አቡበከር ናስር በኢትዮጵያ ቡና መለያ የመጀመርያውን ሐት-ትሪክ ስለመስራቱ ይናገራል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ዛሬ ጅማሮውን ሲያደርግ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ስሑል ሽረን የገጠመው ኢትዮጵያ ቡና በአቡበከር ናስር ሐት-ትሪክ እና ሀብታሙ ታደሰ ሁለት ጎሎት በመታገዝ ስሑል ሽረን 6-1 በመርታት ሁለተኛው ዙር በአስደናቂ ውጤት ጀምሯል። በወጣትነት ዕድሜው ቡድኑን በአንበል እየመራ ወደ ሜዳ የገባው እና በጨዋታው ሐት-ትሪክ የሰራው አቡበከር ናስር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
ቡድናችሁ አሁን እየተነቃቃ በውጤትም በደረጃ እየተሻሻለ መጥቷል። እስኪ ከውጤት ማጣት ጋር ተያይዞ ጫና ውስጥ የነበራቹሁበትን ጊዜ አስታውሰኝ?
ያ ጊዜ ለእኛ ከባድ ነበር። ቡድኑን ውጤታማ አድርገን ደጋፊውን ለማስደሰት በነበረን ከፍተኛ ጉጉት አሸንፈን መውጣት የምንችልባቸውን ጨዋታዎችን በተደጋጋሚ ነጥብ መጣላችን ጫና ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል። ጎል መሆን የሚችሉ ኳሶች የምንስትበት መንገድ ምን ያህል ጫና ውስጥ እንደገባን ማሳያ ነው።
ከጉጉት ውጭ ምንም ሊሆን አይችልም። እንደሚታወቀው ቡድናችን አጀማመሩ ጥሩ ነበር። ብዙ ጎሎችን ያስቆጠርነባቸው ጨዋታዎችም ነበሩ። በኋላ ላይ የቡድኑ ውጤት ሳናስበው እየጠፋ ሲመጣ ማሸነፍ አለብን ብለን ጓጉተን መግባታችን የፈጠረብን ከፍተኛ ጉጉት ያመጣው ችግር ነበር። ሆኖም ደጋፊው፣ የክለቡ አመራሮች እና በተለይ አሰልጣኛችን በሰጡን ድጋፍ ድክመቶቻችንን እያረምን አሁን በጥሩ መነቃቃት ላይ እንገኛለን።
በዚህ ሁሉ ውጤት መጥፋት አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ እናተን የተከላከለበት መንገድ እንዴት አገኘኸው ?
እኔ በጣም ነው ሳስበው የሚገርመኝ። አሰልጣኝ ተጫዋቾቹ ውጤት ሲያመጡ ብቻ ሳይሆን በውጤት ቀውስ ውስጥ ሲሆኑም ከተጫዋቾቹ ጎን ሊቆሙ ይገባል። አሰልጣኝ ካሳዬ በዛ ችግር ሰዓት ከእኛ ጎን የቆመበት መንገድ አስደናቂ ነው። ካሳዬ ተጫውቶ ያለፈ በመሆኑ ያለውን ነገር በሚገባ ያውቀው ስለነበር በደንብ ነበር ይከላከልልን የነበረው። ለዚህም ነው ለእርሱ ያለንን ክብር ለመግለፅ ባለፈው ሳምንት ወላይታ ድቻን ባሸነፍንበት ጨዋታ ወቅት የእርሱን መለያ 15 ቁጥር ለማሳየት የሞከርነው።
በዋናው ቡድን በመጫወት ከአራት ዓመት ያልበለጠ ጥቂት ዕድሜ ነው ያለህ። ዛሬ ቡድኑን በአንበልነት እየመራህ በመግባት የመጀመርያ ሐት-ትሪክ ሠርተሀል…
ቡድኑን አንበል በመሆን መምራቴ እና በኢትዮጵያ ቡና መለያ የመጀመርያውን ሐት-ትሪክ መስራቴ አስደስቶኛል። ዛሬ ለእኔ ልዩ ቀን ነው። ኢትዮጵያ ቡናን የሚያክል ታላቅ ቡድን በአንበልነት መምራት የፈጠረብኝ ተነሳሽነት ቀላል አይደለም። ዛሬም በማሸነፋችን ውስጥ እኔ በግሌ ሐት-ትሪክ በመስራቴም ደስተኛ አድርጎኛል።
በቀጣይ ጨዋታዎች ከኢትዮጵያ ቡና ምን እንጠብቅ?
የዛሬው ጨዋታ ውጤት በጣም ያስፈልገን ነበር። ይህን ጨዋታ አሸንፈን መውጣት እንዳለብን ተነጋግረን ነው የገባነው። ይህ በመሳካቱ ደስተኞች ነን። በቀጣይ ጨዋታዎች የተሻሉ ውጤቶችን እያስመዘገብን ደጋፊዎቻችንን እናስደስታለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ