“ያሳለፍኩትን የጎዳና ህይወት ሰው ሲጠይቀኝ እንባዬ ይመጣል” እስራኤል መስፍን
በኢትዮጵያ ቡና ዋናው ቡድን ሦስተኛ ግብጠባቂ ነው። ተወልዶ ያደገው አሰበ ተፈሪ (ጭሮ) ነው። በልጅነት ዕድሜው አሳዳጊ አያቱ ህይወታቸው በማለፉ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እጅግ አስቸጋሪ የሆነ የህይወት ውጣ ውረድን በጎዳና ላይ አሳልፏል። ከሰፈር የጨርቅ ኳስ አንስቶ በኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኒያላ ከ17 ዓመት በታች ቡድን፣ ከ2009 ጀምሮ ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና ከተስፋ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በጫወት ያሳለፈው ተሰረፈኛ ግብጠባቂ እስራኤል መስፍን ይባላል። እስራኤል ስላሳለፈው የጎዳና ህይወት እና በኢትዮጵያ ቡና ወደ ፊት ሰለሚያስበው ህልሙ ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ተናግሯል።
ስለ ትውልድ እና ዕድገትህ አጫውተኝ?
ተወልጄ ያደኩት በአሰበ ተፈሪ ከተማ ነው። የዕድሜዬን አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፍኩት አያቴ ጋር ነው። በአጋጣሚ አያቴ በሞት ስትለየኝ ብቻዬን በመሆኔ እናት እና አባቴን ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ መጥቻለው። ሆኖም በተለይ ከአባቴ ጋር ልንስማማ ባለመቻላሌ ጎፋ መብራት ኃይል አካባቢ የጎዳና ህይወትን መኖር ጀመርኩ።
አስቸጋሪውን የጎዳና ህይወትህን እመለስበታለው. እስቲ የእግርኳስ መጫወትን እንዴት እንደጀመርክ ንገረኝ?
እንደማንኛውም እግርኳስ ተጫዋች የካልሲ ኳስ እየተጫወትኩ ነው ያደኩት። አዲስ አበባ ከመጣው ጊዜ ጀምሮ የጎዳና ህይወት ባሳለፍኩበት መብራት ኃይል ጎፋ አካባቢ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ሜዳ ይገኛል። በዚህ ሜዳ ላይ የቀድሞ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋቾች የጤና ስፖርት ማኀበር ሲጫወቱ እንደ አጋጣሚ ግብጠባቂያቸው ሲቀር የቀድሞ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋች እና ም/አሰልጣኝ የነበረው ኤርሚያስ ተነስና ግባ ብሎኝ እንድጫወት ያደርጉኛል። ከዚህ በኃላ ነው አሰልጣኝ ኤርሚያስ አቅሜን ሲመለከቱ በቀጥታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እንድጫወት አደረጉኝ። በዚህ ምክንያት የወደፊት ህልሜን አንድ ብዬ ጀመርኩ።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ ብዙም ሳትቆይ ነው ሦስት ዓመት ወደቆየህበት ኒያላ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ያመራኸው…
እንዳጋጣሚ ውድድር ከተጀመረ በኃላ ስለነበረ ኤሌክትሪክ የገባሁት መጫወት ሳልችል የአሁን የኢኮስኮ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑዕሰገድ እንቅስቃሴዬን አይቶ ወደ ኒያላ ታዳጊዎች ቡድን በ2006 ወሰደኝ። በዚህም ክለብ ለሦስት ዓመት መጫወት ችያለው። ይገርምሀል ቡና ዋናው ቡድን ገብቼ በካምፕ ማደር እስከ ጀመርኩበት ጊዜ ድረስ ያለፉትን ስድስት ዓመታት ቀን ልምምድ እየሰራው ለሊት አድር የነበረው ጎዳና ላይ ነበር። አንድ ሰው እንዲያውም በቆርቆሮ በተሰራ ተንቀሳቃሽ የጥበቃ ቤት አይነት ሰርቶልኝ ነበር አድር የነበረው።
በጣም አስገራሚ የህይወት ጉዞህን እያጫወትከኝ ነው። ከኒያላ ወደ ኢትዮጵያ ቡና እንዴት ልትመጣ ቻልክ?
በ2009 አሰልጣኝ ታዲዮስ ነበር ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመጣኝ። እርሱ አስቦ የነበረው ከ17 ዓመት በታች ቡድን እንድጫወት ነበር። ሆኖም በኤም አራይ ምርመራ ዕድሜዬ በማለፉ ለተስፋ ቡድኑ በአሰልጣኝ ዮሴፍ እና እድሉ ደረጄ ስር መጫወት ጀመርኩ። እዛም በነበረኝ ጥሩ ነገር 2011 ወደ ኢትዮጵያ ቡና ዋናው ቡድን ማደግ ችያለው። በአሁኑ ሰዓት የቡድኑ ሦስተኛ ግብጠባቂ በመሆን እየሰራሁ እገኛለው።
ዓምና በፕሪምየር ሊጉ እና በአንድ ጨዋታ ላይ የመሰለፍ አጋጣሚዎች አግኝተህ ነበር ?
አዎ ዓምና በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ በሆነው ከመከላከያ ጨዋታ ላይ እንዲሁም በህዳሴው ግድብ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ ቋሚ ተሰላፊ በመሆን አገልግያለው። ወደፊትም ህልሜ ረዥም ነው። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ጥሩ የስኬት ዓመታትን አሳልፋለሁ።
ቅድም እንደነገርከኝ ለስድስት ዓመታት ህልምህን ለማሳካት አስቸጋሪ የሚባል የጎዳና ህይወትህ አሳልፈሀል። እስቲ ያንን የመከራ ጊዜ አጫውተኝ..
እንደምታቀው እግርኳስ መጫወት በራሱ ከባድ ነው። ኳስ ተጫዋች ለመሆን ብዙ ነገሮች ያስፈልጋሉ። ይህ ችግር እያለ ነው ቀን ልምምዴን በሚገባ እየሰራው ሌሌት ጎዳና አድር የነበረው። ቀን ከፀሀይ ሌሊት ብርድ ጋር እየታገልኩ እራሴን በዲሲፒሊን ጠብቄ ምንም አይነት ሱስ ሳይኖርብኝ አስቸጋሪውን ህይወት እገፋ የነበረው። በጣም የሚገርመኝ የሰው መውደድ አለኝ። ሁሉም ይመክረኛል፣ የምጠይቃቸውን ያደርጉልኛል፣ በርታ አይዞህ ትልቅ ደረጃ ትደርሳለህ አሁን እንዲህ መሆንህን አታስብ ይሉኝ ነበር። ይህ ምክራቸው ድጋፋቸው ጥንካሬ ሆኖኝ እዚህ ደረጃ ደረስኩኝ እንጂ ያለፈው ህይወቴ በጣም አስቸጋሪ በመከራ የተሞላ ነበር።
አሁን ላይ ሆነህ ወደ ኃላ ስታስበው ምን አይነት ስሜት ይሰማሀል?
(እያለቀሰ በእንባ ይሄን ይናገራል) ያሳለፍኩትን የጎዳና ህይወት ሰው ሲጠይቀኝ እንባዬ ይመጣል። ሰው ሁሉ ያለፈበትን ህይወት ያውቀዋል። የእኔ ግን በጣም ከባድ ነበር። በዙርያዬ መልካም ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ እንዲህ ቆሜ አላወራም ነበር።
አይዞህ… (ከዚህ በኃላ እንባው እየቀደመው ለማውራት ተቸግሯል) አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ልጠይቅህ.. ወደፊት ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ምን ታልማለህ?
ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሌሎች ተጫዋቾች የሰሩትን ታሪክ ለመስራት ትልቅ ህልም አለኝ። ብዙ ነገሮችን አስባለሁ። ለብዙዎችም ከጎዳና ተነስቼ ትልቅ ደረጃ የደረሰ ተጫዋች ተብዬ ምሳሌ መሆን እፈልጋለው። በዚህ አጋጣሚ ለእኔ እዚህ መድረስ ትልቅ አስተዋፆኦ ያደረጉልኝን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ።
© ሶከር ኢትዮጵያ