ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወልቂጤ ከተማ

በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረገውን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታን ቀጣዩ ዳሰሳችን ይመለከተዋል።

ከተከታታይ ድሎች በኋላ የመጨረሻዎቹን ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ከተከታዮቹ ያላቸውን ርቀት የማስፋት ዕድላቸውን ያመከኑት ፈረሰኞቹ መልሰው መሪነታቸውን ለመረከብ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ አቻ አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ

ከሜዳቸው ውጪ በጠንካራ መከላከል ወደ ሜዳ የሚገቡ ቡድኖችን ሲገጥም የጠራ የጎል ዕድል ለመፍጠር እንደሚቸገር በአዳማ ከተማው ጨዋታ ላይ የታየው ቅዱስ ጊዮርጊስ በነገው ጨዋታም በተመሳሳይ ለጥንቃቄ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊገባ ከሚችለው ወልቂጤ ፈተና ሊገጥመው ይችላል።

ከውጤቱ አስፈላጊነት አንፃር ከፍተኛ ጫና ፈጥረው እንደሚንቀሳቀሱ የሚጠበቁት ጊዮርጊሶች የሜዳውን ወደ ጎን በመለጠጥ ክፍተት ለማግኘት ጥረት በማድረግ ከመስመር ወደ መሐል አጥብበው በሚገቡት የመስመር አጥቂዎቻቸው የጎል አጋጣሚዎችን እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አስቻለው ታመነ ከረጅም ጊዜ ጉዳቱ ሲመለስ ለዓለም ብርሀኑ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና አቤል እንዳለ በጉዳት ይህ ጨዋታ ያልፋቸዋል፡፡

የወልቂጤ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ ተሸነፈ አቻ አሸነፈ አሸነፈ

በመጨረሻው የአንደኛ ዙር ጨዋታ ወደ ዓዲግራት ተጉዘው በወልዋሎ 3-1 ከመመራት በመነሳት 3-3 የተለያዩት ወልቂጤዎች ከሦስት ጨዋታ በኋላ ወደ ድል መመለስን አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ከሜዳ ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች መጥፎ የማይባል ውጤት እያስመዘገበ የሚገኘው ወልቂጤ በነገው ጨዋታ ሦስት ቀዳሚ ተመራጭ ተከላካዮቻቸውን የማያሰልፉ መሆኑ የኋላ ክፍላቸውን ከጥቃት ተጋላጭነት መከላከል ላይ የተመሰረተ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይገመታል። በዚህም ከተከላካዮች ፊት የመከላከል ባህርይ ባላቸው አማካዮች ለኋላ ክፍሉ ሽፋን በመስጠት ፈጣኖቹ አጥቂዎቻቸው ላይ ያነጣጣረ የመልሶ ማጥቃትን እንደሚከተሉ ይገመታል። የጫላ ተሺታ እና አህመድ ሁሴን ፍጥነትም ሁነኛ የጥቃት መሳርያቸው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በወልቂጤ በከል በጉዳት ቶማስ ስምረቱ የማይኖር ሲሆን በግል ጉዳይ ዐወል መሐመድ እና አዳነ በላይነህ አይሰለፉም። መሐመድ ሻፊ ከጉዳቱ በማገገም ቀላል ልምምድ መስራት ሲጀምር አዲስ ፈራሚዎች ለጨዋታው እንደሚደርሱ ተነግሯል።

እርስ በርስ ግንኙነት

በአንደኛው ሳምንት ባቱ ላይ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ፓትሪክ ማታሲ

ሄኖክ አዱኛ – ምንተስኖት አዳነ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ – መሐሪ ሐና

ሙሉዓለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ

ጋዲሳ መብራቴ- ጌታነህ ከበደ – አቤል ያለው

ሰልሀዲን ሰዒድ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ይድነቃቸው ኪዳኔ

ይበልጣል ሽባባው – ዳግም ንጉሴ – መሐመድ ሻፊ – አቤኔዘር ኦቴ

አዳነ ግርማ – አሳሪ አልማህዲ – በረከት ጥጋቡ

ጫላ ተሺታ – አህመድ ሁሴን – ሳዲቅ ሴቾ

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ