የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት ውሎ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሞየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ አዳማ ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ኢ/ወ/ስ/አካዳሚ፣ ወላይታ ድቻ ፣ ሱሉልታ ከተማ እና ፋሲል ከነማ (ፎርፌ) ድል ቀንቷቸዋል።

ምድብ ሀ

ረፋድ 04:00 በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ በተካሄደው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በወጣቶች አካዳሚ 2-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

በጨዋታው የመጀመርያ 30 ደቂቃዎች ቡናማዎቹ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ የጎል እድል በመፍጠርም ረገድ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ ነበሩ። ፍራኦል ደምሰው በጥሩ ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ነብዩ ዳዊት በቀጥታ ወደ ጎል የመታው ኳስ እና የግቡ ቋሚ የመለሰበት በአጋጣሚ በኢትዮጵያ ቡና በኩል የመጀመርያ ሙከራ ነበር። ብዙም ሳይቆይ የቡናው አጥቂ በየነ ባንጃ ከመስመር ወደ ሳጥን ቆርጦ በመግባት ሌላ ጎል መሆን የሚችል ዕድል ቢፈጥርም የአካዳሚው ግብጠባቂ አቤኔዘር ፈይሳ አድኖበታል። ቡናማዎቹ በጥሩ የኳስ ቁጥጥር የጎል አጋጣሚ ለመፍጥ የሚያደርጉት ጥረት መልካም የሚባል ቢሆንም የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ የሚያበላሿቸው ኳሶች የኃላ የኃላ ቡድኑን ነጥብ አሳጥቶታል።

ቀስ በቀስ ወደ እንቅስቃሴ የገቡት አካዳሚዎች ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ ከመዓዘን ምት የተሻገረን ኳስ በተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ተመስገን ቢያዝን ጠብቆ በግራ እግሩ ኳሱ አየር ላይ እያለ በመምት ግሩም የመጀመርያ ጎል ለአካዳሚ አስቆጥሯል።

ከመጀመርያው አጋማሽ ከነበራቸው መቀዛቀዝ ወተው ጎል በማስቆጠራቸው ተነቃቅተው የተመለሱት አካዳሚዎች በተለይ አጥቂዎቹ ኤልያስ እንደሻው እና ከድር አሊ እግራቸው ኳሱ ሲገባ በፍጥነት ወደ ማጥቃት ሽግግር ውስጥ የሚገቡበት ጥምረት ለኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ፈተና ነበር። ጎል ለማስቆጠር ነቅለው የወጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተመሳሳይ አጨዋወት ወደ ፊት ቢሄዱም ሦስተኛ የሜዳው ክፍል ኳሳቸው እየተቋረጠ በራሳቸው ላይ የመልሶ ማጥቃት አደጋ ሲፈጠርባቸውም ተመልክተናል።

በብዙ ክለቦች እይታ ውስጥ የገባው እና ዓምና ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ስኬታማ ቆይታ ያደረገው የወደፊት ተስፋኛ አጥቂ መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው ከድር ዓሊ ከመሐል ሜዳ ፊት ለፊት የተጠለለትን ኳስ ሳጥን ውስጥ በደረቱ አውርዶ በሚገርም ሁኔታ አስደናቂ ሁለተኛ ጎል ለአካዳሚ አስቆጥሯል። በውድድሩ ላይ ከተመለከትናቸው ቡድኖች ተገቢ የሆነ ዕድሜ ይዞ የቀረበው አካዳሚ በመጨረሻም ጨዋታውን ተቆጣጥረው 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን 3-0 አሸንፏል። ዳግም ፀጋአብ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ዮርዳኖስ ፀጋዬ አንዷን ጎል አስቆጥሯል።

ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ መከላከያን 2-0 አሸንፏል። መሳይ ኒኮላ እና ኬኔዲ ከበደ የድቻን ሁለቱን የድል ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ ያለ ጎል ሲለያዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሳምንቱ አራፊ ቡድን ነው።

ምድብ ለ

ጎንደር ላይ ወልቂጤ ከተማን ያስተናገዱት ፋሲል
ከነማዎች በፎርፌ አሸንፈዋል። ፋሲሎች እና የጨዋታው ዳኞች በስፍራው ቢገኙም ወልቂጤዎች ባለመገኘታቸው ለሰላሳ ደቂቃ ከተጠበቁ በኋላ ለፋሲል ፎርፌ ተሰጥቷል።

አዳማ ከተማ ከሜዳው ውጪ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-1 አሸንፏል። ሙዓዝ ሙኅዲን ሁለቱንም የአዳማ ጎሎች በማስቆጠር የሊጉን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት መምራት ሲጀምር በረከት የኤሌክትሪክን ጎል አስቆጥሯል።

ሱሉልታ ከተማ ሀላባን በኢሳይያስ በላይ እና ኢሳይያስ ኃይሉ ጎሎች 2-0 ሲያሸንፍ አሰላ ኅብረት ከ መድን ያለ ጎል ተለያይተዋል። አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የዚህ ሳምንት አራፊ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ