የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በሴፕቴምበር 2016 በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመጀመርያውን የማጣርያ ጨዋታ ከአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን ጋር በዚህ ወር መጨረሻ ያደርጋል፡፡
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመሩት ሉሲዎቹ መቀመጫቸውን በአፋረንሲስ ሆቴል ያደረጉ ሲሆን በዛሬው እለት ዝግጅታቸውን ጀምረዋል፡፡ የመጀመርያ ልምምዳቸውንም ዛሬ ጠዋት ሱሉልታ በሚገኘ ሜዳ አከናውነዋል፡፡ በዛሬው የልምምድ ፕሮግራም ቡድኑ ለሁለት ተከፍሎ የተለማመደ ሲሆን ፈጣን የኳስ ቅብብል ላይ የተመሰረተ ልምምድ ሲሰሩ ተስተውሏል፡፡
አሰልጣኝ ብርሃኑ ባለፈው ሳምንት ይፋ ካደረጉት 30 ተጫዋቾች መካከል በዛሬው የመጀመርያ ልምምድ 26 ተጫዋቾች ተገኝተዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሷ ትዕግስት ዘውዴ ሪፖርት ባለማድረጓ ከቡድኑ ራሷን እንዳገለለች ተቆጥራ የተቀነሰች ሲሆን በውጭ ሃገር የመጫወት እድል እየሞከረች የምትገኘው ሎዛ አበራ ፈቃድ ጠይቃ በዛሬው ልምምድ ላይ አልተገኘችም፡፡
የመከላከያዋ አማካይ እመቤት አዲሱ እና የኤሌክትሪኳ ፅዮን ፈየራ ዛሬ ለክለቦቻቸው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የሚያደርጉ በመሆኑ በልምምዱ ላይ ያልተገኙ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው፡፡ የደቡብ ዞን የአንደኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች እሁድ ሲደረጉ ከዞኑ ክለቦች የተመረጡት ታሪኳ በርገና ፣ ገነት ፍርዴ ፣ አዲስ ንጉሴ ፣ የካቲት መንግስቱ እና ትደግ ፍስሃ ለክለቦቻቸው ለመጫወት ወደየክለቦቻቸው ያመራሉ፡፡
ቡድኑ ቀጣዮቹን 5 ቀናት በሱሉልታ እና በአዲስ አበባ ስታድየም በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ የሚያደርግ ሲሆን ስብስቡን ወደ 25 በመቀነስ ከሀሙስ እለት ጀምሮ የልምምድ ቦታውን ሙሉ ለሙሉ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም ያዞራል ተብሏል፡፡
-በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመካከለኛው ዞን ከ10ኛው ሳምንት ጀምሮ የሚደረጉት ጨዋታዎች በብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት ምክንያት ላልታወቀ ጊዜ መራዘማቸው ታውቋል፡፡