያድግልኝ ኤልያስ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ዮናስ ገረመው – ዳንኤል ደምሴ – ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ያሬድ ከበደ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ኦኪኪ ኦፎላቢ

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ