በድሬዳዋ ስታዲየም የሚደረገውን የነገ 9:00 ጨዋታ የዳሰሳችን ማሳረጊያ አድርገነዋል።
የአንደኛውን ዙር በድል በማሳረግ ባለፉት ቀናት ዝውውር ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ከራጅ ቀጠናው ለማምለጥ በጥሩ ተነሳሽነት ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ከነገው ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ለቀጣይ ጉዟቸው ወሳኝ ነው።
የድሬዳዋ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | ተሸነፈ | አቻ | ተሸነፈ | አሸነፈ |
ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር በመለያየት በምትካቸው ጥቂት የማይባሉ ተጫዋቾችን ያስፈረሙት ድሬዳዋ ከተማዎች እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በሁለተኛው ዙር ጠንክረው ለመቅረብ ያደረጉት ጥረት አመዛኞቹ ፈራሚዎች ለጨዋታው የማይደርሱ በመሆኑ ምን ያህል እንደሚያስኬድ የነገው ጨዋታ ጠቋሚ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።
ዘንድሮ የጎል ዕድል መፍጠር ላይ ደካማ የሆነው ድሬዳዋ ተጋጣሚው ሀዋሳ በዚህ ዓመት ከሜዳው ውጪ ያለው የጥንቃቄ አቀራረብ በጊዜያዊ አሰልጣኙ ስርም በቶሎ ለውጦ ይቀርባል ተብሎ አለመጠበቁ ይበልጥ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ብርቱካናማዎቹ ካስፈረሟቸው አምስት ተጫዋቾች ሄኖክ ኢሳይያስን ብቻ ነገ ሲያገኙ ይስሀቅ መኩሪያ፣ ምንያምር ጴጥሮስ፣ አንዶህ ኩዌኪ እና ፈይሴኒ ኑሁን አያገኝም። ነገ በተጠባባቂ ወንበር ላይ አንድ ግብ ጠባቂን ጨምሮ ሦስት ብቻ ተጫዋቾችን እንደሚያስቀምጥ የሚጠበቀው ቡድኑ በጉዳት ወሳኝ ተጫዋቾቹንም ያጣል። ሳምሶን አሰፋ፣ በረከት ሳሙኤል፣ ያሬድ ታደሰ፣ ሙህዲን ሙሳ፣ ረመዳን ናስር እና ፈርሀን ሰዒድ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾች ሲሆኑ ያሬድ ሀሰን እና ያሲን ጀማልም መሰለፋቸው አጠራጣሪ ነው፡፡
የሀዋሳ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ |
በመጨረሻው የአንደኛ ዙር ጨዋታቸው ፋሲልን 2-0 ከመመራት ተነስተው ማሸነፍ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በጊዜያዊ አሰልጣኙ ብርሀኑ ወርቁ እየተመሩ ዙሩን በድል ለመክፈት ያልማሉ።
ቡድኑ በጊዜያዊ አሰልጣኝ እየተመራ ወደ ሜዳ የሚገባ እንደመሆኑ አሰልጣኙ ይዞት ሊቀርበው ስለሚችለው አቀራረብ ለመተንበይ አዳጋች ቢሆንም ብርሀኑ ወርቁ በወጣት ቡድኑ ያሰለጠናቸውን በርካታ ተጫዋቾች ባህርይ የሚረዳ ከመሆኑ አንፃር የአጥቂዎቹን ፍጥነት በመልሶ ማጥቃት ውጤታማ የማድረግ እቅድ ይዞ እንደሚገባ ይገመታል።
በሀዋሳ በኩል የአንድ ዓመት እገዳ የተጣለበት አለልኝ አዘነ እና ጉዳት ላይ የሚገኘው እስራኤል እሸቱ ወደ ድሬዳዋ አላመሩም። ዳንኤል ደርቤ በገጠመው መጠነኛ ጉዳትም የመሰለፉ ነገር አጠራጥሯል፡፡
በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ምትክ ቡድኑን የሚመራው የቀድሞው የቡድኑ ተጫዋች ብርሀኑ ወርቁ በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ መነሳሳት እንዳለ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡
የእርስ በእርስ ግንኙነት እውነታዎች
– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 17 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ 6 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ አምስት አሸንፏል። በቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ድሬዳዋ ከተማ 17 ጎሎች በማስቆጠር ብልጫ ሲኖረው ሀዋሳ ከተማ 16 ጎሎችን አስቆጥሯል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)
ፍሬው ጌታሁን
ያሲን ጀማል – ፍሬዘር ካሳ – ያሬድ ዘውድነህ – አማረ በቀለ
ቢኒያም ጾመልሳን – ፍሬድ ሙሸንዲ – ኤልያስ ማሞ – ሄኖክ ኢሳይሳስ
ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ዳኛቸው በቀለ
ሀዋሳ ከተማ (4-4-2)
ሀብቴ ከድር
ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – መሳይ ጳውሎስ – ያኦ ኦሊቨር
ሄኖክ ድልቢ – ተስፋዬ መላኩ – አስጨናቂ ሉቃስ – ዘላለም ኢሳይያስ
ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ
© ሶከር ኢትዮጵያ